Friday, January 20, 2017

እንዲያው ለነገሩ



እንዲያው ለነገሩ
እንዲያው ለነገሩ ምንድነው አሉ ፍጥረት?
እንዴት ያለ ነው አሉ ውበት
ምንድር ነውስ ይኼ ስኬት
ብር በጆንያ ብቅል ይመስል መጋዘን ሞልቶ
ምርጥ ምርጡ ሁላ ተበልቶ ተጠጥቶ፣
ቁንጣን ችጋርን ተጣግቶ
በቪላ በዘበናይ ኦቶሞቢል ተንደላቆ
በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት መጥቆ ተራቆ
መኖር ነው ወይ የመኖር ትርጉሙ
የክስተታችን ምሥጢር የውነት ጣዕሙ

እንዲያው ለነገሩ ምንድነው አሉ ፍጥረት?
እንዴት ያለ ነው አሉ ውበት
ምንድር ነውስ ይኼ ስኬት

ቆሎ ቆልቶ ንፍር አንፍሮ፣ ጥሬ ከጮማ አማርጦ በልቶ
ለቤት ግድግዳ ላስቲክ ቋጥሮ፣ አሊያም በጡብ ገንብቶ
ጧት ማታ በታጠፈ እንጀት ፈጣሪን ለምኖ
ተስፋን ሰንቆ በተስፋ ተማምኖ ተስፋ ብቻ ገኖ
መኖር ብቻ ነው ወይ የመኖር ትርጉሙ
የክስተታችን ምሥጢር የውነት ጣዕሙ

እንዲያው ለነገሩ ምንድነው አሉ ፍጥረት?
እንዴት ያለ ነው አሉ ውበት
ምንድር ነውስ ይኼ ስኬት

በዋልንበት ላናድር፣ ባደርንበት ላንውል
በተስፋ ጭልፋ፣ ከንቱ የምንዋልል፣ የምንገዋለል
እንዲያው ለነገሩ ምንድነው አሉ ፍጥረት?
እንዴት ያለ ነው አሉ ውበት
ምንድር ነውስ ይኼ ስኬት
                                        
ታህሳስ 25/ 1995

No comments:

Post a Comment