Sunday, January 15, 2017

አቤቱታዬ




ፍቅርሽ ሲፀነስ ባይኔ
ያኔ ገና ያኔ
ልቤ ተመኝቶ ነበር
በጣም ብዙ፣ ብዙ ነገር
የፍቅር ረሃብ፣ የፍቅር ጥማቱ
ግድ ቢለኝ ነው ኃይልና ብርታቱ
ስፈራ ስቸር
ስግደረደር
ይገባሽ ይሆን ብዬ እውነቱ፣ ፍፁም መረታቴ
 አናገርኩሽ አንዴ፣ ቢታይሽ ብዬ ውስጣዊ ጉዳቴ

አንቺ ግን፣ አንቺ ግን ምንም አልታየሽም
ረቂቅ ቅኔ አድርገሽው፣ ከቶ አልገባሽም
ሁሉን በጅምር መንገድ ላይ ጥለሽው
ለትዝታዬ ትዝታን በላዩ ላይ ነቅስሽ፣ ወቅረሽው
እንደ ድንጋይ ሐውልት እንደ ጡብ ቀርፀሽው
ዝንት ዓለም እንዳልረሳሽ፣ አደራ ሰጥተሽኝ
ባንቺ ውስጥ፣ መላ መላዬን አፈር አለበስሽኝ
እያየሁ በቁሜ ገንዘሽ፣ አፈር ምሰሽ ቀብረሽኝ

እኔን ግን እንደ ምትረግጪው ትብያ
እንደ አንድ ወቅት ቡቃያ
እንደ የአንድ ወቅት መኸር፣
እንደተበላ ማዕድ፣ እንደማይዘከር
ልትረሽ ፍፁም ከነመፈጠሬ
ዳግም ላታይ ላታናግሪኝ
መንገድ ላይ ትተሽኝ ብቻዬን
ልታርቂ ጭራሽ ከልብም ከዓይን

በወርቅ በብር ልትደምቂ
ጐጆሽን ብቻ ልታሞቂ
ከቁር ከብርዱ እኔን ጥለሽ
ርቆ መሔዱ አስቻለሽ።



ከሙታኑም የለሁ ካሉትም እንዲሁ
ዛሬም እንደገና አንቺኑ እላለሁ
በልቤ ያቆምሽውን ሐውልት
አድሰዋለሁ ዛሬም በጽናት በትባት
ብትርቂኝም ብዙ፣ ከማልደርስበት ቦታ
አልቀየርኩም ቦታ፣ አለሁ ከዚያው ቦታ

ያንቺ ፍቅር እንዲህ ቢያደርገኝም
ሠርክ ከንቱ ቢያለፋኝም፣ ባያለማኝም
ብቆጠርም ከሙታን ተርታ
ባላገኝም ባንቺ ዘንድ ቦታ

ልቤ ፍፁም አይሞትም፣ ልንገርሽ! ሕያው ነው ዘላለም
ይዞት ይዞራል ያረገዘውን ሽል፣ አሁንም ይወለድ አላለም
ዛሬም እንደ ትላንቱ፣ ከቃሉ አልጐደለም
አንቺን እንጂ፣ አሁንም ማንንም አላየም
                             መታሰቢያነቱ ለማን እንደሆነ ለምታውቂው                                      
2002

No comments:

Post a Comment