የልጅ እግር ወታደሮች ምንነት እና አንደምታው (ክፍል ሦስት)
(የዘመናችን ችላ የተባለ ቁጥር አንድ አንገብጋቢ አደጋ)
የልጅ ወታደሮች ጠቀሜታ
ትክክለኛ ውጊያ በማይካሔድበት ጊዜ ሕፃናት በፍተሻ ኬላዎች ላይ እንደ ጠባቂ ሆነው በመመደብ ያገለግላሉ። በዚህም ትክክለኛ ወታደሮች ከፍተሻ ኬላው ራቅ ብለው ስለሚሰፍሩ አንዳች ጥቃት ቢመጣ በመጀመሪያ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑት በጥበቃ ኬላዎቹ ላይ የተቀመጡት ሕፃናት ይሆናሉ። አንድ ጊዜ ከተመለመሉ በኋላ ልጅ እግር ወታደሮች ከላይ እንደ ተጠቀሰው በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ተሠማርተው መልማዩን ቡድን ያገለግላሉ። አብዛኛዎቹ ልጅ እግር ወታደሮች ተሸካሚዎች ወይም ምግብ አብሳዮች፣ ዘበኞች፣ መልእክት ተላላኪዎች ወይም ሰላዮች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በርካታ ሕፃናት በቀጥታ በጦር አውዳማ ውስጥ ገብተው በተዋጊነት እንዲሳተፉም ይገደዳሉ። ዕድሜያቸው ትላልቅ ለሆኑት ወታደሮች እንደ ጥይት ማብረጃ ከለላ ጋሻ ወይም እንደ ፈንጅ ማምከኛ በመሆንም እንዲያገለግሉ ይደረጋሉ። አንዳንድ ሕፃናት ለአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበረም እና እየዋሉ እንዳሉም እዚህ ላይ ማስታወስ ግድ ይለናል።
ልጅ እግር ወታደሮች በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በ 14 አገሮች ውስጥ እየተዋጉ እንዳሉ ይታመናል። ከነዚህም አገሮች መካከል በዋንኛነት ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ሊቢያ፣
ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፣ ኮሎምቢያ፣ ማይንማር፣ ፊሊፒንስ፣ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ኢራቅ፣ ታይላንድ፣ የመን፣ እና ሶሪያ ይገኙባቸዋል።
ሴት ልጅ ወታደሮችና ልዩ ጠቀሜታቸው
ሴት ልጃገረድ ወታደሮች ብዙውን ጊዜ እንደ ዐዋቂ ወታደሮቹ “ሚስቶች” እና የወሲብ ፍላጎት ማርኪያ ፍጡራን ሆነው ያገለግላሉ። እንደ ሁዩማን ራይትስ ዋች ዘገባ ከሆነ ሴት ልጃገረድ ወታደሮች ባሉበት የጦር ሠራዊት አዛዦች እንዲያረግዙ ከመገደዳቸው ባሻገር የወለዱዋቸውን ልጆች በጀርባቸው አዝለው በጦር ሜዳ ላይ በውጊያ በቀጥታ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ። እንደ ኔፓል፣ ስሪ ላንካ፣ እና ዩጋንዳ በመሳሰሉ አንዳንድ አገሮች አንድ ሦስተኛ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ልጅ እግር ወታደሮች ሴት ልጃገረዶች እንደሆኑ ሪፖርት ተደርጓል። በአንዳንድ ግጭቶች ላይ ሴት ልጃገረዶች ተገደው ሊደፈሩ፣ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው በቀጥታ ለጦሪ አዛዥ በሚስትነት በቀጥታ ሊታጩ ወይም እንደ ገጸ በረከት ሊሰጡ ይችላሉ።
ልጅ ወታደሮችን መልሶ ማቋቋም
ልጅ እግር ወታደሮች ከውትድርና ዕድል አግኝተው ከተሰናበቱ በጦርነት ጊዜ ምግብ እና መጠለያ በወታደር መሪዎቻቸው ይቀርብላቸው የነበሩ እንደመሆናቸው መሠረታዊ የኑሮ ክኅሎቶችን ባለማወቃቸው፣ ራሳቸውን ችለው ለመኖር ይቸገራሉ። ይህም ነጻ ከሆኑ በኋላ እንኳ ከሌላው ኅብረተሰብ መካከል ገብቶ በሰላም ለመኖር የመቻላቸውን ዕድል እጅግ ጠባብ ያደርገዋል። በአንዳንድ አገሮች የቀድሞ ልጅ እግር ወታደሮች ለመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮግራሞች የታደሉ ሲሆኑ በእነዚህ ፕሮግራሞች አማካኝነት ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ መልሰው ፈልገው ለማግኘትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል፣ ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ፣ ሙያ ሥልጠና ማግኘት፣ እና ሰላማዊ የሲቪል ሕይወትን እንደገና ሀ ብለው ለመጀመር ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል። ሆኖም ይህ እንቅስቃሴ ያን ያክል በጉልህ የሚታይ ባለመሆኑ ካለው ፍላጎት አንጻር ሲታይ ጥረቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ልጅ እግር ወታደሮች ከውትድርና ሲሰናበቱ ሙሉ በሙሉ ከባድ ፈተና ውስጥ ይገባሉ። ከኅብረተሰቡ ጋር መልሰው እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ የሚደረግላቸው ድጋፍ አሊያም በቂ አይደለም ወይም ከናካቴው ምንም ድጋፍ አያገኙም። በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው የተሃድሶ ድጋፍ እጥረት ወይም የመልሶ ማቋቋሙ ሥራ ድክመት ካለ እነዚያ ከውትድርና የተሰናበቱት ወይም በተለያየ መንገድ ነጻ የወጡት ሕፃናት መልሰው የልጅ እግር ወታደሮች የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
የልጅ እግር ወታደሮችን ምልመላ እና ጥቅም ላይ ማዋል ለማስቀረት የተወሰዱ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ እርምጃዎች
የልጅ እግር ወታደሮች ሕጎች ድህረ ታሪክ
ስለ ልጅ እግር ወታደሮች ወይም በፈረንጅ አፍ “Child Soldiers” ስለሚባሉት ስናስብ አእምሮዋችን ላይ የሚመጣልን ካቅሙ በላይ የሆነ የወታደር ልብስ የለበሰና ቁመቱ ከራሱ ቁመት የበለጠ ኤኬ 47 የታጠቀ አፍሪካዊ ልጅ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ወታደራዊ ሥልጠና እየተሰጣቸው ያሉ አፍጋኒስታናዊ ሕፃናትንም ተመልክተን ሊሆን ይችላል። ሌላም ፣ ሌላም ዘግናኝ ተግባራትን ልጅ እግር ወታደሮች ሲፈጽሙ ዐይተን እናውቅ ይሆናል። እንዴት እነዚህ አንድ ፍሬ ልጆች ያንን አውቶማቲክ መሣሪያ መጠቀም እንደሚችሉ ስናስበው ግራ ግብት ይለናል። ምክንያቱም ልጆቹ እንኳን ያን መሣሪያ እንደ ልባቸው ሊጠቀሙበት ቀርቶ በአግባቡ እንኳ ልብሳቸውን ራሳቸውን ችለው መልበስ መቻላቸው ያጠራጥራል። ይህ ብቻ አይደለም መሣሪያውን መጠቀም አለመጠቀማቸው ሳይሆን በዓለም ላይ ዘግናኝ በሚባሉ ዐውድ ውጊያዎች ላይ መሳተፋቸውን ስንረዳ በዚያ ጦር ሜዳ የሚፈጠረውን ነገር ሁሉ ስናስበው ሊያመን፣ በተለይ ልጅ ያለን ወላጆች ከሆንን አደ ላይ ሊለን እና የበላነው ሊጣላን ይችላል።
ልጅ እግር ወታደሮች የሰው ልጅ ታሪክ በጦርነት መጻፍ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እስከዚች ደቂቃ ድረስ በጦርነት ውስጥ ሲሳተፉ እንደነበሩ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በወንጀል የማያስጠይቅ ጎጂ ባሕል እንደነበረ ፥ አሁንም ድረስ ደግሞ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ልጅ እግር ወታደሮች ለተለያየ ዓላማ በማገልገል ላይ መሆናቸውን ስናውቅ ይበልጥ ሊያመን ይችላል።
የአነስተኛ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር፣ ትዕዛዝን ለመቀበልና ለመታዘዝ ሕፃናት ያላቸው የማያጠራጥር ብቃትና ውጤታማነት፣ ድህነት፣ የተለያዩ የሐሳብ ፍልስፍናዎች እና የበላይነትን የማግኘት ዘመቻዎች (አይዶዮሎጂ) እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ነፍስ ወከፍ ፕሮፓጋንዳ ሕፃናትን እንደ ወታደሮች ለመጠቀም ችግር የየራሱን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ “የልጅ እግር ወታደር ችግር” እንደ ችግር መታየት የጀመረው በጣም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።
የሮማ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ መቅጫ ፍርድ ቤት ሕግ ወይም Rome Statute
of the International Criminal Court (2002) የሚባለው ሕግ ሕፃናትን እንደ ልጅ እግር ወታደር መመልመል
በወንጀል የሚያስጠይቅ የጦር ወንጀል መሆኑን ይደነግጋል።
በስተመጨረሻም ልጅ እግር ወታደር ወይም Child Soldier ምን ማለት ነው? በሚለው
አርእስት ሥር ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው “child soldier” የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ ብያኔ ከመስጠት
ባሻገር ሕፃናትን እንደ ወታደር በተለያየ መንገድ መጠቀም ስለመቻሉ እ.አ.አ በ2007፣ በፓሪስ ከተማ ፈረንሳይ ውስጥ በተደረገ
ስብስባ ተብራርቷል። በዚህም ስብሰባ የፓሪስ መርሆዎች 2007 በመባል ይታወቃል።
የአዲስ ዘመን አዲስ እሳቤ
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከዛሬ ዐርባና አምሳ ዓመት በፊት ሕፃናትን ለውትድርና
ሥራዎች መገልገል በምንም ዓይነት መልኩ የሚወገዝ ተግባር አልነበረም። በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው ጦርነት በተለያዩ ደረጃዎች በርካታ
ሕፃናት በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል። ሆኖም ግን ድንገት ዓለም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ግን ዓለም ይህን የልጅ እግር
ወታደሮች በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆንን ማውገዝ ጀመረ። ለምን ይህ ውግዘት መጣ? ችግሩ ምንድን ነው? በርግጥ ሕፃናትን ለውትድርና
መጠቀም አንደምታው አስከፊ ማኅበራዊ ቀውስን የሚያስከትል ነውን?
እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት፣ “ሕፃን” የሚለው ቃል በዓለም ዙሪያ፣ በተለያዩ አገሮች እና በተለያዩ ባሕሎች ውስጥ ምን ዓይነት ትርጓሜ በተለያየ ጊዜ ይሰጠው እንደነበረ መመልከት በራሱ ምን ያክል ይህ ቃል አወዛጋቢ ቃል እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል።
ሕፃናትን በቀጥታ በጦርነት ውስጥ እንደ ተዋጊ ለማሳተፍ የሚያስችለው ዝቅተኛ የዕድሜ ጣሪያ 15 ሆኖ የተቀመጠው በ1949ኙ የጄኔቫ ስምምነት (1949 Geneva Conventions) ሲሆን ይኸው ስምምነት መልሶ በ1977 ከተጨማሪ ፕሮቶኮሎች ጋር እንዲፀድቅ ተደርጓል። እነዚህ ተጨማሪ ፕሮቶኮሎች በመጀመሪያው ስምምነት ላይ የጨመሩት ነገር ቢኖር ”በቀጥታ መሳተፍ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማብራሪያ መስጠት እና ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ለውትድርና እንይመለመሉ የሚከለክሉ የሕግ አንቀጾችን መጨመር ነበር። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ትምህርት ፈንድ ወይም ዩኒሴፍ (UNICEF) እና የተባበሩት መንግሥታት (UN) ግንዛቤ ከሆነ ሕፃናትን እንደ ወታደር ላለመጠቀም ዘመቻውን የተጀመረው በግራሺያ ማሼል በ1996 ባቀረቡት “ጦርነት በሕፃናት ላይ የሚያስከትለው ጫና” (The Impact of Armed Conflict on Children) በሚለው ሪፖርታቸው አማካይነት ነው። በዚህ ሪፖርታቸው ላይ ወይዘሮ ግራሺያ ምን ያክል ጦርነት ሕፃናትን ከሌሎች የሰው ልጆች በበለጠ ክፉኛ ጉዳት እንደሚያደርሱባቸው እና ሕፃናት የጦርነት ዋንኛ ሰለባዎች እንደሆኑ አፅዕኖት ሰጥተው ሐተታ ከነማስረጃው አቅርበዋል።
በ1967 ሎሬን ሺኔደር የተባለች የዐራት ልጆች እናት እና የሕትመት ባለሙያ የበኩር ልጇ ወደ ጦር ሠራዊት ሊመለመል ይችላል ከሚል ፍርቻ በቬትናም ጦርነት ዘመን ብዙ ሰው ያያቸውን እና አነጋጋሪ የነበሩትን የማስጠንቀቂያ ደውል የሆኑ ፖስተሮችን ፈጥራ አሠራጨች። እነዚህ ፖስተሮች ላይ ያለው ሥዕል “ጦርነት ለሕፃናት እና ለሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ጤና ጥሩ አይደለም” የሚል መልእክትን የያዙ ፖስተሮች ነበሩ። ይህ ሥዕል እንደ ፀረ-ጦርነት ቅስቀሳዎች ማራመጃ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው ባሻገር በዩናይትድ ስቴትስ ደረጃ ከፍተኛ ድጋፍን አስገኝተው ነበር። ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በኋላ በ1989፣ የ1989ኙ የሕፃናት መብት ስምምነት (Convention on the Rights of the Child of 1989) በ15 ዓመት ዕድሜ ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ ወደ 18 ከፍ ያደረገው ቢሆንም አሜሪካን እና እንግሊዝን ጨምሮ የዓለም ኃያላን አገሮች ይህንን ስምምነት እንዲቃወሙት አድርጓቸዋል።
የግራሺያ ሪፖርት በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ሕፃናት ጉዳይን ወደ መደበኛ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና ቅድሚያ ተሰጪ የተባበሩት መንግሥታት ፕሮግራሞች ውስጥ እንዲካተት የሚያስችል ግፊትን ፈጥሯል። የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ድርጅት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች፣ ኢንተርናሽናል ሴቭ ዘ ችልድረን አሊያንስ፣ ጀስዊት ረፊዩጂ አገልግሎት፣ ኳከር ዩኤን ኦፌስ እና ቴር ዴስ ኦም ጋር በመተባበር ሕፃናት ለውትድርና ሊመለመሉ የሚችሉበት ዝቅተኛ ዕድሜ 18 ዓመት እንዲሆን በጋራ ቅንጅት በመፍጠር የተለያዩ የድጋፍ ማግኛ ዘመቻዎችን በጋራ አከናውነዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ የጋራ መድረክን የፈጠረው ቅንጅት ለቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ተሳትፎ (ቀጥተኛ ያልሆነ)፣ የአገር ውስጥ እና በአገሮች መካከል ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጦርነቶች፣ እና ተቀባይነት ስላላቸው የምልመላ አሠራሮች ሁሉም ሊያከብራቸው የሚገቡ መመሪያዎችን አስቀምጧል።
ሙሉ በሙሉ ዐሥራ ስምንት ላይ የተቀመጠው ገደብ (A Straight-18
standard)
ሕፃናትን እንደ ወታደሮች መጠቀምን ለማስቆም ከላይ በተጠቀሱት ድርጅቶች የተቋቋመው ቅንጅት ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ያገኝ ዘንድ ጠንክሮ ያለማሰለስ ሲሠራ ቆይቷል። ዲፕሎማቶችን፣ መያድ እንቅስቃሴዎችና ንቅናቄዎችን፣ ሰፊውን ሕዝብ ዒላማ ያደረገ አነስተኛ መጽሐፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሆኖ እንዲያገለግል አዘጋጅቷል። በዚሁ አነስተኛ መጽሐፍ ላይም የልጅ እግር ወታደሮችን ችግር መጠነ ስፋትና ምንነት፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ በሕፃናት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖዎቹ እንዲሁም አሁን ያሉት ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ያሉባቸውን ሕጸጽ እና ድክመት አፅዕኖት ሰጥቶ ለሚመለከተው ወገን ሁሉ ምክሩን ሰጥቷል። ከዚህም ባሻገር፣ ቅንጅቱ ክልላዊ ድርጅቶች እርስ በርስ መልእክት ሊለዋወጡ የሚችሉበትን እና ክልላዊ አውታረ መረቦችን መፍጠር የሚችሉባቸውን በርካታ ክልላዊ ኮንፈረንሶችን አዘጋጅቶ አስተናግዷል።
ይህም ብቻ አይደለም ሙሉ በሙሉ ዐሥራ ስምንት ዕድሜ ላይ ብቻ የተቀመጠ ገደብ /A Straight-18 standard/
ወጣቶችን ለውትድርና ለመመልመል ዝቅተኛው የዕድሜ ጣሪያ እንዲሆን ተወስኖ በዓለም ዙሪያ እየተተገበረ ይገኛል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት በጦር አውድማዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሕፃናት ስላላቸው የሕፃናት መብት በተመለከተ የተደረገ ስምምነት አማራጭ ፕሮቶኮል /Optional Protocol to
the Convention on the Rights of the Child on the involvement of Children in
Armed Conflict/ ወይም OPAC በመባል የሚባለውን ሕግ ይፍፋ አድርጓል። ፕሮቶኮሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በግድ መመልመልን ከመከልከል ባሻገር በጦር አውድማ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ ማድረግን እንደ ወንጀል በመቁጠር ያግዳል። እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ ይህ ስምምነት በ167 አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ የስምምነት ፊርማቸውን አኑረውበት ፀድቋል።
የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት ወይም
/International Labor Organisation/ ያወጣው የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የመጨረሻዎቹ አስቀያሚ ዓይነቶች ስምምነት በሚለው ሰነዱ ላይ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በግድ ወይም በግዳጅ መመልመልን ይከለክላል። ይህን የስምምነት ሰነድ ከ150
በላይ አገሮች ተቀብለው በፊርማቸው አፅድቀውታል።
(ይቀጥላል)
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ነሐሴ 21 ፥ 2018 (በራስ አቆጣጠር)
No comments:
Post a Comment