የልጅ እግር ወታደሮች ምንነት እና አንደምታው
(የዘመናችን ችላ የተባለ ቁጥር አንድ አንገብጋቢ አደጋ)
እንበልና አንተ በዘመናዊ መንገድ የሠለጠንክ ፕሮፌሽናል ወታደር ነህ። ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነህ። አንዱ ልጅህ ዐሥራ ሦስት ሌላኛው ደግሞ ዕድሜያቸው ዐራት ነው።
ከዕለታት ባንዱ ቀን አገርህ የሰጠችህን ግዳጅ ለመወጣት በውጊያ አውድማ ላይ ትገኝተሃል እንበል። በወታደራዊ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 900 ላይ አንድን የጠላት ምሽግ ሰብራችሁ እንደምትገቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷችሁ አንተና የጦር ክፍልህ አሃድ አንድ ላይ በተጠቀሰው ሰዓት ግዴታችሁን ለመወጣት ተንቀሳቅሳችኋል።
በቦታውም እንደደረሳችሁ የእናንተን መምጣትና እንቅስቃሴ የተረዳ ዋርዲያ ቀድሞ ተኩስ ስለከፈተ ከጠላት ምሽግ ወዲያውኑ እናንተን እንዳትንቀሳቀሱ ለማድረግ ብሎም ለመደምሰስ ውጊያው ተጀምሯል። ያው እናንተም የሔዳችሁት አስባችሁበት ልታጠቁ ነበረና በቀላሉ በዝግጅታችሁ መሠረት እርምጃ መውሰድ ትጀምራላችሁ። ውጊያው እናንተ በቂ ዝግጅት አድርጋችሁበት የገባችሁበት ስለነበረ ግማሽ ሰዓትም ያክል አልወሰደም። ጠላት ምሽጉን ጥሎ ሽሽት ጀመረ። ጥቂት እጅ አንሰጥም ያሉ የጠላት ወታደሮች ብቻ አልፎ፣ አልፎ በመታኮስ ላይ ናቸው።
የጦር ክፍልህ አዛዥ ወደፊት በመንቀሳቀስ ምሽጉን እንድትቆጣጠሩ ትዕዛዝ ስለሰጠ በሩጫ ወደ ምሽጉ እየተኮሳችሁ፥ ራሳችሁን እየጠበቃችሁ በመግባት ላይ ናችሁ። ገና ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት እንኳ አልሆነም። ልብ አድርግ። ያንተ ጦር እያሸነፈ ያለ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም እርግጠኛ ግን አይደላችሁም። እየተኮሱ ያሉትን የጠላት ወታደሮች አሊያም መደምሰስ አሊያም ማርኮ ጸጥ ማሰኘት ግድ ይላችኋል።
ወደ ምሽግ ተጠግታችኋል። ድንገት ፊት ለፊትህ ክላሽ የያዘ ሕፃን ቆሟል። ሊተኩስብህ በሚያስችለው አቋም ላይ ነው። ምን ታደርጋለህ? መሣሪያውን ጥሎ እጅ እንዲሰጥ ታደርገዋለህ? ማስጠንቀቂያህን የማይሰማ ከሆነ ትተኩስና ትገለዋለህ? አዘንግቶ ሊያጠቃህ ቁርጠኛ አቋም ያለው ስላለመሆኑስ በምን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
መልሱን እንደ አንድ ፕሮፌሽናል ወታደር ሆኖ፣ ከስሜታዊነት ነጻ በመሆን መልስ መመለስ ያስፈልጋል። በርግጥ ራስን በመከላከል አሳማኝ ፍትሐዊ ምክንያት ልትተኩስና ልትገለው ትችላለህ። ግን የሆነ ደስ የማይል መጥፎ ከባድ ስሜት የዚያ ልጅ ምስል በአእምሮህ ተቀርጾ ለዘላለም አንጎልህን ሲወቅረውና ሲፀፅትህ ሊኖር ይችላል። ልጆችህን ስታይ ያ ልጅ ከፊት ለፊትህ ድቅን ይላል። ለምን ? ለምን ? መልሱን ሁልጊዜ ማወቅ ትፈልጋለህ? አታገኝም። ወይም በቃ የሰው ልጅ ጨካኝ ከንቱ ነው ብለህ ራስህን ለማባበል ትሞክራለህ? ግን ራስህን መዋሸት አትችልም እስከ ዕለተ ሞትህ ሲቆጠቁጥህ ይኖራል።
ሌላ ምሳሌ ደግሞ እናንሣ። የምትወደው የዐሥራ ሦስት ዓመት ልጅህ ወይም የምትወዳት የዐሥራ አምስት ዓመት ልጅህ ድንገት ከቤት ጠፍቶ ወይም ጠፍታ ከመንግሥት ተቃራኒ በሚፋለም ኃይል ወይም በሌላ አገር ውስጥ በሚገኝ እንደ ዳአይሽ ወይም አልቃይዳ የመሰለ ቡድንን ለማገልገል መሰለፉን ወይም መሰለፏን አረጋገጥክ? ልጅህ ከነዚህ ቡድኖችን ጋር ግንኙነት እንደነበረው ምንም የምታወቀው ነገር የለም፥ ምንም ዓይነት ፍንጭም አልነበረህም። እንዴት ሊገናኝ እንደቻለም አታውቅም፥ ልትገምትም አትችልም። ግን ሆኗል። ማመንም አቅቶሃል። እንዴት ይኼ ሊሆን ይችላል?
ይህ ጽሑፍ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች መንስዔያቸውን እና መከላከያ መፍትሔያቸውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይሞክራል። በነገራችን ላይ ጽሑፉ ከግንዛቤ ማስጨበጫነት ባሻገር ማንንም ወገን ትክክል ማንንም ወገን ደግሞ እንደ አጥፊ ወንጀለኛ አድርጎ የመፈረጅ ዓላማ እንደሌለው ከወዲሁ ልብ እንዲባል ማሳሰብ እወዳለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ መካከል ግንዛቤ በመፍጠር ለታዳጊ ወጣቶች እና ሕፃናት አስፈላጊው ጥንቃቄና ክብካቤ እንዲሰጣቸው እንዲሁም ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማድረግ ማስቻል ነው።
የችግሩ ስፋት እና አስፈሪነት
·
ሕፃናት እርሳስ እና እስኪብርቶ መያዝ በሚገባቸው እጆች እጅግ አጥፊ የሆኑ አውዳሚ የጦር
መሣሪያዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱባቸው በርካታ የዓለማችን አገሮች በአሁኑ ጊዜ እየተበራከቱ በመሔድ ላይ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም
ገና በአፍላ ዕድሜያቸው ሰውን መግደል እንዲለማመዱ እና በግድያ እንዲሠለጥኑ ያደረጋሉ። በሥልጠናው ወቅት ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን
በመግደል ለመልማይ አለቆቻቸውና የጦር አዛዦች ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩ የሚገደዱባቸው ሁኔታዎችም አሉ።
·
በዓለም ላይ በአሁኑ ጊዜ በቀጥታ ነፍጥ አንግተው በውትድርና የሚያገለግሉ በግምት ወደ 300,000 የሚደርሱ
ሕፃናት ይገኛሉ። ይህ ቁጥር በየዓመቱ አስፈሪ በሚባል ደረጃ እያደገ ያለ ከመሆኑ ባሻገር ብዙዎች እንደ የድኃ አገሮች ችግር ከማየት በዘለለ የሠለጠኑ አገሮች ችግርም እንደሆነ ማመን ጀምረዋል። በየዓመቱ ከተቀማጠለ እና ይህ ቀረሽ ከማይባል የአውሮፓና የአሜሪካ ኑሮ ራሳቸውን በማፈናቀል በርካታ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሽብር ፈጣሪ በመባል የተፈረጁ ድርጅቶችን በገዛ ፍቃዳቸው ይቀላቀላሉ።
·
በተዘዋዋሪ መንገድ በውትድርና እያገለገሉ ያሉት ሕፃናት ቁጥርን መገመት ባይቻልም በሚሊዮኖች የሚቆጠር አስፈሪ አሃዝን ለመስጠቱ ግን ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ከዚህ ጎን ለጎን ከአንድ ዓመት በፊት በ2007 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ቁጥራቸው ከ240 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሕፃናት በዓለም ዙሪያ በጦርነት በተጎዱ አገሮች
ውስጥ እንደሚኖሩ ተረጋግጧል። ከእነዚህ ሕፃናት መካከል በርካታዎች ለዐመፅ፣ ለኃይል ጥቃት፣ ለመፈናቀል፣ ለረሃብ እና በታጠቁ ኃይሎች
እና ቡድኖች ለሚደረግ የጉልበት ብዝበዛና ሌላም ሌላ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው።
·
ኤኬ 47ን የመሳሰሉ ጅምላ ጨራሽ አውቶማቲክ መሣሪያዎች ዩጋንዳ ውስጥ አንድ ዶሮ መግዛት በሚያስችል የገንዘብ መጠን ወይም ሞዛምቢክ ውስጥ ካንድ ጆንያ በቆሎ ዋጋ ባልበለጠ ዋጋ መግዛት ይቻላል። የዐዋቂ ሰዎችን ጦርነት እንዲያዋጉ ለማድረግ ሕፃናትን ለውትድርና መመልመል እና መሣሪያ ማስታጠቅ የአፍሪካ እና የአፍሪካውያን ችግር ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ችግር ሆኗል። ችግሩ በተለይ በአፍሪካ እና በኤዥያ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል።
·
አብዛኛዎቹ ልጅ እግር ወታደሮች ለመንግሥታት ሳይሆን ለዓማፂ ኃይሎች የሚያገለግሉ በመሆናቸውና
እነዚህ ዓማፂ ኃይሎች ደግሞ በአብዛኛው ዓለም አቀፍ የውጊያ ሥነ ምግባር ሕጎችን እና ሌሎች ስምምነቶችን ስለማይቀበሉ እና ስለሚጥሱ
ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
·
በአፍሪካ ያሉት የልጅ እግር ወታደሮች ብዛት በቀጣይነት እያሻቀበ በመሔድ ላይ በመሆኑ የልጅ
እግር ወታደሮችን ቁጥር ይኼ ነው ብሎ ለመገመት አዳጋች ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ሕፃናትን ለወታደር የሚመለምለው ወገን ማንም እንደፈለገ
መጥቶ መዝገቦችን አገላብጦ ሊያረጋግጥ የሚችልበትን የሰው ኃይል አደረጃጀት ሥርዓት ስለማይከተል እንዲያው በደፈናው ከሩቅ ሆኖ ከመገመት
ውጭ ማንም በዓማፂያን መካከል ገብቶ ቆጠራ ለማከናወን የሚችልበት ምቹ ሁኔታ የለም። በመሆኑም የልጅ እግር ወታደሮች ምልመላና ጥቅም
ላይ ማዋል ሂደት ከፍተኛ ምሥጢራዊነት የተላበሰ የዘመናችን ዘመናዊ ባርነት ዓይነት ነው ማለት ይቻላል።
·
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በዓለም ዙሪያ ትምህርት ዕድል ተነፍገው ለረዥም ሰዓታት እዚህ
ግባ በማይባል ክፍያ ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ በመደረግ ላይ መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ይህም ሕፃናቱ ነጻነትን ፍለጋ
ወደ ታጠቁ ኃይሎች ዓይናቸው እንዲያማትር ወይም በቀላሉ ተታለው ሊመለመሉ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
·
ልጅ እግር ወታደሮች ድፍረት እንዲያገኙ በሚል እና የቀለብ ወጪያቸውን ለመቀነስ ሲባል እንደ
ሲጋራ፣ አልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ ዕፅ ለመሳሰሉ ነገሮች እንዲጋለጡና እንዲጠቀሙ ስለሚደረጉ ከውትድርናው እንዲወጡ ሲደረጉ አብረው
ይዘዋቸው የመጡዋቸውንድ ደባል ሱሶች ለማላቀቅ ከፍተኛ ጥረትና እልህ አስጨራሽ ብሎም ተስፋ አስቆራጭ ትግልን ማድረግን ይጠይቃል።
·
ልጅ እግር ወታደር ሆነው ሕፃናት ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች በኋላ ላይ በሕግ ቢጠየቁ እንኳ
ለአካለ መጠን ባልደረሱ ሕፃናት የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ወንጀላቸው ስለሚታይ የሚጣልባቸው ቅጣት ቀላል ከመሆኑም በላይ በሌሎች በሌላ
ቀላል ወንጀል የታሰሩ ሕፃናት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ገና ብዙ ምርምር እና ጥናት የሚያሻው አደገኛ ስለመሆኑ ከወዲሁ
ሊገመት የሚችል ችግር ነው።
·
ልጅ እግር ወታደሮች ለውትድርና በሚመለመሉበት ጊዜ ጤናቸው እና ጤናማ አካላዊ ዕድገታቸው
በተለያዩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዋዊ ምክንያቶች ይዛባል። በጦርነት ጊዜ ለአካለ መጠን ከደረሱ ተዋጊዎች ይልቅ ልጅ እግር ወታደሮች
ይበልጥ ለአካል ጉዳት በተለያዩ ምክንያቶች ይጋለጣሉ። በቀላሉም ሊገደሉ ይችላሉ። ከዚህ ጎን ለጎን የሚደርሳባቸው ሥነ ልቦናዊ ቀውስ
በቀላል የሚታይ አይደለም። በግድያ ላይ መሳተፍ፣ ወይም ሰው ሲገደል መመልከት በልጅ አእምሮ ላይ የሚፈጥረ ጥቁር ነጥብ በቀላሉ
የሚሽርና ሊወገድ የሚችል አይሆንም። ለውትድርና ብላ ከታጣቂ ኃይሎች ዘንድ ወዳም ሆነ ሳትወድ የተመለመለች ልጃገረድ ስትደፈር እና
ያለውዴታዋ የጦር አበጋዞች ሚስት ስትሆን የሚደርስባት ሥነ ልቦናዊ ቀውስ በኋላ ላይም ከማትፈልጋቸው ወይም ማንነታቸውን ከማታውቃቸው
ሰዎች ልጆችን ፀንሳ ስታሳድግ የሚደርስባት የሕሊና ጉዳት በቃላት ሊገለፅ የሚችል አይደለም።
ልጅ እግር ወታደር ወይም Child Soldier
ምን ማለት ነው?
በዚህ ጽሑፍ ላይ “ሕፃን ወታደር”፣ “ብላቴና ወታደር”፣ “ማንጁስ” ወይም “ልጅ ወታደር” ከማለት ይልቅ “ልጅ እግር ወታደር” ማለቱን ከብዙ ምክንያቶች አንጻር ተመርጧል። ሕፃን ወታደር ወይም ሌሎቹ አገላለጾች child soldier
ከሚለው የእንግሊዝኛ ፅንሰ ሐሳብ አኳያ ሲታይ ሕፃናቱን በቀጥታ ምንም የማያውቁ፥ የዋሆች፥ እና ተበዳዮች አድርጎ የማየት አዝማሚያን ወይም አንደምታን ሊፈጥር ይችላል። ሆኖም ግን ሕፃናቱ ምንም እንኳ እንደ አንድ ለአካለ መጠን የደረሰ በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበት አካላዊና አእምሯዊ ብቃት ደረጃ ላይ ባይገኙም የታጠቁት መሣሪያ የሰውን ልጅ ሊቀጥፍ ይችላልና የዋህነት ደረጃቸው በከፍተኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ የስጋት ምንጭነት ያሸጋግራቸዋል።
ሕፃናትን እንደ ወታደር መጠቀም ስለመቻሉ እና ይህም አግባባ ስላለመሆኑ ለማስገንዘብ ለዘመናት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት አግኝቶ ችግሩ የዓለም መሪዎች የተወያዩት እና ከመፍትሔ ሐሳብ ላይ የደረሱት የዛሬ ዐሥራ አንድ ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2007፣ በፓሪስ ከተማ ፈረንሳይ ውስጥ በተደረገ ስብስባ ነው። በዚህም ስብሰባ ላይ የፓሪሱ መርሆዎች በመባል የሚታወቀው ግዢ ድንጋጌ ሊበየን እና መንግሥታትም ሆነ የተለያዩ በጦር አውድማ ውስጥ በመሳተፍ ላይ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ይህን ብያኔ እንዲያከበሩ፥ ሳያከብሩ ሲገኙም በጦር ወንጀለኝነት እንዲጠየቁ ውሳኔ ተወስኗል።
የፓሪስ መርሆዎች 2007 በመባል የሚታወቀው ልጅ እግር ወታደር ወይም Child Soldierን እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፦
ማናቸውም ጦር ከታጠቁ ኃይሎች ወይም ቡድኖች ጋር የተቆራኘ ወይም ግንኙነት ያለው ልጅ እንደ ልጅ እግር ወታደር ይቆጠራል። ልጅ እግር ወታደር ስንል ማናቸውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ በታጠቁ ኃይሎች ወይም ቡድኖች በማናቸውም አቅም ኃይሉን እንዲያገለግል የተመለመለ ሕፃን ማለታችን ሲሆን ይህን ስንል ሕፃናቱ የሚሰጡት አገልግሎት እንደ ተዋጊ፣ እንደ ምግብ አብሳይ፣ እንደ የጽዳት ሠራተኛ፣ እንደ ኩሊ (ተሸካሚ)፣ እንደ ተላላኪ፣ እንደ ሰላይ ወይም እንደ ወሲብ መሣሪያ ሊገለፅ የሚችል ቢሆንም በነዚህ ብቻ የተገደበ ግን አገልግሎቱ ያልተገደበ ሊሆን ይችላል።
የእንግሊዝኛው ብያኔ የሚከተለው ነው፦
A child solider is a
child associated with an armed force or armed group. A child solider refers to any person below 18
years of age who is or who has been recruited or used by an armed force or armed
group in any capacity, including but not limited to children, boys and girls,
used as fighters, cooks, porters, messengers, spies, or for sexual purposes. It
does not only refer to a child who is taking or has taken a direct part in
hostilities.
Paris Principles,
2007
ይቀጥላል . . .
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ነሐሴ 21
No comments:
Post a Comment