Monday, August 27, 2018

የልጅ እግር ወታደሮች ምንነት እና አንደምታው (ክፍል ዐራትና መጨረሻው)

የልጅ እግር ወታደሮች ምንነት እና አንደምታው (ክፍል ዐራት)
(የዘመናችን ችላ የተባለ ቁጥር አንድ አንገብጋቢ አደጋ)
የልጅ እግር ወታደር መኖር መገለጫዎችና ተሳትፎ
ልጅ እግር ወታደሮች ብዙውን ጊዜ በታጠቁ ቡድኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ። በመሆኑም ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ ከባድ እና ሥር የሰደዱ ሥነ ልቦናዊ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ምግባራዊ ግራ መጋባቶችን በግዳጅ ቦታ ላይ ላሉ ፕሮፌሽናል ሠራተኞች ሊፈጥር ይችላል። በታክቲክ ደረጃ ሲታይ ልጅ እግር ወታደሮች በማናቸውም ሰዓትና ደቂቃ በግዳጅ ላይ ላለው ፕሮፌሽናል ሠራተኛ ሕይወቱን ሊያሳጣው የሚችልን አደጋ ሊጥሉ ወይም አደጋ ሊያስከትሉበት የሚችሉበት አቅም አላቸው። በሕፃናት ላይ የሚወሰድ እርምጃ የዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ደንቦችን እንዲሁም ወደ ግዳጅ ያሠማራው ኃይል በሚሰጠው መመሪያ መሠረት በጥንቃቄ መከናወን ይኖርበታል።
ስድስቱ በጦርነት ጊዜ በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ዘግናኝ ወንጀሎች
1.      ሕፃናትን ለውትድርና አገልግሎት መመልመል እና መጠቀም
2.      ሕፃናትን መግደል ወይም አካለ ጎደሎ ማድረግ
3.      ሕፃናትን ወሲብ ለመጠቀም
4.      ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ላይ ጥቃት መፈጸም
5.      የሕፃናት ጠለፋ
6.      ሰብአዊ እርዳታ ለሚሰጡ ወገኖች መዳረሻን መከልከል
ማጠቃለያና መፍትሔ ሐሳቦች
በግዳጅ ጊዜ የፕሮፌሽናል ወታደር የሥነ ምግባር መመሪያ
ልጅ እግር ወታደሮች ሊኖርበት የሚችሉ የጠላት ጦርን ለመደምሰስ እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ በተቻለ መጠን በጠላት ጦር ውስጥ ያለውን ዐዋቂ መሪ አዋጊ ሰው ላይ ዒላማ ማነጣጠር ያስፈልጋል። አመራሩ እንዲወገድ ማድረግ ብዙውን ጊዜ ሕፃናት እጃቸውን እንዲሰጡ እና ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስችልን ዕድል ይፈጥራል። ከዚህ ውጭ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ማለት ይገባል፦
1.      ግዳጅህን በጥንቃቄ እና ያለ ምንም አድልዎ በሕግ አግባብ ተወጣ
2.      ግዳጅህን ለመወጣት ከሚያስፈልገው በላይ ምንም ዓይነት ኃይልን አትጠቀም፤ ስትጠቀምም ለመጠቀም የሚያስችልህን የበላይ ትዕዛዝ ማግኘትህን እርግጠኛ መሆን መቻል አለብህ
3.      በማናቸውም ጊዜ በጨዋነት እና የሰው ልጅን አክባሪ በሆነ አገባብ ተንቀሳቀስ። ሁሉንም ሰው በዘር፣ በብሔር፣ በጎሣ፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በዕድሜ፣ በአካል እና የአእምሮ ጉዳት ሳታዳላ፣ በእኩልነት አስተናግድ
4.      ለንብረት አስፈላጊውን ክብር ስጥ
5.      የታሰሩ ወይም የተማረኩ ሰዎችን ሰብአዊ መብታቸውን በማክበር አስተናግድ። ማናቸውም የመብት ጥሰትን መፈጸም የተከለከለ ነው።
6.      ያልተፈቀዱ የጦር መሣሪያዎችን አትጠቀም
7.      ግዳጅህን በምትፈጽምበት ጊዜ ምንም ዓይነት ልዩ ጥቅምን ወይም ውለታ ክፍያን አትጠብቅ። የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠርብህም አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ አድርግ።
8.      ማናቸውም በሥራ ባልደረቦችህ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትን በፍጥነት ለበላይ አካል በማሳወቅ ሕገወጥ ድርጊቱ እንዲቆም የበኩልህን ግዴታ ተወጣ። ሕገወጥ ተግባራት በቸልታ ወይም በዝምታ እየተፈጸሙ እንዲቀጥሉ በፍራቻም ሆነ በምን አገባኝ ስሜት ችላ ብለህ አትለፍ።
የሕፃናት ጥበቃ አደራረግ የሥነ ምግባር ደንቦች ለወታደራዊ ሰዎች
1.      ልዩ ትኩረት ለሴቶች እና ለሕፃናት እየሰጡ በማናቸውም ጊዜ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ
2.      የሕፃናትን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት (ለምሳሌ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ የጤና ክብካቤ ወዘተ)
3.      ሕፃናትን ከእናቶቻቸው አለመለየት
4.      ሕፃናት እስረኞችን በተቻለ መጠን በጾታና በዕድሜ ለይቶ ማቆየት
5.      ሕፃናትን አለመድፈር፣ በወሲብ አላግባብ አለመጠቀም ወይም ምንም ዓይነት ወሲብ ነክ ግንኙነት አለማድረግ
6.      ሕፃናትን ከፈንጂዎች መጠበቅ
7.      ሕፃናትን አለመቅጠር
8.      ለሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ልጅ እግር ወታደሮችን የተመለከተ መረጃን ለመስጠት መተባበር እና ሌሎችንም ድርጅቶቹ በዚህ ዙሪያ በሚፈልጓቸው ትብብሮች ላይ ተባባሪ ሆኖ መገኘት
9.      በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሁልጊዜ ለሚመለከታቸው አካላት በአግባቡ በማስረጃ ሪፖርት ማድረግ
ለልጅ እግር ወታደሮች በሚያዙበት ጊዜ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ? ለወታደራዊ ሰዎች
·         ሁሉንም ሰው በማናቸውም ጊዜ ማክበርና ክብሩን መጠበቅ
·         ግዳጅን ለመወጣት በተቻለ መጠን ዝቅተኛውን ተመጣጣኝ የጉልበት መጠን መጠቀም፥ ከበላይ የሚሰጠውን መመሪያ ማክበር
·         በማናቸውም ጊዜ ራስን ለመከላከል ዝግጁ ሆኖ መጠባበቅ
·         ከልጅ እግር ወታደሮች ጋር የሚደረግን መስተጋብር ጨምሮ አብዛኛውን ከሕፃናት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች በከፍተኛ ደረጃ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ተብለው ሊታሰብ አለመቻላቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል
·         እጃቸውን የሰጡ፣ የተማረኩ ወይም ከለላ ማግኘት የሚፈልጉ ልጅ እግር ወታደሮች እንደ ማንኛውም ሌላ የጦር ምርኮኛ ወይም እስረኛ ሁሉ ከአስፈላጊው ሰብአዊ ክብር ጋር ዓለም አቀፍ ሕጎች በማክበር መያዝ
·         የተማረኩትን ወታደሮች በአፋጣኝ ለሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በማስተላለፍ አስፈላጊውን ትምህርትና ሥልጠና አግኝተው ከኅብረተሰቡ ጋር መልሰው እንዲቀላቀሉ ማስቻል
ምክር ለወላጆች
·         ልጆችዎን ኃይል፣ ዐመፅ፣ ጦርነት እና መሰል ዘግናኝ ትዕይንቶች የሚታዩባቸውን ፊልሞች፥ ምስሎች፣ ትርዒቶች፣ የቪድዮ ጨዋታዎች፣ የእጅ ስልክ ጨዋታዎች እንዳይመለከቱ እና እንዳይጠቀሙ ማድረግ።
·         ስለ ሕፃናት መብትና ግዴታዎች በሚገባቸው ቋንቋ ከአፍላ ዕድሜያቸው እንዲገነዘቡ ማድረግ።
·         ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን ወይም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ የመገናኛ ዘዴዎች ሕፃናት የአክራሪ አስተሳሰቦችና ሥር ነቀል ለውጥ እናመጣለን ባይ አብዮተኞች ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆኑ በግልፅነት ከአፍላ ዕድሜ ጀምሮ መወያየትና አላስፈላጊ መሆኑን በመተማመን መግባባት
·         ለሃይማኖታዊ እና ሌሎች ባሕላዊ ትውፊቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ልጆች በሥነ ምግባርና በፈሪሐ እግዚአብሔር ታንፀው እንዲያድጉ ማድረግ።
·         ሕፃናት ለሚጠይቁዋቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በቂና ሳይንሳዊ የሆነ መልስ ለዕድሜያቸው በሚመጥን መልኩ አጣፍጦ ነገር ግን ምንም ነገር ሳይደብቁ ማስረዳት።  
ምክር ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ በልጅ እግር ወታደሮች መልሶ ማቋቋም ለሚሠሩ ድርጅቶች
·         ድህነትን እና ረሃብን መዋጋት።
·         ሙስና እና ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶችን የሚያስከትሉ ማኅበራዊ ንቅዘቶችን በቂ ትኩረት ሰጥቶች መዋጋት።
·         መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልጅ እግር ወታደሮችን ለመታደግ በሚሠሯቸው ሥራዎች በሙሉ በመካከላቸው ቅንጅት መኖሩን ማረጋገጥ።
·         ልጅ እግር ወታደሮች አስፈላጊውን ሥልጠና እና ትምህርት ካገኙ በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ሲደረጉ አድልዎና መገለል እንዳይደርሳባቸው ከአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር በቅርበት መሥራት እና አስፈላጊውን ቀጣይ ክትትል ማድረግ።
·         ሕፃናት በሚውሉባቸው እና በትምህርት ቤቶች አካባቢ ወታደራዊ ካምፖች በተቻለ መጠን እንዳይኖሩ ማድረግ። ወታደራዊ ካምፖች መኖራችው ግድ ከሆነ ግን ወደ ካምፑ ውስጥ ልጆች በምንም ዓይነት ምክንያት እንዳይገቡ መከላከል። በካምፑ ውስጥ የሚኖሩ ወታደሮች ወታደራዊ ልብሳቸውን እንደለበሱ በተቻለ መጠን ከሕዝብ ጋር አለመቀላቀል።
·         ሕፃናት ሊጠለፉ የሚችሉባቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ጥበቃና ክትትል ማድረግ።
·         የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበትና ማሳደግ።
·         ለደባል ሱሶች እና ከነዚህ ማገገሚያ ፕሮግራሞች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ሕፃናቱ ከደባል ሱሶች የሚላቀቁባቸውን ዘዴዎች ሳያለሰልሱ ቀጣይ ጥረት ማድረግ።
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ነሐሴ 21 በፈረንጆች 2018 (በራስ አቆጣጠር)

No comments:

Post a Comment