Thursday, November 10, 2016

ሥጋና ቸኮሌት



ሥጋና ቸኮሌት
ልገዛ ብዬ ሥጋ፣ ያውም ጠፈፍ ያለ
ፀዳ ብሎ ለስለስ፣ በደንብም ቀላ ያለ
“ሱፐርማርኬት” ከሚሉት የፈረንጅ ገበያ ገብቼ
ከበሬ፣ ከበጉ፣ ከዶሮው፣ ከአሣማው ሥጋ ዐይቼ
ከሞርቶዴላው፣ ከሞዘሬላው ባይነት ባይነቱ
ማቀዝቀዣ ገብቶ ቀዝቅዞ ወጥቶለት ብልቱ

«ቶሎ ገዝታችሁ በልታችሁ፣
ረፍቴን ስጡኝ ባካችሁ
በቁምም በሞቴም
ከንቱ አታስቀሩኝ
ውሻ ከሚበላኝ፣
ገንዳ ከምትጥሉኝ
እናንተው እናንተው፣ አደራችሁ
ጨርሱኝ እንደ ጀምራችሁ! »
ይል ይመስል፣ በሰው ሠራሽ ብርሃን ደምቆ
ለዛውን አጥቶ ክብሩን ሁሉ፣ ከላዩ አወላልቆ
ፍጡር እንዳልነበር ትናንት፣ እንደ ዕቃ ታጭቆ
መላ መላውን ወጥቶ ዛሬ፣ እስታጥንቱ ታርቆ

ሥጋ ቆራጩ እየተንጐማለለ፣ ሲያፏጭ ቢላውን
ሲያቁለጨልጭ፣ አላፊ አግዳሚ፣ ሸማች ተረኛውን
ሊያጠምድ የራበውን፣ የቸኮለ፣ ለሥጋ የሴሰነውን፣

ይኼን ውዳቂ ሥጋ እኔም ልገዛ ዳዳሁና
ጠጋ አልኩ ከመደቡ፣ አንዱን መረጥኩና

ግና ግና ከወዲያ ማዶ፣
ከዚያ ከሌለበት በረዶ
ከመደርደሪያው ላይ
የካካዎን ልጅ፣
ቸኮሌትን ድንገት ባይ
ራሴኑ በራሴ
በቅፅበት ሞገትኩ

ግርማ ሞገሷን ዐይቼ እሷኑ ወደድኩ፣
ዐይቼታም አልቀረሁ፣ እሷኑ መረጥኩ
በምትሃቷ ተስቤ ወደሷ ቀረብኩ

ብትሸጥም፣ ዛሬም እንደትናንቱ
ብትለወጥም ዛሬም ብትሆን ከንቱ፣
ክብሯን አላጣችም አሁንም
በደራው፣ በዚህ በሸቀጡ ዓለም፣

ሻጭ ከገዢ መልሶ የሚያሽሞነሙናት
ሥጋውን አራቁቶ እሷን የሚያልብሳት
የሚያሽሞነሙናት
የሚያቀናጣት
አንዳች ረቂቅ ነገር
አንዳች ምትሃት አላት
11/9/2016

No comments:

Post a Comment