Tuesday, March 27, 2018

ምርጥ ሐበሻና የዜሮ (የክብ) ትስስርና ከአራት ማዕዘን ቅርጽ ጋ ያለው ነገር


ምርጥ ሐበሻና የዜሮ (የክብ) ትስስርና ከአራት ማዕዘን ቅርጽ ጋ ያለው ነገር

  1. እውነተኛ ሐበሻ ሲወለድም፣ ሲኖርም፣ ሲሞትም ጎጆ ቤት ውስጥ ነው፤ ጎጆ ቤት ቅርጹ ክብ ነው። ኮንዶሚኒየም ያለውን የኑሮና አኗኗር ስኬት እዚህ ላይ ልብ ይሏል። 
  2.  እንደ ተወለደ መሀል አናቱ ላይ ክብ ቅቤ ይደረጋል። በክብ ቅርጽ የተድቦለቦለ ቅቤ ይውጣል። ሁለቱም ዜር ቅርጽ አለው። 
  3.  ዐርባ ወይም ሰማንያ ቀን ሲሞላው ለክርስትናው በክብ ገንዳ ተጠምቆ በክብ እንጀራ ላይ ይንደባለላል።    
  4.  የሚበላው እንጀራ፣ ጢቢኛው፣ ቂጣው፣ ሙልሙሉ፣ አምባሻው፣ ቆጮው፣ ዳቦው የሚጋገረው የግድ በክብ ቅርጽ ነው።     
  5. ወጥ የሚወጣው በክብ ቅርጽ ያለው ጭልፋ ክብ ተሠርቶ ነው። ገንፎም የሚቀርበው በክብ ቅርጽ መሃሉ ላይ ክብ ጉድጓድ ተበጅቶ ቅቤ ፈሶበት ነው።    
  6.  ሐበሻ ሲያድግ ቁንጮ ተላጭቶ ነው። ቁንጮ ክብ ቅርጽ ነው። አሁንም ከዜሮ አልራቀም።    
  7.  ሐበሻ አንገቱ ላይ ክርስቲያን ከሆነ ማእተብ፣ ሲልም ጥምጣም ወይም ሙስሊም ከሆነ ቆብ አያጣውም።    
  8.  ቄስ ትምህርት ሲማር ዛፍ ሥር ክብ ሠርቶ ነው። ክብ ሆኖ የተማረው ዕድሜ ልክ እስከ ዕለተ ሞቱ የማይስተው በደንብ የሚገባው ትምህርት ነው። አራት ማዕዘን ክፍል ሆነ በአራት ማዕዘን ሠሌዳ ተምሮ ለውጥ ሲያመጣ አላየንም። ለምለሚቱ አገሬ እያለ ትላንትም ሲረዳ ነበር ዛሬም ይረዳል።   
  9.  አይሮፕላን ክብ ቅርጽ ስላለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ውስጥ ካሉ ምርጥ አየር መንገዶች አንዱ ለመባል ቢችልም ያንኑ አይሮፕላን ያበረረ ድንቅ ሐበሻ አብራሪ መኪና ሲይዝ ሥርዓት ሲጥስ ወይም አደጋ ሲደርስበት ብሎም አደጋ ሲያደርስ ይታያል፤ ምክንያቱም መኪና ቅርጹ አራት ማዕዘን ነው። ሐበሻ የአራት ማዕዘን ነገር አለርጂክ ነው ብለናል።   
  10.  ቤተክርስቲያኑ መስጊዱ ሁሉ ክብ ቅርፅ ነው። አራት ማዕዘን ከሆነ መጤ ስለሆነ ችግር ፈጣሪ ነው።     
  11.  እንስራው፣ ድስቱ፣ ምንቸቱ፣ አገልግሉ፣ ጣሳው፣ ስኒው፣ ሽክናው፣ ማክዳው፣ የቤት ቁሳቁሱ ሁሉ ክብ ነው።    
  12.  አፈርሳታ፣ ዳኝነቱ፣ ጉባኤው የሚከናወነው ክብ ሠርቶ ተቀምጦ ፊት ለፊት እየተያየ ነው። በአራት ማዕዘን አቀማመጥ ውጤታማ መሆን አይቻልም።    
  13.  ክብ የማይሠሩ ነገሮች እንኳ ቢኖሩ የግድ በተራ መዞር አለባቸው። ለምሳሌ፦ ጽዋ፣ ጉዳይ ለማስፈጸም ቢሮ መሄድ፣ ማኅበር፣ ዕቁብ፣ ዕድር ወዘተ።  
  14.  ሐበሻ በአራት ማዕዘን ቅርጽ አንድ ነገር ከሠራ እጅግ የመረረ ቁምነገር ወይም አስፈሪ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፦ ክታብ፣ ሬሳ ሣጥን፣ መቃብርና የመቃብር ድንጋይ፣ ብራና መጽሐፍ፣ መስቀል ወዘተ።    
  15.  በአራት ማዕዘን ቅርጽ የሚዘጋጁት ነጠላ፣ ኩታ፣ ጋቢ፣ ጃኖ የክት ናቸው። ዝም ተብሎ አይለብሱም።   
  16.  የጥንት ባሕላዊ ሥዕሎች በሙሉ እንደሚያሳዩት ሰው ፊቱ ቅርጽ ክብ ነው። ሁሉ ነገሩ ክብ ነው። ወይም ለክብ የተጠጋ ነው።   
  17.  ክብ (ቀለበት) ያለበት ፊደል ሳይጠቀሙ ምንም የተሟላ ዓርፍተ ነገር በግዕዝ፣ በትግርኛ ሆነ በአማርኛ ወዘተ መጻፍ አይቻልም።   
  18.  አክሱም ሐውልት ጫፉ ክብ ነው። ላሊበላ የተፈለፈለው ክብ ቅርጽ ባለው መሬት ውስጥ ተከቦ ነው።   
  19.  የንጉሥ እና የንግሥት ዘውድ ክብ ነው። አራት ማዕዘኑን ያደርጉ ወይም ምንም ያላደረጉ ታሪካቸው በስተመጨረሻ አጉል ነው። ምሳሌ፦ አፄ ዩሐንስ።  
  20.  ጦር ይዞ የግድ ጋሻ መጨመር አለበት። ክብ ከሌለ ትጥቁ አይሟላምና። ለሴቷ መቀነት፣ ለወንዱ ዝናርን መጨመር ይቻላል።   
  21.  ሐበሻ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲያማ፣ ሲያጠቃ፣ ሲወር ወዘተ የግድ ክብ ሠርቶ ነው።   
  22.  ሰውን ሲቀብር የግድ ክብ ሠርቶ በመቆም ነው።  
  23.  ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ራሱ ሦስት ክብ ነገር፣ ጎጃም ሦስት፣ ኦሮሞ ሦስት፣ ወላይታ ሦስት፣ ትግራይ ሁለት፣ አማራ ሁለት፣ ሸዋ ሁለት፣ ጐንደር ሁለት፣ አደሬ ሁለት፣ ጉራጌ አንድ፣ አፋር አንድ ክብ ነገር አላቸው።   
  24. ቀን መቊጠሪያው ልክ እንደ ሰዓት በእኩል ሠላሳ ቀናት ተከፋፍሎ ክብ ሠርቶ ሲገጥም አንድ ዓመት ይሆናል።   
  25.  በስፖርት ሜዳ መዞርን (አምስት ሺህ ወይም ዐሥር ሺህ) ወይም ከተማ መዞርን (ማራቶን) የተመለከቱ ስፖርቶች ከሆኑ ማንም አይችለውም። ምሳሌ፦ እንደ እግር ኳስ ያሉ ግን በአራት ማዕዘን ሜዳ፣ በአራት ማዕዘን ግብ የሚጫወቱ ጨዋታዎች መቼም አይቀናውም። በተመሳሳይ መልኩ ገበጣንና ቼዝን ልብ ይሏል።

No comments:

Post a Comment