የንብ መጥፋትና የዓለም ሁሉ ፍጻሜ
እንደ መግቢያ
ዱሮ፣ ዱሮ ነው አሉ አንድ ሰው ዝምብሎ ጥቅም ፍለጋ ብቻ ሲጋልብ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ የተረዱ ብልሆች አባቶቻችን «ማር አገባ ፥ አገባ ፤ ገደል አገ’ባ» (እዚህኛው አገ’ባ ላይ “ገ” ይጠብቃል) ይሉ ነበር። የንብ ቀፎውን ብቻ ዐይቶ ወደ ንብ ቀፎው ለመድረስ የሚደረግ ሩጫ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አመላካች ነው። በተመሳሳይ መልኩ ታዲያ ዛሬ ምንም እንኳ የሰው ልጅ “ማር” ፍለጋ ባይሆንም “ሕይወቴን፣ ኑሮዬን ያቀሉልኛል” ያላቸውን ሳይንሳዊ መላዎችና መሣሪያዎች በመጠቀም በቴክኖሎጂ ሥልጣኔ ከከፍተኛው ማማ ላይ የወጣ ቢመስልም ዛሬም እንደ ባቢሎን ዘመን እርስ በርሱ መግባባት የተሳነው ይመስላል። ቋንቋው ክፉኛ ተደበላልቋል። ዛሬ የሰው ልጅ የማይግባባው የተለያየ ቋንቋ እያወራ ሳይሆን አንድ ተመሳሳይ ቋንቋም እያወራ ነው። እንደ ኖህ የውሃ ጥፋት ዘመን ሁሉ የዓለምን መጥፋት መቃረብን የሚያመለክቱ መለከቶች በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ በየቀኑ ይነፋሉ። ማንም ሰሚ የላቸውም። ሁሉም
ማለት በሚቻል አስፈሪ ደረጃ በደንታ ቢስነት የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሳያቋርጥ በዘፈቀደ ይኖራል። በከፍተኛ ጩኸት እየተነገሩ ካሉ ከእነዚህ የ«እንጠፋለን ፥ ወዮልን ይህን ባናደርግ !» ከሚሉ ማስጠንቀቂያ ደወሎች መካከል የትኛዎቹ እውነት ናቸው ? የትኞቹስ ዝም ብለው ማስፈራሪያ ከንቱ የቁራ ጩኸቶች ናቸው ? ጊዜ ብቻ የሚመልሳቸው ጥያቄዎች ይሆናሉ።
ተወደደም ተጠላም ግን እዚህ ላይ ሁላችንንም አንድ የሚያግባባን አሌ የማንለው ሐቅ አለ። እሱም ከቴክኖሎጂ ግሥጋሤያችን ጎን ለጎን
ወይም ትይዩ ተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ እንገኛለን።
የከባቢ አየር መዛባት (climate change) ዋንኛ
ምክንያቶች የኦዞን ሽፋን መቀደድ፣ የካርቦን ልቀት፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የውቅያኖሶችና የባሕሮች መበከል፣ የውሃ ሀብቶች መመናመን ወዘተ እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል። ከነዚህ አደጋ ውስጥ ከገቡ የምድራችን ሀብቶች አንዱ ደግሞ ማርንብ ነው።
የማርንብ ተፈጥሮ ካደለችን እጅግ ረቂቅ አሆኑ የምድር በረከቶች አንዱና ምናልባትም ዋንኛው ነው። እንዲያውም እንደ ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅና ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን አባባል «ንቦች የጠፉ ቀን የሰው ፍጡር ድራሹ ከምድረ ገጽ ይጠፋል»። እነሆ ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ እየወጡ ያሉ የጥናትና ምርምር መረጃዎች ንቦች በከፍተኛ ደረጃ በምድር ላይ መኖር የማይችሉበት ብሎም እስከ መጥፋት የሚዳርጋቸው አደጋ እንደተጋረጠባቸው ማስረጃ ይዘው በመከራከር ላይ ይገኛሉ። ይህ የጥናት ውጤት እጅግ ያሳሰባቸው የተለያዩ የተፈጥሮ ሕላዌ ደኅንነት ተከራካሪዎች በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ዘመቻዎችን በዚህ ዙሪያ እያጧጧፉ ናቸው።
ወደ
ራሳችን አገር መለስ ብለን ጉዳዩን ስንመለከተው ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ ንብ ልብሳችን ላይ ሲያርፍ ወይም ወደ ቤታችን ውስጥ ሲገባ «እሰይ ሲሳይ ነው ፥ አትንካው ወይም እንዳትገድለው» ሲባል ልብ ሳንል አልቀረንም። አባቶቻችንና እናቶቻችን ምንም እንኳ ያለ ንብ መኖር እንደማንችል የሚያውቁት ነገር ባይኖርም ንብን ባለመግደል የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ ማድረግ እንደሚቻል አንዳች ሹክ ያላቸው ነገር አለ ወይም ከኛ የደበቁን እነርሱ ብቻ የሚያውቁት ሌላ ረቂቅ ምሥጢር አለ። ይህን እውነት ጎርጉሮ ማውጣቱን በመስኩ ለተሠማሩ ተመራማሪዎች ለጊዜው ወደ ጎን በመተው ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ «ቄስና ንብ እያዩ እሳት ይገባሉ» የሚባለው ብሂል ከእንግዲህ «ቄስና የሰው ልጅ እያዩ እሳት ይገባሉ» የሚባልበት ዘመን እየደረሰ ያለ ይመስላል።
በተመሳሳይ መልኩ ከንብና ከማር ጋር የተያያዙ ትውፊቶቻችን እና ዘፈኖቻችን ሁሉ እንደ ዳይኖሰር በ«ነበር» መዝገበ ቃላት ወይም «ቤተ መዘክር» ውስጥ ሊገቡ ትንሽ የቀራቸው ይመስላል። እንደ ቦሌ፣ ሐያት፣ ሲኤምሲ፣ ኦልድ ኤርፖርት፣ ለጋጣፎ ለሚኖረው አማርኛ ላጣረው ለአዲሱ ትውልድ «ከቤት ከዋለ ንብ ፥ አደባባይ የዋለ ዝንብ» ወይም «ሰው ሲሔድ ላገር ፥ ንብ ሲሔድ ላጥር» ወይም «አውራ የሌለው ንብ ፥ አለቃ የሌለው ሕዝብ» ወይም «እንደ ንብ ቀስሞ ፥ እንደ ወጥ ቀምሞ» ምን ማለት ነው ብትሉት «ንብ ማሌት ሚን ማለት ነው ?» መልሶ ቢላችሁ በፎቶ ብቻ ለማሳየት ከምትገደዱበት ዘመን ላይ እመኑኝ ግድ የለም ! እየተዳረስን ነው።
እንደ የቅርብ ጊዜዎቹ የእሱባለው ይታየው የተዋጣላቸው «ማሬ ማሬ» ከመሳሰሉ የዘመኑ «ማር» ነክ የዘፈን ጋጋታዎች ጀምሮ ወደ ኋላ ዞር ብለን እንደ ሙሉቀን መለሰ «ኧረ ወተቴ ማሬ» የሚለው ዘፈን ድረስ
ብዙ ንብና ማርን የተመለከቱ ትውፊቶችን ማንሣት ይቻላል። ሰርጋችን የሚደምቀው «ንቦ ፥ ንቦ አትናደፊ» ፣ «ዘበናይ
ማሬ ማሬ» የሚለው ዘፈን ጀምሮ ዝርዝሩ
አታካች ነው። ዛሬ፣ ዛሬ
በትላልቅ ከተሞች «ንጹሕ ማር እኮ ጠፋ ! » ከሚለው ስሞታ አልፈን ከናካቴው ለልጆቻችን ስለማር ለማስረዳት «ማር» ማለት «የሆነ ድሮ አባቶቻችን ይበሉት የነበረ የሚጣፍጥ ነገር ነው» ወደ የምንልበት ዘመን እየተቃረብን እንደሆነ በመስኩ የተሰማሩ ሳይንቲስቶች ከወዲሁ ያሳስቡናል።
አደጋው ግን በንብ መጥፋት ብቻ የሚወስን ቀላል ነገር አይደለም። አሳዛኙ ነገር እኛም ራሳችን መጥፋችን ነው ? እንዴት ንብ ስለጠፋ የሰው ልጅም ይጠፋል ? በቀጣዩ የዚህ ጽሑፍ ሐተታ ላይ የምናገኘው ይሆናል። ይህንን ከማየታችን በፊት ግን አጠቃላይ የንብን ተፈጥሮና የአኗኗር ዘይቤ በስሱ ማየት ግድ ይለናል።
ማርንብና ተፈጥሮ
እንደ አሌክስ ስሽንከር የተባለ ጦማሪ እምነት ማር የምትሰጠው ንብ ከተፈጥሮ ልዩ በረከቶች መካከል አንዷ ናት። ሆኖም ግን ከበረከትነትም አልፎ ይችው ንብ ራሷ ለተፈጥሮ መኖር ወይም አለመኖር ቁልፍ ሚናውን ትጫወታለች። ማር ከምታመርተው ንብ ውጪ ፍሬ ሊያፈሩ የማይችሉ በርካታ ዕፅዋትና ፍራፍሬ ዛፎች ይገኛሉ። ማር አምራቿ ንብ አንድ ቀን ሕልውናዋ የጠፋ ቀን እና በዚህች ምድር ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ እነዚህ ዕፅዋቶችና ፍራፍሬ ዛፎች በሙሉ ያለ ጥርጥር የተፈጥሮ ሞታቸውን ይሞታሉ።
ማር ለጋሹ ማርንብ መጠኑ እና የክንፎቹ ስፋት ሲታይ ኢምንት ቢመስልም ለምድር መኖር ወይም አለመኖር ግን ወሳኝነት አለው። «እንዴት ?» አላችሁ። አዎ ፥ እንዴት ይህ ደቂቅ ፍጡር በምድር ላይ መኖር መቻላችንን ሊወስንልን ይችላል ብሎ መጠየቁ ብልህነት ነው።
ዱሮ ትምህርት ቤት ስንማር መቸም ንብ አበባን ቀስሞ ማር እንደሚሠራ መማራችንን የምንዘነጋው አይመስለኝም። ሆኖም ምናልባት መምህራኖቻችን ንብ ማሯን ለመሥራት አበባ ከመቅሰሟ ባሻገር የተፈጥሮ ሥነምህዳርን እንዴት እንደምትጠብቅልን አልነገሩን ይሆናል። ይህ ከሆነ ይህን ጽሑፍ ማንበብ ግድ ይላል።
ንብ ተፈጥሮ ባደላት ልዩ ዘዴ ከአንዱ አበባ ወደ አንዱ አበባ በምትሔድበት ጊዜ ዘረ-አቧራውን (pollen) በእግሮቿ በመሸከምና በማራገፍ በተመሳሳይ ጊዜ ምግቧን ማዘጋጃ ዘረአቧራ እየሸከፈች ለወደፊት ቀለቧ አበቦች እንዲያብቡ ፥ ፍሬ እንዲያፈሩና ብሎም ዘር እንዲተኩ ታደርጋለች።
በምግብነት እስካሁን ከምንገለገልባቸው 100 (አንድ መቶ) የሰብል ዓይነቶች መካከል 90% (ዘጠና በመቶ) የሚሆነው ሰብል ፍሬ የሚያፈራው በእያንዳንዱ የሰብል አበባ ላይ ዘረ-አቧራውን ከአንዱ አበባ ወደ አንዱ አበባ ንቦች በሚያደርጉት የማስተላለፍ ወይም ተውስቦ ዕፅዋትን (pollination) በመፍጠራቸው ነው። እንግዲህ የመኖር ወይም ያለመኖር ዋስትናችን ይህን ያክል በንቦች እጅ ላይ እንዲህ በቀላሉ የወደቀ መሆኑን መረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም።
ንቦች ከወንዱ ፅጌዎች (male stamens) ወደ ሴቴ ፅጌዎች (female pistils) ዘረ-አቧራን (pollen) በማስተላለፍ በራስ ተነሳሽነት እንዲሁም ተፈጥሮ ባደለቻቸው አርቆ አሳቢነት የወደፊት ሕይወታችውን ዋስትና ይሰጣሉ። በዚህም ተክሎች እንዲራቡ በሚያደርጉት አስተዋፅዖ በስፍነ ዕፅዋት ዓለም (plant kingdom) ዋንኞቹ የሥነ ተዋልዶ (reproduction) አሳላጮች መሆናቸውን ሳይንስ አስረግጦ ይነግረናል።
ሆኖም ግን ከላይ እንደ ተገለፀው ከፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ በዓለም ላይ ያሉ የንቦች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃና በሚያሳስብ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመሔድ ላይ ይገኛል። በደፈናው አነጋገር፣ የሚረጩ ፀረ አረም ኬሚካሎች፣ በንቦች በራሳቸው ላይ የተፈጠሩ የበሽታ አደጋዎች፣ ጥገኛ ተሕዋሲያንና ተባዮች፣ መጥፎ የአየር ንብረትና ሌሎችም ሰው ሠራሽ ችግሮች ለንቦች ቁጥር መመናመን በዋንኛነት የሚጠቅሱ ምክንያቶች ናቸው።
በሃዋይ አገር የሚገኘው የሃዋይ ቢጫ መልክ ያላቸው ንቦች (Hawaiian
yellow-faced bees) በ2017 ዓ.ም. እና ቦምቡስ አፊኒስ (Bombus affinis) የሚባሉት የንብ ዝርያዎች ደግሞ በ2018 ሙሉ በሙሉ ከምድረ ገጽ በመጥፋት አደጋ ላይ እንዳሉ ተዘግቧል። ዘገባውን ተከትሎም ቁጥራቸውን መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ እና ከመጥፋት ለመታደግ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው። ለዚህ በከፍተኛ ደረጃ በንቦች መንጋ ቁጥር ላይ የተስተዋለ ማሽቆልቆል በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ግን በዋንኛነት ይጠቀሳሉ።
ንቦችና አስገራሚ ተፈጥሮዋቸው
በተለምዶ አብዛኛው ሰው ማርንብ አንድ ጊዜ ከነደፈች በኋላ ትሞታለች በማለት ያምናል። ሆኖም ግን እውነታው እንዲህ አይደለም. የማርንብ መርዝ ከሆዷ ላይ የተጣበቀ ሲሆን ልክ በምትነድፍበት ጊዜ የነደፈችው አካል የማይበሳ ጠንካራ ነገር ከሆነ መርዙ መልሶ ንቢቱን ስለሚያጠቃት በገዛ እጇ እንድትሞት ያደርጋታል። እዚህ ላይ ሊታወስ የሚገባው ሴት ማርንብ ብቻ እንጂ ወንዱ ማርንብ የሚነድፍበት መርዝ የለውም።
ማርንብ በሰውነቷ ላይ ባለው ቀለም አማካይነት ምን ያክል አደገኛ እንደሆነች መልእክት እንደምታስተላልፍስ ያውቁ ኖሯል ? መልኳ ይበልጥ ቢጫ እየሆነ በሔደ ቁጥር የመርዙ ኃይልም እየጨመረ እንደሚሔድ ሳይንስ አረጋግጧል። በዚህም ንቧን ሊያጠቃ የሚነሣ ማናቸውም ኃይል ይህን አስቀድሞ በመረዳት ጥንቃቄ እንዲያደርግና እንዳይተናኮላት በተፈጥሮ ማስጠንቀቂያዋን አስቀድማ ትስጣለች ማለት ነው። አለበለዚያ ውጤቱ ያው የታወቀ ነው።
ንቦች ልክ እንደ አብዛኛዎቹ በረሪ ነፍስት ሁሉ ዓይኖቻቸው ስብስብ ክብ ዓይኖች (compound eyes) የሚባሉ የበርካታ ትናንሽ ዓይኖች ስብስብ አላቸው። በዚህም 360 ዲግሪ በየትኛውም አቅጣጫ ለማየት ታድለዋል።
አንዱ የንቦ መንጋ በአጠቃላይ አነጋገር ሦስት ዋንኛ አካላት ይኖሩታል። እነዚህም ንግሥቲቷ ንብ (አውራ ንብ በመባል በተለምዶ የምትታወቀው)፣ ድንጉላዎች (drones) እና ሠራተኛ ንቦች ናቸው። ድንጉላ ንቦች ወንድ ንቦች ሲሆኑ ለወሲባዊ ተራክቦ በረራቸው ንግሥት ንቦችን ከርቀት ነጥለው ማየት እንዲችሉ ከሌሎቹ ንቦች ይልቅ ተለቅ ያሉ ዓይኖች አሏቸው።
እያንዳንዱ ንብ በቀፎው ውስጥ የራሱ ሚና እና የሥራ ድርሻ አለው
በቀፎ ውስጥ ካሉ ንቦች መካከል የምናስተውለው ልዩነት ዓይናቸው ላይ ያለው ልዩነት ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ በንብ ቀፎው ውስጥ ያለ ንብ የራሱ የሆነ ሚና እና የሥራ ድርሻ አለው።
ንግሥቲቱ ንብ
ንግሥቲቱ ንብ ሁልጊዜ በቀፎው ውስጥ የምትኖር ሆና ብቸኛዋ በአንድ ቀፎ ውስጥ የምትገኝ ንግሥት ናት። የሥራ ድርሻዋም መራባትና ተጨማሪ ንቦችን መፈልፈል ነው። ንግሥቲቱ በቀፎው ውስጥ ላሉት ንቦች እንደ አለቃቸው ነች። በአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ እንቁላሎችን ትጥላለች። ከንቦች ሁሉ መርዟን ደጋግማ መጠቀም የምትችለው ንግሥቲቱ ንብ ብቻ ነች። ንግሥቲቱ ንብ በቀፎው ውስጥ ካሉት ሌሎች ንቦች ይልቅ በመጠኗ ተለቅ ያለች ነች። ይህ ብቻ አይደለም፦ ከሌሎቹ ይልቅ ረዥም ዕድሜ ያላት ንግሥቲቱ ንብ ነች። አንዳንድ ጊዜ እስከ ስምንት ዓመታት ድረስ በሕይወት ልትኖር እንደምትችል መረጃዎች ይጠቁማሉ !
ድንጉላ ንብ
ድንጉላ ንቦች ወይም ወንድ ንቦች ግን በአሳዛኝ ሁኔታ በሕይወት የሚቆዩት ለስምንት ሳምንታት ገደማ ወይም ለሁለት ወር ብቻ ነው። እነዚህ ደቃቃ የሆኑት ድንጉላ ንቦች መርዝ የላቸውም። በንብ ቀፎ ውስጥ ያላቸው የሠራ ድርሻ ደግሞ ከንግሥቲቱ ንብ ጋር በመዋሰብ ተጨማሪ ንቦች እንዲፈለፈሉ ማድረግ ነው። በአንድ ቀፎ ውስት በአንድ ጊዜ በሕይወት ሊኖሩ የሚችሉ ወንድ ንቦች ብዛት ከሁለት መቶ አይበልጥም። በእያንዳንዱ ሁለት ወር ርዝመት ባለው ወቅት ማብቂያ ላይ ያልሞቱ ድንጉላ ንቦች በሌሎቹ ንቦች እየተሳደዱ ከቀፎው ወጥተው እንዲሰደዱ ይደረጋሉ።
ሠራተኛ ንብ
ሠራተኛ ንቦች ከንግሥቲቱ ንብና ከድንጉላ ንቦች በተቃራኒ አብዛኛውን የቀፎውን የንብ መንጋ የሚሸፍኑ ንቦች ናቸው። ሠራተኛ ንቦች መራባት የማይችሉ ሴት ንቦች ናቸው። ወጣቶቹ ሠራተኛ ንቦች የቤት ውስጥ ንቦች (house bees) በመባል ይታወቃሉ። የሥራ ድርሻቸውም ቀፎውን ማጽዳት፣ ቀፎውን ከጠላት መከላከል፣ ንግሥቲቷን እና ድንጉላ ንቦቿን አንድ ላይ መንከባከብ እንዲሁም ገና የተፈለፈሉትን ሕፃን ንቦች ማሳደግና መንከባከብ ነው። አንድ ጊዜ ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ የመስክ ሠራተኛ ንቦች (field bees) በመባል ይታወቃሉ። ዘርአቧራ ከሚሰበስቡበት ከመስክ፣ ከአበባ ፅጌ (nectar)፣ ከውሃ እና ቀፎን ለመሥራት ንቦች የሚጠቀሙባቸው ቁሶች ከሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን ያጠፋሉ። ሠራተኛ ንቦች የሕይወት ዘመናቸው በተወለዱበት ወቅት ዓይነት የሚወሰን ይሆናል። በአጠቃላይ አነጋገር ግን ከስድስት ሳምንት እስከ ዘጠኝ ወራት ድረስ ሊዘልቅ ይችላል። ሠራተኛ ንቦች ከመንደፍት መያዣው (sting box) እና ኔክታር (nectar) ለማጓጓዝና ለማከማቸት ከሚጠቀሙበት ትርፍ ጨጓራ በተጨማሪ የኋላ እግራቸው (hind leg) ላይ ዘርአቧራ ቅርጫት (pollen basket)፣ ዘረቧራ ማመቂያ (pollen packer)፣ ዘርአቧራውን የሚያጣሩበትት ማበጠሪት (pectren)፣ ዘር አቧራውን የሚያራግፉበት ዘረአቧራ ብሩሽ (pollen brush) ስላላቸው ከሌሎቹ ንቦች ይልቅ የሰውነት አፈጣጠራቸው ይዘት ለየት ይላል። ብዙውን ጊዜ እኛን የሚነድፉን ሠራተኛ ንቦች ናቸው።
ሠራተኛ ንቦች ወይም በዋንኛነት የመስክ ንቦች የሚባሉት ዘር አበባን (pollen) እንዲሰበስቡ ከቀፎው ወደ መስክ ሲላኩ ዘር አበባውን በዘር አበባ ቅርጫታቸው እና በጉልበቶቻቸው ይዘው ወደ ቀፎዋቸው ይመለሳሉ። ሠራተኛ ንቦች ከአንድ አበባ ወደ ሌላኛው አበባ ዘር አበባን ለመቅሰም በሚጓጓዙበት ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ከአንዱ አበባ ወደ ጎረቤት አበባ ወይም ራቅ ብሎ የሚገኝ አበባ የዘር አበባውን ያራግፋሉ። ይህም ተክሉ እንዲራባ ምክንያት ይሆነዋል። አንዳንድ ተክሎች የማርንቦች ባይኖሩ ኖሮ ሊባዙና በምድር ላይ መኖራቸውን መቀጠል ከናካቴው አይቻላቸውም ነበር።
ሠራተኛ ንቦች አንድ ጊዜ የዘር አበባ ቅርጫታቸውን እንደሞሉ ወደ ቀፎዋቸው በመመለስ ያመጡትን የዘር አበባ ቀፎ ውስጥ በተዘጋጀው የምግብ ማከማቻ ላይ ከእግራቸው ያራግፋሉ።
የማር እንጀራ (honeycomb)
ስለ ንቦች ስናስብ የማር እንጀራን መጥቀስ እዚህ ላይ ግድ ይለናል። የማር እንጀራ የማርና የሰም ቅይጥ ሲሆን የሚያመርቱትም ሠራተኛ ንቦች ናቸው። የማር እንጀራው ዓይኖች ለተለያዩ ጥቅሞች ይውላል። ሕፃናቱ ንቦችን ማቆያ ማረፊያ ክፍልነት አንሥቶ እስከ በመስክ ንቦች የተሰበሰበው ዘርአበባ ማከማቻነት ድረስ የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል። በተጨማሪ በማርንቦች የሚመረተው ማር የሚከማቸው በዚሁ በማር እንጀራው ላይ ነው።
የንቦች ምግብ
ንቦች እራሳቸው በሰውነታቸው ያመረቱትን ምግብ የሚመገቡ አስገራሚ ፍጡሮች ናቸው። ይህ በሰውነታቸው የሚመረተው ማር ዓመቱን ሙሉ በቀለብነት ያገለግላቸዋል። አበባ በማይኖርበት ወቅት ይህ የማር ክምችት የምግብ መጠባበቂያ ዋስትናን ይሰጣቸዋል። ይህ ማር ከቀለብነት ባሻገር በክረምቱ ብርድ ጊዜ ለሰውነታቸው ሙቀትን ይሰጣቸዋል። በበረዶ ወይም በቅዝቃዜ እንዳይሞቱ የራሳቸው ማር ይጠብቃቸዋል።
ንቦች እንዴት ለአደጋ ሊጋለጡ ቻሉ?
የንቦችን ሕይወት አደጋ ላይ ከጣሉ በርካታ ምክንያቶች መካከል ከባቢ አየርን በካይ መርዛማ ጋዞች፣ እንደ የተንቀሳቃሽ ስልክ አውታረ መረብ (ሞባይል ኔትዎርክ) የመሳሰሉ የአየር ሞገድ ብክለቶች ፀረ አረም ኬሚካሎች እንዲሁም ጥገኛ ተህዋሲያንና ተባዮች በዋንኛነት ይጠቀሳሉ።
ፀረ አረም ኬሚካሎች
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ወዲህ በእርሻ ሥራ ላይ የፀረ አረም ኬሚካሎች ጠቀሜታ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቶ በከፍተኛ ደረጃ ተጧጡፎ በሥራ ላይ ሲውል ቆይቷል። ይህ ኒዮኒኮቲኖይድስ (neonicotinoids) በመባል የሚታወቅ ፀረ-አረም ኬሚካል በበራሪ ነፍሳት (insects) ማእከላዊ የነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት በማድረስ ነፍሳቱ ሺባ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ለሞት ይዳርጋቸዋል። ይህ ኬሚካል በንቦች ቁጥር ማሽቆልቆል ላይ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ንቦች ለኒዮኒኮቲኖድስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተለያየ መንገድ እንዲጋለጡ በሚደረጉበት ጊዜ ከፍተኛ መደናገጥ ይፈጠርባቸውና ወደ ቀፎዋቸው የሚያደርሳቸውን መንገድ ሙሉ በሙሉ እንዲረሱ ያደርጋቸዋል (በራሪ ነፍሳትን የሚያጋጥም የመርሳት በሽታ ወይም በአልዛይመር በሽታ መያዝ እንደማለት ነው)።
ጥገኛ ተሕዋሲያንና ተባዮች
ከፀረ አረም ኬሚካሎች ጎን ለጎን ሌላኛው ዋንኛ የንቦች መጥፋት መንስዔ ቫሮ ማይትስ ወይም Varrao mites የሚባሉት ተባዮች ናቸው (በተመሳሳይ መልኩ Varrao destructors ወይም ቫሮ አውዳሚዎች በመባልም ይታወቃሉ)። እነዚህ ቫሮ የሚባሉ ተባዮችያን በንብ መንጋ ያለበት ሰፈር (bee colony) ውስጥ ብቻ መራባት ይችላሉ። ቫሮዎች ትላልቆቹን እና ገና በለጋ ዕድሜ ላይ ያገኙትን ንቦች በጠቅላላ የሚያጠቁ ደም መጣጭ ተባዮች ናቸው። በነዚህ ተባዮች የሚመጣው በሽታ ንቦች እግራቸውን ወይም ክንፋቸውን እንዲያጡና አካለ ጎዶሎ እንዲሆኑ በማድረግ ቀስ በቀስ ወደ አይቀሬም ሞት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያመሩ ያስገድዳቸዋል።
ቫይረሶች
እንደ የእስራኤል ገዳይ ሽባ አድራጊቫይረስንም (Israeli Acute Paralysis Virus) መጥቀስ ይችላል። ይህ ቫይረስ የማር ንቦች እንዲራቡ የሚያስፈልጋቸውን የፕሮቲን ንጥረ ነገር እንዳይመርቱ ወይም በሰውነታቸው ውስጥ በበቂ መጠን እንዳይኖር በማድረግ በንቦች መራባት ሂደት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳርፋል።
የንብ መንጋ ያለበት ሰፈር ድንገተኛ መራቆት ችግር (Colony
Collapse Disorder)
ንብ በማንባት የሚተዳደሩ ገበሬዎች የሚያገኙት ገቢ ድንገት በማሽቆልቆል ላይ መሆኑን ይኸውም በይዞታቸው ሥር የነበሩት ዐዋቂ ንቦች ጠቅልለው ከሰፈራቸው መጥፋት በመጀመራቸው የተከሰተ መሆኑን ሪፖርት ማድረግ ከጀመሩ ወደ አንድ ዐሥርት ዓመታት ሞላቸው። የንብ ቀፎዎቹ ውስጥ ንግሥቲቱና ገና ፍልፈላ ንቦች ብቻ እየቀሩባቸው ተቸግረዋል። ለዚህ ዓይነቱ ጤናማ ያልሆነ የንብ ቀፎ ይዞታ መንሥዔ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶችን አሁንም በዋንኛነት መልሶ መጥቀስ ይቻላል።
የንቦች መጥፋት የሚያስከትለው አደጋ ምንድን ነው?
የንቦች መጥፋት ዕፅዋትን፣ እንስሳትን፣ ነዳጅና ዘይትን፣ የመሬት ገጽታን፣ አለባበስ ዘይቤን እና የሰው ልጅ ሕይወትን ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል።
የንቦች መጥፋት በዕፅዋት ላይ የሚያስከትለው አደጋ
አንዳንድ ዕፅዋቶችና ተክሎች የሚራቡት በነፋስ አማካኝነት ነው፣ ሆኖም ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ዕፅዋቶችና ተክሎች በንብ አማካኝነት ከሚራቡት አኳያ ሲታይ ብዛታቸው በጣም ጥቂት ነው የሚያስብል ነው። በዚህች ምድር በተባለች ፕላኔታችን ላይ የዕፅዋትን መራባትን በዋንኛነት የሚያካሒዱት በራሪ ነፍሳት (insects) ናቸው። ከነዚህ በራሪ ነፍሳት መካከል ጢንዚዛዎችንና ቢራቢሮዎችን መጥቀስ ቢቻልም በዚህ ተፈጥሮዋዊ የዕፅዋት ማራባት ሂደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከንቦች አንጻር ሲታይ አሁንም ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያለ ንቦች ተሳትፎ የዕፅዋት መራባት ግቡን አይመታም ፥ ልክ በድሮ ጊዜ «ያለ ሴቶች ተሳትፎ አብዮቱ ግብ አይመታም» ይባል እንደነበረው መሆኑ ነው። ንቦች ከሌሉ ዕፅዋትን ማሰብ አይቻልም። ንቦች ከሌሉ የምንወዳቸውን ፍራፍሬዎች እነ ብርቱካንን እነሙዝን፣ እነፖምን፣ እነ ጎመንን እነ አበባ ጎመንን፣ እነ ቆስጣን ፣ እነቃሪያን እነ ቲማቲምን ማሰብ አይቻልም። በአሜሪካ አገር ከተመረተው የፍራፍሬ ምርት አንድ አራተኛ የሚሆነው በማርንብ ቀጥተኛ የተክል ርቢ አስተዋፅዖ የተገኘ ስለመሆኑ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ንቦች ከጠፉ በመጀመሪያ ከምድር ላይ የሚጠፉት ዛፎች ናቸው። የዛፎች መጥፋት ደግሞ ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
ንቦች ከጠፉ ከፍተኛ የሆነ የሰብል ምርት ቀውስ ይፈጠራል ይሉናል ጥናት አድራጊ ሳይንቲስቶች። ምንም እንኳ እንደ ስንዴ እና ሩዝ የመሳሰሉ ሰብሎች የበራሪ ነፍሳትን አስተዋፅዖ ለመራባት (pollination) ባያስፈልጋቸውም፣ ሰዎች በሩዝና በዳቦ ብቻ መኖር እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።
የንቦች መጥፋት በእንስሳት ላይ የሚያስከትለው አደጋ
በዕፅዋት ማለትም በሣርና ቅጠላ ቅጠል ላይ ሕይወታቸው የተመረኮዘ ሣር በል እንስሳት (ኸርቢቨረስ) በመጀመሪያ ደረጃ የንቦች መጥፋት በሕይወታቸው ላይ አደጋ የሚያስከትልባቸው ፍጡራን ናቸው። ለምሳሌ፣ ላሞችና በሬዎች በከፍተኛ ደረጃ አልፋልፋ (alfalfa) እና ሉፒንስ (lupins) የሚባሉ በበራሪ ነፍሳት የሚራቡ የሣር ዓይነቶች ለሕልውናቸው ያስፈልጉዋቸዋል። ከብቶች ምግባቸው ላይ ችግር ከተፈጠረ የሥጋና የወተት ምርትም አብሮ ችግር ውስጥ ይገባል። ይህም በሰው ልጅ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሦስተኛው የእንስሳት መደብ ላይ የሚገኙት ሥጋ በል እንስሳት (carnivors) ወዲያውኑ የተፅዕኖው ሰለባ ይሆናሉ። በዚህ ሁሉ ሂደት ተጠቃሚ የሚሆኑት ጥንብ አንሣ ወፎች ብቻ ናቸው።
የንቦች መጥፋት በነዳጅና በዘይት ላይ የሚያስከትለው አደጋ
ካኖላ የሚባለው እንደ ነዳጅ እና ምግብ ዘይት የሚያገለግለው የዕፅዋት ዓይነት በበራሪ ነፍሳት የሚራባ ተክል ነው። ባዮጋዝ የምናገነው ከዚህ ተክል ነው። በተመሳሳይ መልኩ እዚህ ላይ እነ ሸንኮራ አገዳና መሰል የቅባት እህሎችን መጥቀስ ይቻላል። ባዮጋዝ ካልተጠቀምን ከከርሰ ምድር የሚወጣውን ነዳጅ ብቻ ለመጠቀም የምንገደድ ሲሆን ይህም በከባቢ አየር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ብዙ እየተነገረለት የሚገኝ ሌላ አደጋ ነው።
የንቦች መጥፋት በአለባበስ ዘይቤ ላይ የሚያስከትለው አደጋ
የንቦች መጥፋት በጥጥ ምርት ላይ ከፍተኛ ጫና ከማሳረፍ አልፎ ጥጥ የሚባል ነገር አብሮ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። የጥጥ መጥፋት ደግሞ በልብስ ምርጫችን ላይ የበኩሉን ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ መገመት አይዳግትም (በቆላማ አካባቢዎች ከናይለን የተፈበረኩ ልብሶችን መልበስ ይታያችኋል ?)
አብዛኛዎቹ ዕፅዋቶች መራበትና መብቀል እንደ ያለመቻላቸው በሣር የተሸፈነ መሬት ባድማ ይሆናል። በዚህም በረሃማነት ይከሰታል። የመሬት መንሸራተት የዕለት ተዕለት ገጠመኝ ይሆናል። መንደሮች በዚህ መልኩ መበታተንና መጥፋት ይጀምራሉ። ቀስ በቀስም መሬት በፕላስቲክ የተሸፈነች በረሃ ትሆናለች።
የንቦች መጥፋት በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የሚያስከትለው አደጋ
የሰብል ምርት መቀነስ ረሃብን በዓለም ዙሪያ እንዲንሰራፋ ያደርጋል። ረሃብና ድህነት የምድር ዕጣ ፈንታ ይሆናሉ። ንጹሕ የሚጠጣ ውሃ ብርቅ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። ከደን መጥፋት ጋር ውሃን ማቆር የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ውሃና ምግብ በበቂ ሁኔታ እስከሌሉ ድረስ ደግሞ የሰው ልጅ በውሃ ጥምና በጠኔ መሞቱ አያጠያይቅም። ሰው ልጅም ካልበላ ካልጠጣ ሊራባ አይችልም። በስተመጨረሻ የሰው ልጅ እንደ ፍጡር በምድር ላይ የመቀጠል ዕድሉ አብሮ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይደርሳል።
እንደ መደምደሚያ
ከንቦች መጥፋት በኋላ ለመኖር ብቸኛው አማራጭ
ንቦች ከጠፉ በኋላ በምድር ላይ ሕይወትን ለማስቀጠል ብቸኛው አማራጭ ሮቦቶች የማርንቦችን ሥራ ተክተው እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ለበርካታ የጤና ችግሮች መፍትሔ የሆነውን ጣፋጩን ማር እስከወዲያኛው ላንቀመሰው ከመለያየታችን ባሻገር አርቴፊሻሉ ኑሮ በጤናችን ላይ የሚያስከትለው አደጋና ተጽዕኖ በሮቦት ዕፅዋትን ማራባት ከጀመርን በኋላ በሚገባ በጥልቀት የምናውቀው የመጪው ትውልድ የቤት ሥራ ነው።
እነዚህን ደቃቃ ነገር ግን ዓለማችንን ቀጥ አድርገው ደግፈው የያዙ ምትሀተኛ ንቦችን ዛሬ በቸልተኝነት መግደላችን ሌላ ማንንም ሳይሆን ራሳችንን ብሎ መጻዒ የአብራካችን ክፋይ የሆነውን ትውልድ በቅኝ አዙር መግደላችን ነው። የመኖራችን ዋስትና በከፍተኛ ደረጃ የተሞረኮዘው በፕላኔታችን እና በምድር ፍጥረታት ተፈጥሮ ባደለቻቸው ዘይቤ መኖር በመቻላቸው ዕድል ላይ ነው። ይህን እውነታ መቀበል እስካልቻልን ድረስ የራሳችንን መጥፊያ ቀን እናጣድፋለን። ሚጢጢዎቹን እና ከማንም በላይ ታታሪ እንደሆኑ በመቁጠር በአርአያነት የሚጠቀሱት ንቦችን እንዳይጠፉ ለመታደግ ሥር ነቀል እርምጃ እስካልወሰድን ድረስ መኖር የመቻላችን አስተማማኝነት ክፉኛ አደጋ ላይ መሆኑ እየተባበሰ ከዕለት ወደ ዕለት ይቀጥላል።
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ተደረሰ የአቡነ አረጋዊ ቀን የቡሄ ማግስት በወርሃ ነሐሴ በ2018 ዓ.ም. (በራስ አቆጣጠር)
No comments:
Post a Comment