ይቅርታ
ሳናውቅ ላጠፋነው፣
አውቀንም ላጠፋነው፣
ካንደበት ለወጣው፣
ለተነፈስነው፣
ሰውን በኪሱ ለፈረጅነው፣
ዕድሜን በቁጭ ለፈጀነው፣
ጊዜን ገዝግዘን አስገዝግዘን
አላፊ ነው ብለን ለሰየምነው
ቆርጠን ቆራርጠን
ተቀራምተን
በጊዜ ላይ ላለመጥነው፣
በተኛንበት ነግቶ ለመሸብን
ምጽድቅ ለገነነብን፣
የኛነት ኅብር በመላ መላችን
በአካላችን ነግሦብን
ገንዘብ ሃይማኖት ሆኖን
በቀኖናው ለኖርነው
ስሜታችንን ላስገዛነው፣
በእርሱ አልፋና ኦሜጋነት
ስንት በር ተከፍቶ ስንቱ በር ተዘጋ
ያንዱ ክረምት የሌላው በጋ
ስንንሿከክ፣ ስናሿክክ
ስናላክክ፣
በዘመን ላይ ዘመን ሲተካ
አንድ ጭቃ አንድ ወሬ ስናቦካ
ቁምነገር ሳይመረግ . . . ቤቱም
ሳይመረግ፣
የቤታችን መሠረት በጅምር ተናጋ
ልፋታችን ሁሉ አጥቶ ዋጋ
ያቆምነው ዋልታው ዘሞ፣
ጊዜ ጥሎን ሲሄድ ገስግሶ
የኛን ዘመን ብሂል ጥሶ በጣጥሶ
ሕያውነታችን ባክኖ፣
በደኅንነታችን ለታየው ገኖ፣
እንደ አሮጌ ዕቃ የሚጣል የትም
እንደ ሸንኮራ ጊዜን ብንመጠውም
ብንመጠምጠውም
እሱ እኛን እንጂ እኛ እሱን አልጣልንም
የትም ለቀረነው . . . ስማችንን
ሜድ ላይ የጣልነው
ክብራችንን አፈር ያበላነው
ለሥራ መፍታታችን ዋስትና
ለስንፍናችን ዕውቅና
ከትብያ መጣን ወደ ትብያ
ብለን አንድ ላይ ለዘመርነው
አቦ ኃይሉ ጊዜ ይቅር በለን፣
በምህረትህ ደግመህ ጐብኘን
እያየህ ሥቀህ አትለፈን
ሰላም ለነፍሳችን
ለብኩን ሕይወታችን!
ጊዜ ኃይሉ ሰላሙን ስጠን!
በፀፀት አትደቁሰን!
በጨለማ እንደኖረን በጨለማው ውስጥ ተወን
ጊዜ ኃይሉ ባክህ ብርሃን አታሳየን
ራሳችን ጊዜ መሆናችንን አትንገርን።
እንደ ፈረንጆቹ 1997