መዘዘኛው እረኛ
ያ እረኛ!
በአርያም ምድር . . . በሰዶም ጐመራ
ምስኪን በጐቹን ደፍሮ ያሠማራ
ምሱ ሊተርፍ ደሞ ለእኛ . . . ያ እረኛ!
“ደሞ ማነህ?” ያሉት
ፈጥነው ቀንድ የነከሱት
በስላቅ የጠየቁት
እውነቱ የቅርብ ሩቅ . . . ያ እረኛ!
ንፅሕናው እጥፍ ቢያሳድፋቸው
ድርብ ቢያጐድፋቸው . . . እንደ ከርስ ቢያሸት ቢያገማቸው
ቀይ ዓይናቸውን ቢጠነቁል
ሐቁ ቢደንቁላቸው፣ ቢኮሰኩሳቸው!
መስሎዋቸው . . . የፈታቸው
ክብር ነፍጐ የተፋባቸው
የግልገል በግ ዋጋ እንኳ ያሳጣቸው
ተነሡበት ድንገት፣ ሐቁ እሬት ሆኖባቸው
እናም ከነበጐቹ እንደ ልቡ ላይፈነጭ
ራሱ የጠመቀውን እንዲጐነጭ
ምድር በሞላ ለብሳ እሳት
እረኛው ተደቆሰ በክህደት።
ምድርም ልትበጅ አፉን ላሞጠሞጠ . . . በደሙ ለተጉመጠሞጠ
የሰላሙን ባሕር አብሮ ለናጠ . . . ላናወጠ . .
. ላቀላወጠ
እረኛው ተተፋ በወጀቡ! እጅጉን ተገፋ
ሕልሙ እንደ ዋዛ ብን ብሎ ጠፋ።
ባፍ ይጠፉ እንዲሉ ሆኖበት
ቁልቁል ወረደ! ወረደ ከድጠት!
ቅኔም ዘረፉለት . . . አንድ አዲስ ቅኔ
ግዳይ ጥለው እየጨፈሩ በወኔ
በሐሙስ ምሽቱ ጀብዱ፣ በታላቁ ሴራ
በአርያም ምድር የሞት ብርሃን በራ
ከሳሽም የለባቸው! ደግሞ ለአንድ ተራ እረኛ
ማን ሊሆነው ዋስ ማን ሊቆምለት ጠበቃ
ስንዴው በአርም አውድማ አብሮ ተወቃ።
እነርሱው ገዝተው
እነርሱው ሸጠው
እነርሱው ወግረው
እነርሱው ሰቅለው
የክፋታቸው ክርፋት
የገበናቸው መብዛት
ለእኛም ተርፎ . . . ይኸው በስሙ ቆዳችን ተገፎ
ከበሮ ሊሠሩን ወጠሩን፣ ዝንት ዓለም ሊደልቁን
ዕድሜ ልክ ሊያለፉን! እኛ ጥቁሮቹን. . .
እሱም በጐቹን በትኖ ሔደ!
እኒያ የተኩላ ለምድ የለበሱ በጐቹን
አደራውን ለእኛ ጥሎልን።
ይኸው አለን እስካሁን
እነሱም እኛም ሰላም እንቅልፍ እንደ ራቀን
እንደ ዓሣ እርስ በርስ እየተባላን።
አበጅቶ ፍፁም ላያበጃጃት
ፉንጋዋ ላይ ውበት ላይጨምርላት
ዓለምን እንደ ሕልም ዐለም አድርጓት
ፍፁም ላያስተሰርያት፣ ከበሽታዋ ላያድናት
በሽታ ጨምሮላት፣ ይባስ አሳምሟት
በጐቹን የሰቀሉትነት ለተኩላነት
እኛንም ለዘላለም ባርነት!
ፍቅርን ዘምሮ . . . አስቀረን ባዶ ቤት!
ኦና ቤት!
ከአዝመራችን አምና የገባው ነጭ ዝንጀሮ
አለ ይኸው ዛሬም ዘንድሮ
ያ እረኛ! ያ ጦሰኛ!
በአርያም ምድር . . . በጐመራ
በሰዶም በጐቹን ያሠማራ
ምሱ ለእኛ ተርፎ . . . በስሙ ቆዳችን ተገፎ
ስለ ፍቅር፣ ቤታችን ሆኖ ቀፎ
ይኸው አለን እስተዛሬ
በከበሮነታችን ስንሰዋ ዝማሬ!
1998 እ.አ.አ
No comments:
Post a Comment