Thursday, November 17, 2016

የአንድ አበሻ አጭር የሕይወት ታሪክ



የአንድ አበሻ አጭር የሕይወት ታሪክ

ምዕራፍ አንድ፦
ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ ቅዳሜ ቀን
ተፀነሰ ድንገት ሳይታሰብ ሳይወጠን
ወላጆቹ አሉ አንድዬ ነው የሰጠን
በቦታው አልነበረን፣ እኛ ምንም አላየን!!

ምዕራፍ ሁለት፦
ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ አፍለኛ ቀን
ተወለደ እንደ ሰው
ሳይረጋገጥ ማን እንደፈጠረው
ካባት ከናቱ ነው?
ወይስ ከላይ አለ የወረወረው?

ድክ ድክ ብሎ ቆመ
እናም. . .  እናም
አደገ እንደ ምንም ሆዱን እየራበው
ሌት ተቅን ዕንቅልፍ የሚነሳው
ሆድ ሆኖት ባለንጣው
አደገ እንደም ምንም
ማጣት ጣት እያስመሰለው
ከሰው ተራ አውጥቶ፣
እንደ ውሃ ያጣ ተክል እያመነመነው

ምዕራፍ ሦስት፦
ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ የሠመረ ቀን
ሰባ እንደ ሠንጋ፣ ጠረቃ አበጠ
እንደ ደረሰ ማሽላ ሆዱ አገነበጠ
እንደ እመጫት ላም አነጠነጠ
እና ከዚያማ አገርና ወንዙንጂ
ወገንና እትብቱን እንጂ. . .
ሆዱን ከቶ አልረሳም
ተመቸው አማረበት ተባለ
ወፈረ ደለበ አንዳች አከለ
ኋላውን ረሳና ራሱን ወደ ላይ ቆለለ
መሬትን ረሳና አየር ላይ ተዘናጐለ

ምዕራፍ አራት፦
ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ ጎዶሎ ቀን
ድንገት ጤናው ታውኮ ካልጋ ላይ ዋለ
የነካው ሳይታወቅ ሰውነቱ ሰለለ
ታኪም ከጠበሉ ከቃልቻው አልቀረ
ላንድዬ ምህረት፣ ተቀደሰ፣ ተዘየረ
ጤናው እንዲመለስ ብዙ ተሞከረ
ሆንኮንግ ነው ማነው ታይላንድ የሚሉት
ሄደ ምን ያድርግ ‘ንግዲህ ሂድ ሲሉት
ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንደሚሉት
ሆዱ እንደው ጠላቱ ደበቁ ሳይነግሩት

ምዕራፍ አምስት፦
ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ ክፉ ቀን
እንደ ሰው ተወልዶ
በሆድ ተቀይዶ
ሲበላ ኖሮ እንደ አሳማ
ድንገት መሞቱ ተሰማ

እነሆ ይኼ ሰው
አጭር ታሪኩ ረዥም ነው
የታመመ ሆዱን ሳያድን
ሳያሽር ወስፋቱን
ያን የተጣባውን
ጠኔውን ሳይቀብረው
ቀድሞ የቀበረው ጠኔው።

ተዕለታት አንድ ቀን
ከቀናት መካከል
ባንድ ክፉ ቀን
መዳኑ ሳይሰማ፣
መሞቱ ተሰማ . . .


አብረን ነውና ይህችን በቡና ያማጥነው
ብሥራት አጥላባቸው ወሮታው ላንተ ነው
ኖቨምበር 17፥ 2016

No comments:

Post a Comment