የልጅ እግር ወታደሮች ምንነት እና አንደምታው
(የዘመናችን ችላ የተባለ ቁጥር አንድ አንገብጋቢ አደጋ)
ተዋጊ ኃይሎች ለምን ልጅ እግር ወታደሮችን ይጠቀማሉ?
·
ሕፃናት ክፍያን ሳይጠይቁ ተዋጊ ወታደር ሊሆኑ ይችላሉ።
·
ሕፃናት በቀላሉ ሊታዘዙ፣ የተሰጣቸውን ግዳጅም በቀላሉ ሊወጡ ይቻላሉ።
·
ሕፃናት ከውትድርና ግዳጅ ውጪ ያሉ አገልግሎቶችን ያለምንም ተቃውሞ አሜን ብለው አገልግሎቱን እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል።
·
ሕፃናትን በቀላሉ ማሳመንና ለተፈለገው ዓላማ ታማኝ ወታደሮች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።
·
ሕፃናት ቢማረኩም አሳልፈው የሚሰጡት ምሥጢር ያን ያክል አደጋን ሊያስከትል አይችልም። ምክንያቱም ማራኪው ወገን ሕፃናት ናቸው በሚል እሳቤ የረቀቁ ወታደራዊ ምርመራዎችን ሊያደርግላቸው ወይም ከባድ ምሥጢሮችን እንዲያወጡ ጫና ሊያሳርፍባቸው አይችልም።
·
ሕፃናት ጦርነትን እንደ ጨዋታ ስለሚያዩት አይሰለቻቸውም።
·
ሕፃናት በጦርነት ውስጥ ካደጉ ከጦርነት ሌላ ነገር ስለማያውቁ ጦርነቱ መቸም ማብቂያ አይኖረውም።
·
ሕፃናት በጦርነት ውስጥ መኖራቸው በተቃራኔው ፕሮፌሽናል ጦር ላይ የሚደርሰው ሥነ ልቦናዊ ጫና ከባድ ነው።
·
ሕፃናት ቀለብ፥ ትጥቅ ወዘተ አይፈጁም። ባለው አቅም እና እንዳለው ሁኔታ መጠቀም ይቻላል።
·
ሕፃናትን እንደ ወሲብ መገልገያ መሣሪያ መጠቀም ይቻላል።
·
ሴት ሕፃን ወታደሮች አርግዘው ስለሚወልዱ የዐማፂ ኃይሉ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ይሔዳል። የተወለደው ሕፃን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነፍጥ አንግቦ ዐማፂውን ኃይል ይቀላቀላል።
·
ሕፃናቱ የተወሰዱባቸው ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው ሳይወዱ በግድ ለልጆቻችው ሲሉ የዐማፂውን ደህንነት ይመኛሉ፣ ዐማፂው ቡድን ላይ ምንም ጉዳት እንዳይደርስበት ከመጸለይ እና መልካሙን ከመመኘት አልፈው ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችለውን ማናቸውንም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ትብብር ያደርጋሉ።
·
ዐማፂ ቡድኑ ሕፃናት ወታደሮችን በመጠቀሙ ተነሣሁበት ያለው ዓላማ ፍትሐዊ እንደሆነ ለዓለም ለማሳመን እንደ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ይጠቀምባቸዋል። የምሬቱን ልክ ማለፍ ማሳያ ናቸው ብሎ ይከራከራል።
·
ሕፃናትን በውዴታም ሆነ በግዴታ ለተዋጊነት መመልመልም ቀላል ነው።
ልጅ ወታደሮች እንዴት እና ለምን ተዋጊ ኃይሎችን ይቀላቀላሉ?
·
ጦርነት ባለባቸው አካባቢ በመኖራቸው ምክንያት የሚኖሩበት አካባቢ በዐማፂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሲውል በግዳጅ በመመልመል ሕፃናት ወታደሮች ይሆናሉ።
·
በቀል። አባትና እናታቸውን ታላላቆቻቸውን በጦርነት ያጡ ሕፃናት በበቀል ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ካሳጣቸው ወገን በተቃራኒ ሊሰለፉ ይችላሉ።
·
ወጣትነትና ዓለምን ቶሎ የመቀየር ፅኑ ፍላጎት ወይም ትኩሳት። ታዳጊ ወጣቶች ሥር ነቀል ለውጥ እናመጣለን በሚሉ ንቅናቄዎች የመሳብ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ በዓማፂ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ከማንም በላይ ከፍተኛ ነው።
·
ዐመፅን ውጊያን የሰው ልጅ ዕልቂትን ለሚያሳዩ ጨዋታዎች፣ ቪዲዮ ጌሞች፣ ፊልሞች፣ እንደ ሽጉጥ የመሳሰሉ መጫወቻዎች ከአፍላ ዕድሜ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ መሆን ሕፃናት አማራጭ ሲያገኙ በራሳቸው ፍላጎት የልጅ እግር ወታደር እንዲሆኑ ይዳርጋቸዋል።
·
በአካባቢያቸው የጦር ካምፖችን በማየት የጦር ጄነራሎች፣ ኮነሬሎች ባለማዕረግ ወታደሮች ያላቸውን ግርማ ሞገስና ማኅበራዊ ከበሬታ በማየት ወታደር ሆኖ ከዚያ ደረጃ ለመድረስ እነዚህን የጦር መኮንኖች እንደ አርአያ የማየት ዝንባሌ ያድርባቸዋል።
·
ዲሞክራሲያዊ መንግሥታት አለመኖርና በዚህም የተነሣ በሚፈጠር ማኅበራዊ ቀውስ፣ የፍትሕ መዛባት፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና ሥር የሰደደ ድህነት ሕፃናት ራሳቸውን እና ቤተሰባቸው ከዚህ ሁሉ ስንክሳር ለመታደግ ሲሉ በተቃራኒው ለመሰለፍ እንዲችሉ ያስገድዳቸውዋል።
ስለ ልጅ ወታደሮች ሁሉም ሰው ማወቅ ያለበት መሠረታዊ እውነታዎች
በዓለም የልጅ ወታደሮች ብዛት
በዓለም ላይ ካሉ የጦር ኃይሎች መካከል ዐርባ በመቶ የሚሆኑት ልጅ እግር ወታደሮችን ይጠቀማሉ። ምንም እንኳ በመንግሥት ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ትክክለኛ ቁጥር ይሄ ነው ብሎ ለመናገር ባይቻልም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ለውትድርና እንደሚመለመሉ ይገመታል። ከዚህ በላይ
በነበረው የችግሩ ስፋት እና አስፈሪነት በሚለው አርእስት ሥር እንደ ተገለፀው በአሁኑ ጊዜ በቀጥታ በጦርነት ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሕፃናት ወይም ልጅ እግር ወታደሮች ቁጥር 300, 000 ይደርሳል። እነዚህ ሕፃናት ዕድሜያቸው ከዐራት ዓመት ጀምሮ ኣስከ ዐሥራ ስምንት ዓመት ድረስ ይዘልቃል።
በዓለም ዙሪያ የልጅ ወታደሮች ስርጭት
ምንም እንኳ ልጅ እግር ወታደሮች በአፍሪካ ውስጥ ባሉ የርስ በርስ ግጭቶችና በአገራት መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ እንደሚሳተፉ በሰፊው የሚታመን ቢሆንም በመላው ዓለም ዙሪያ ልጅ እግር ወታደሮችን ማግኘት ይቻላል። ይህም ሕፃናትን በጦርነት የማሳተፍ ወንጀል ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ የሚስተዋል ሕገወጥ ተግባር ነው። ከፈረንጆቹ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ በ21 በዓለም ዙሪያ በተደረጉ እና በመደረግ ላይ ባሉ ጦርነቶች ውስጥ ልጅ እግር ወታደሮች መሳተፋቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ድህነት እና ሌሎች የልጅ ወታደሮች ምልመላ ምክንያቶች
ድኃ የሆኑ እና ለትምህርት ዝቅተኛ ተደራሽነት ያላቸው ሕፃናት በውዴታም ሆነ በግዴታ በውትድርና የመመልመል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ሕፃናት ባላቸው ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ብስለት ደረጃ ምክንያት ከማንም በበለጠ ለውትድርና ምልመላ በተለየ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው። እምቢ ለማለት ሆነ ምን እየተባሉ እንዳሉ ለመረዳት አቅማቸው ካለመፍቀዱ ባሻገር በቀላሉ እንደ ተፈለገው አድርጎ ማሳመን እና ማሽከርከር ስለሚቻልም ሕፃናትን በጦርነት ውስጥ በሚያሳትፉ ወንጀለኞች ዘንድ ተመራጭ ወታደሮች ናቸው። እዚህ ላይ ሕፃናት ድሆች ከሆኑ፣ ከቤተሰቦቻቸው በተለያየ መንገድ እንዲለያዩ ከሆኑ፣ ከቤታቸው ከተፈናቀሉ፣ ጦርነት በሚካሔድበት ክልል ውስጥ የሚኖሩ ከሆኑ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው ለትምህርት ያላቸው ተደራሽነት የተገደበ ከሆነ እና ሥራ ፈትተው (ማለትም ትምህርት ቤት ገብተው በመማር ፈንታ) ሰፈር ውስጥ እንዲያውደለድሉ ዕድል ከተሰጣቸው ልጅ እግር የመሆን ዕድላቸው በዚያው ልክ እየጨመረ ይሔዳል።
አንዳንድ ሕፃናት ሕይወታችንን ሊያሻሽልልን ይችላል ወይም እንደ ዐዋቂ የመታየትን ዕድል ያስገኝልናል ወይም ዐዋቂ ለመቆጠር ካላቸው ፅኑ ፍላጎት የተነሣ ወይም ከድህነት ለመውጣት ሲሉ በውትድርና ውስጥ ገብተው ለማገልገል ይመርጣሉ። በርካታ ሕፃናት በሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች አስገዳጅነት በራሳቸው ፍላጎት የታጠቁ ኃይሎችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ። እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ምግብ እና የመኖር ዋስትናን እንደሚሰጡ ተደርገው በሕፃናቱ አእምሮ ሊሳሉ ይችላሉ። በአጓለ ሙታን (ሕፃናት ማሳደጊያ ያሉ) ማደጎ ሕፃናት ኣና ስደተኛ ልጆች በሕይወት ለመኖር ወታደር መሆን ብቸኛው አማራጫቸው ሆኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲታያቸው ይደረጋሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም ሕፃናት በግድ በቀጥታ በታጠቁ ኃይሎች ሊመለመሉ፣ በአቻ ዕድሜ ግፊት ተፅዕኖ ተማለው በፈቃደኝነት ሊሰለፉ ወይም በታጠቁ ኃይሎች በጠለፋ ተወስደው ወታደር ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ቴክኖሎጂያዊ ሥልጣኔ እና ግሥጋሤ ለዚህ ምልመላ እና የወንጀል ድርጊት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። አማላይ ከሆኑት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች መልክና ዓይነት በተጨማሪ ለአጠቃቀምና ለአያያዝ ቀላል መሆናቸው ሕፃናቱን ለዚህ እኩይ ምግባር በቀላሉ እንዲሠማሩ የበኩሉን አስተዋፅዖ ሳይንሳዊ ሥልጣኔ ያበረክታል። ለመሸከምና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ እንደ ኤኬ 47 ፥ ክላሺንኮቭ ፥ ኤም ሲክስቲን የመሳሰሉ አውቶማቲክ የጦር መሣሪያዎች እና የእጅ ቦንቦች ዐዋቂ ሰዎች ሊጠቀሙ በሚችሉበት ፍጥነትና ብቃት ልክ ሕፃናት ሊጠቀሙ መቻላቸው የዘመናችን አስፈሪ ገጽታ ነው።
አንዳንድ ጊዜ እንደ ምልመላው ሂደት አንድ አካል ጭካኔን እንዲለማመዱ የገዛ ቤተሰባቸውን አባል ወይም ጎረቤታቸውን ወይም ሌላ በቅርብ የሚያውቁትን ሰው እንዲገድሉ ይገደዳሉ። ይህም ሕፃናቱ ድንገት እንኳ የፀፀት ስሜት ተሰምቷቸው ወደ ተወልደው ያደጉበት ቀዬ ለመመለስ ቢፈልጉ የሠሩት ወንጀል እንዳይመለሱ ከባድ ጋሬጣ ይሆንባቸዋል። ምናልባት እንኳ የመመለስ ዕድሉን አግኝተው ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ቢደረጉ የጣት መጠቋቆሚያ መሆናቸውና የመገለል በደል ስለሚደርሳባቸው የጦር ሜዳውን ሕይወት ከሰላማዊው ሕይወት ይልቅ ሳይወዱ በግዳቸው እንዲመርጡ ይደረጋሉ።
(ይቀጥላል)
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ነሐሴ 21 ፥ 2018 (በራስ አቆጣጠር)
No comments:
Post a Comment