Friday, January 6, 2017

አትማር ልጄ !



አትማር ልጄ !

ወገን ዘመድ ባይኖር ሀብት ባይኖረኝ ከእጄ
ያንተ መማር ላገር ለዘመዱ ለሁሉ ካልበጄ
ያንተ አስኳላ የሰው ልጅ ከፈጀ
የተከልከው ዕፅ ሳይበቅል ካረጀ

መማርህ ላንተም ለኛ ካልበጄ
ለምን ትማራለህ፣ አትማር ልጄ

ሌቱም ሰላም ነው ፀጥታ የሰፈነበት
ሠርቶ የደከመ አርፎ የሚተኛበት
ዱር አራዊት ግን ግዳይ የሚወጣበት
ከዋክብቱም ሰማይን የሚኩሉበት


እና ያንተ መማር ካረገህ የቀን አውሬ
ድንጋይ ከጣልክብን እንደ እብድ ገመሬ
ዘር ከልጓም ይስባል ሲባል ካልገባህ
የባዕድ ጅኒ ከሰፈረብህ ከጫንቃህ

መማርህ ላንተም ለኛ ካልበጄ
ለምን ትማራለህ፣ አትማር ልጄ

የራስህን ቀዬ የራስህን ታዛ ካልጠቀምክ
ያባትህ ሞፈር እርፍና ቀንበር ካስጠላክ
ከኤረር ማዶ ከሰማይም በላይ ከራማ ከላይኛው ጠፈር
ከባሕር ጥልቀቱ ከምድር ጓዳ ስምጥ ብትመረምር
ዕውቀት ላይኖረው መጨረሻ
ለጉዞህም ወደብ መድረሻ


ላትደርስ ከሆነ የጀመርከው ከወዲያኛው ጥግ
ልትቆነጽል ከሆነ ጥበብን በትንሹ ልትለግግ
የዕውቅተ ፍኖት ያ የሚታይ ከወዲያ
መንገዱ ሰፊ ነው ወለል ያለ ጥርጊያ
በማወቅ ውስጥ ስላለ እያወቁ ማለቅ
ተው ልጄ በልክህ እንደ ራስህ ዕወቅ
መጥነህ ደቁስ መጥነህ አድቅቅ

መማርህ ላንተም ለኛ ካልበጄ
ለምን ትማራለህ፣ አትማር ልጄ

እንዳታሳጣኝ እኔን ጧሪና ቀባሪ
አታዛንቀው ባክህ አላፊን ከኗሪ
ማወቁን ዕወቅ ግን በራስህ ልክ ዕወቅ
የሰው ስታንቧችር የራስህን እንዳትነጠቅ

ላጫውትህ ጨዋታ እንደ ልጅነትህ
የዘርህን ትተህ ደሞ እንዳያንዘረዝርህ
እምዬ ቅሌት ያብሽ ገለባ
ሜዳ ነው ብዬ ገደል ልገባ
እንዳይሆን ነገርህ ልጄ ለራስህ ዕወቅ
አርቀህ ተመልከት ረዥም እንድትዘልቅ

መማርህ ላንተም ለኛ ካልበጄ
ለምን ትማራለህ፣ አትማር ልጄ

ሕፃን እንኳ ባቅሙ እንዲያውቅ እናቱን በጠረኗ
ለአገርም መሆን ይበቃታል አገር መሆኗ
ካልቆምክላት በሸንጎ፣ ባውድ ባደባባይ
ካልሞገትክላት ለሷ በሊቃውንቱ ጉባይ

ስኰናህን ካለመንከው ይቅርብህ መንገዱን አትጀምረው
የሰው ልጅ ዕድሜ እንጂ ዕውቀት መጨረሻ የለው
ዐውቃለሁ ማለት ግብዝነት ነው ባትውቅ ነው የሚሻለው

ዓይንህን ጥለህ በሰው ዓይን ከምታይ
ጎጆህን ጠልተህ ከምትባል ዘበናይ
ዋና ሳታውቅ ከምትገባ ከቀላይ
በሰው አሮፒላ ከምትበር በሰማይ
አደራ ልጄ፣ ራስህን ስታውቅ  
ሌላ ምንም እንዳታውቅ

በቅጡ ሳታውቅ የኛን ትንሹ ሐይቅ
ባሕር ላይ ብትራቀቅ
ማናችንም ላንባጅ
ታንገላታናለህ እንጅ
ታንኳህ ቀዳዳ አለው ብዙም አይዘልቅ
አንተም ከንቱ አትልፋ እኛም አንሳቀቅ
ዕውቀት ቀሊል መስሎህ የጀመርከው ጉዞ
ይቀንጨር ግድየለም ዐጽጾ ይቅር ታርዞ

መማርህ ላንተም ለኛ ካልበጄ
ለምን ትማራለህ፣ አትማር ልጄ

በዕለት መድሃኒዓለም የታህሳሱ፣ በ2009 አዲስ አበባ፣ ዶን ብሩኖ

No comments:

Post a Comment