Monday, June 4, 2018

ከዘመነ ደርግ የግልበጣና የግድያ ሴራዎች ኰሎኔል መንግሥቱንና ፊደል ካስትሮን ለመግደል የተደረገ ሙከራ በአሻጋሬ ጣሰው


ከማስታወሻ ደብተራችን

 

ከዘመነ ደርግ የግልበጣና የግድያ ሴራዎች
ኰሎኔል መንግሥቱንና ፊደል ካስትሮን ለመግደል የተደረገ ሙከራ

በፖለቲካ ቀውስና በሥርነቀል ለውጥ ትናጥ በነበረች ሀገር ውስጥ ያንድ ወታደራዊ መሪ የክብር ዘብ ወይም አጃቢ ሆኖ መሥራት በርካታ አስገራሚ ፥ አሳዛኝና አንዳንዴም አስደንጋጭ ድርጊቶችን እንድታዘብ ረድቶኛል። በወቅቱ ትኩረት አልሰጠኃቸውም እንጂ ፥ የታዘብኳቸውንና ያየሁኋቸውን ነገሮች በሥርዓት ብከትባቸው ኖሮ ዛሬ ደጎስ ያለ መጽሐፍ መድረስ እችል እንደነበር ሳስበው ቁጭት ቢጤ ይሰማኛል። ይሁንና እንደኔ በሕይወት የመኖር ዕድል ያልገጠማቸው ጓደኞቼ በየጦር ግንባሩ አልቀው ፥ እኔ ግን ለታሪክ ምስክርነት በመብቃቴ ተመስገን ማለቱን መርጫለሁ። ከትዝታዎቼ መሀል በጥር ወር 1969 የተካሔደው የነጄነራል ተፈሪ ባንቲ ግድያና በ1971 ደግሞ ኰሎኔል መንግሥቱንና ለጉብኝት መጥተው የነበሩት ፊደል ካስትሮ ሩዝን “ለመግደል” ተደርጎ የነበረው ሙከራ ከአስገራሚ ትዝታዎቼ ውስጥ የሚደመሩ ናቸው።
በተለይ የግድያውን ሙከራ ባስታወስኩ ቊጥር መንግሥቱ ያኔ ተገድለው ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት አቅጣጫው ይቀይር ነበር ? እያልኩ አስባለሁ። የካስትሮ አዲስ አበባ  መቅረትስ የኩባን የወደፊት እጣ ምን ዓይነት ገጽታ ይሰጠው ነበር ? በዩናይትድ ስቴትስና በሶቪዬት ኅብረት ይካሔድ የነበረው “ቀዝቃዛ ጦርነት” ጉዞው ይቀይር ነበር ? ለማንኛውም የታሪክ ጸሐፊዎች ትክክለኛውን የደርግ ዘመን መዋእለ ዜና እስኪያስነብቡን በግንባር በመገኘት የታዘብኳቸውን ሒደቶች አልፎ አልፎ ላቀርብላችሁ እሞክራለሁ።

ደርግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የደርግ አባላትና ከፍተኛ መኰንኖች እንዲስተናገዱባት የተሠራች አንድ ክብ ቅርጽ ያላት ካፊቴሪያ አለች። ይህች ካፊቴሪያ አልፎ አልፎ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ጠንሳሾች መዶለችና የንትርክ አምባም በመሆን አገልግላለች።
ባልሳሳት ዕለቱ ጥር 25 ቀን 1969 ነበር። የግቢው ጦር አባላት በሙሉ ባስቸኳይ በምኒልክ አዳራሽ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ተደረገ። ከዚያም መንግሥቱ ኃይለማርያም በደብረብርሃኑ ነባር ስፔሻል ፎርስ ወታደሮች ታጅበው ወደ አዳራሹ መጡ። ተበሳጭተዋል። ከዚያም መድረኩ ላይ ቆመው ፤

“ጓዶች ! ነገር አላበዛም። ዛሬ የመጣሁት እናንተ የማታውቁትን አዲስ ሤራ ላሳውቃችሁ ነው። ነገሩን አድምጣችሁም ውሳኔያችሁን በእኔና በእነሱ ላይ እንድትሰጡ ነው። በትልቁ ካፊቴሪያችን አንዳንድ የደርግ አባላት በተናጠል ተገናኘተው ከተወያዩ በኋላ በኔ ላይ ግድያ እንዲፈጸም ወስነዋል። ለዚሁም ዋናውም ምክንያት በስብሰባ ላይ ሠራዊቱ ተበደለ ፥ ደሞዝ ይጨመርለት ፥ የበርሃ አገልግሎቱ ዕድሜ ልክ መሆኑ ቀርቶ ከሁለት ዓመት በላይ መሆን የለበትም . . . በማለት ለመብታችሁ ጠበቅ ያለ ክርክር በማድረጌ ጦሩን አስተባብሮ ያጠፋናል ብለው ስለሰጉ ሊገድሉኝ ወስነዋል። እነዚህ ኃይሎች ደማችሁን አፍሳችሁ ፥ አጥንታችሁን ከስክሳችሁ ያቆማችሁትን አብዮት ከመቀልበሳቸው በፊት ውሳኔያችሁን ልትሰጡ ይገባል . . .” በማለት በመናገር ላይ እንዳሉ እንባቸው ስለ መጣ የመጨረሻውን ዓርፍተ ነገር እየነፈረቁ ነበር የጨረሱት።

የመንግሥቱ ኃይለማርያም ለቅሶ የወታደሩን አንጀት አባባው። አንዳንዶችም ከተቀመጡበት እየተነሡ “ለኛ የማይበጁ የደርግ አባላት ካሉ ርስዎንም እንደ ፀረ-አብዮተኛ ከቆጠሩዎት እንደዚህ ዓይነቶቹ ዐመፀኞች ጋር መራመድ ስለማንችል በዛሬው ዕለት ርምጃ እንዲወሰድባቸው” በማለት ቁጣ አዘል አስተያየት ሰጡ። ከዚህ በኋላ ተሰብሳቢ ወታደሮች መሣሪያችንን ወድረን “ሞት ! ሞት ! ሞት !” የተሰኘውን መፈክር ደጋግመን አሰማን።

መንግሥቱ እንባቸውን በመሃረባቸው ጠረጉ። ብስጭት አጨማዶት የነበረው ፊታቸው በደስታ ፈካ። ከቆሙበት ትንሽ ወደፊት ራመድ ካሉ በኋላ ፤ “ጓዶች ጥሩ ብላችኋል። የውሳኔያችሁን ውጤት ባጭር ጊዜ ታዩታላችሁ። ያሰብኩት ሁሉ እስኪሳካ ትንሽ ታገሱኝ . . .” ካሉ በኋላ በልዩ አጃቢዎቻቸው ተከበው ከአዳራሹ ወጡ።

የቤተ መንግሥቱ ወታደሮች መንግሥቱ የሰጡንን የደመወዝ ጭማሪ ተስፋ ስናጣጥምና በደስታ ስንፈነድቅ አደርን። በማግሥቱ የመንግሥቱ ውሳኔ በጦሩ ይሁንታ ተግባራዊ ሆነ። ብርጋዴር ጄነራል ተፈሪ ባንቲ ቢሮአቸው ውስጥ ሥራ ላይ እንዳሉ ተገደሉ። ሌሎች ስድስት የደርግ አባላትም ታድነው ተረሸኑ። በዕለቱ በተነሣው የቤተ መንግሥት ሁከት የመንግሥቱ ደጋፊዎች የነበሩ ሰዎችም ተገድለዋል። ዶክተር ሰናይ ልኬ በሰባት ጥይት ከተመታ በኋላ ጥቂት ቆይቶ ሲሞት ፥ ሌተና ኩሎኔል ዳንኤል አስፋውና ሁለት የበታች ሹማምንትም በዚሁ የስልጣን ሽኩቻ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።

ከዚህ በኋላ አብዮቱ “ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት” ተሸጋገረ ተባለ። መንግሥቱ ሥልጣኑን ጠቅልለው ያዙ። ምሽት ላይም እዚያች ካፊቴሪያ ውስጥ ፌሽታ ተደረገ። የመንግሥቱ ደጋፊዎች ላዳዲስ ሹመት ታጩ። የሟቾቹ ወዳጆች ደግሞ አኮረፉ። በነገራችን ላይ በዚህ ዕለት መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጥቂት ነበር ከሞት ያመለጡት። ወደ ቢሮአቸው ዘልቆ አንድ መኰንን ሊገላቸው ሲል በመስኮት ዘለው ፥ ኤፒሲ ታንክ ውስጥ ገብተው ከሞተ ሊተርፉ ችለዋል። ያም ሆን ይህ ከዚህን ጊዜ በኋላ በደርጉ ውስጥ የሚካሔደው ሽኩቻ ውስጥ ውስጡን ቢቀጥልም ነገሮች ሁሉ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ቁጥጥር ሥር ዋሉ። የሶማሌ ወረራ ፥ ነጭ ሽብር ፥ ቀይ ሽብር ፤ የኢህአፓ የከተማ ጦርነት ፤ የመኢሶን መቀናጣት ወዘተ . . .  ቀጣዩ ታሪክ ነበር።

መንግሥቱ ኃይለማርያም የሥልጣን ሽኩቻውን በአሸናፊነት ከተወጡ ካንድ ወር በኋላ የኩባው አብዮታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ ሩዝ ኢትዮጵያን ለሦስት ቀናት ጐበኙ። የኩባ ወታደሮችም የመጡት ከዚህ በኋላ ነበር። ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋርጣ ወደ ምሥራቁ ጠቅልላ የገባችውም ከዚህ ክስተት በኋላ ነበር። በመንግሥቱና በፊደል ካስትሮ ላይ የግድያ ሙከራ የተቃጣው ግን በ1971 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት በዓል 4ኛ ዓመት በከፍተኛ ሥነሥርዓት በተከበረበት ወቅት ነበር።
1971 ባለብዙ ትዝታ ዓመት ነው። የሶማሌን ወረራ በድል ተወጥተናል። መሀል አገር ውስጥም የኢህአፓ የከተማ ተዋጊዎች ተደምስሰዋል። በኤርትራም የተገንጣዮች ኃይል ቅስም ተሰብሮ መንግሥቱ ኃይለማርያም “ቆራጥ ፥ አስተዋይ ጀግና . . .” የተሰኙ ሙገሳዎች በገፍ ይጎርፍላቸው የነበረው ከዚህ ዓመት ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል።
ከነዚህ ክስተቶች አንጻር የ1971 የአብዮት በዓል በልዩ ድምቀት መከበሩ ብዙም አያስገርምም። በዚህ ታላቅ በዓል ላይ የኩባው መሪ የፊደል ካስትሮ መገኘት ደግሞ ልዩ ትርጉም ነበረው። ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያን በይፋ ለመጎብኘትና በ4ኛው የአብዮት በዓል ላይ ለመገኘት ከመስከረም 2 - እስከ 8/71 ሀገራችን ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህ ቆይታቸው ወቅት በርካታ ተቋማትን ጐብኝተዋል። “ፀረ-ኢምፔሪያሊስት” ሴሚናር ከፍተዋል። ጅጅጋ ውስጥ በተካሔደው የመልሶ ግንባታ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ከነዚህ ቀናት ባንዱ ምሽት ግን ከሞት ማምለጣቸውን ያውቁ ይሆን?
ካልተሳሳትኩ ዕለቱ መስከረም 6 ቀን 1971 ይመስለኛል። ምሽት ላይ ጥቂት አብዮታውያን ከሶሻሊስት ኩባ ከመጡት ፊደል ካስትሮ ጋር እንደሚተዋወቁ ተነገሮን ስለነበር ዝግጅት ስናደርግ መቆየታችን ትዝ ይለኛል። የደንብ ልብሳችንን በጥሩ ሁኔታ ተኩሰን ለብሰናል። የበር ጥበቃውም ሆነ የአካባቢ ቅኝታችን ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። በሁለተኛው በር አካባቢ ከሚገኘው አስፋልት ላይ አንድ የመቶ ጦር በላንድሮቨር ሆኖ በድብቅ ሥፍራ አድብቶ ይጠብቃል። የካፊቴሪያውን ዙሪያ ጥበቃ ለመረከብ የመጡት የኩባ የደኅንነት አባላትና አጃቢዎች ዙሪያ ገባውን በልዩ መሣሪያ ከመረመሩ በኋላ ፥ በተለይ አራት ኩባውያን ወደኛ መጥተው ስማቸውን ነግረውን ተዋወቁን። ከርመንቴ ፥ ሚቺ ፥ ሳንትያጎስና ሂሄዳ እንባላለን ያሉት እነዚህ የፊደል ካስትሮ ጠባቂዎች በያዙት ዎኪ-ቶኪ መልእክት ይቀባበላሉ።

የኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አጃቢዎችም ተሰባጥረው ክቧን ካፊቴሪያ ይጠብቃሉ። አንዳንዶቹ ይንጎራደዳሉ። ሻለቃ እሸቱ ገብረሕይወት ከወታደር ፖሊስ ከበደ ጋር ራቅ ብለው ቆመዋል። የስፔሻል ፎርስ አዛዥ ሻለቃ ሀብቱ በፍጥነት እየተራመዱ ወደ ሻለቃ እሸቱ ገብረሕይወት መጡ። ሻለቃ ሀብቱ አጭርና ቀጥን ይሁኑ እንጂ ፥ ቀልጣፋ ወታደራዊ አዛዥ ነበሩ።

በዚህ ሁኔታ በጥበቃ ላይ እያለን በስም የማላውቃቸው ሰባት ሰዎች በግምት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከሩብ ላይ ወደ ካፊቴሪያው መጡ። ሁሉም ካፖርት ደርበዋል። ይነጋገራሉ። ግን ምን እንደሚያወሩ መስማት አይቻልም። በተን ብለው በሁለት ቡድን ተከፍለው በረንዳው ላይ ቆመዋል። ከሰባቱ አንድ ራቅ ብሎ ብቻውን ይንጎራደዳል። የካስትሮ አጃቢዎችም የሬዲዮ ቅብብላቸውን ቀጥለዋል።

መንግሥቱ ኃይለማርያም ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ውባንቺ ቢሻውና ከልጃቸው ከትዕግሥት ጋር ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው ወደ ካፊቴሪያው አቅጣጫ ከመጡ በኋላ እንግዳ መቀበያ እንዲሆን ከተመረጠው ሥፍራ ቆመዋል። ነጣ ያለ ጸጉራም ካፖርት የለበሰው የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ልዩ ረዳት መንግሥቱ ገመቹም ከኋላቸው ቆሞ የእንግዳውን መምጣት ይጠባበቃል።

የእንግዳውን መቃረብ አብሣሪ የሆነው የትራፊክ ፖሊስ መኪና ዋይታ ድንገት ተሰማ። ፊደል ካስትሮ በሽንጣሙ መርቸዲስ የቤተመንግሥቱን በር አልፈው ውደ ውስጥ ዘለቁ። የኩባው መሪ ከመኪናው እንደወረዱ መንግሥቱ ራመድ ራመድ ብለው ወደ መኪናው በመሔድ ተቀበሏቸው። ተጨባበጡና ወደ ካፊቴሪያው ማዝገም ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ነበር ከሰባቱ ሰዎች ለየት ብሎ ይንጎራደድ የነበረው ያ ብቸኛ ሰውዬ ወደነመንግሥቱ የሮጠው። ሁኔታው ያስደነገጠው መንግሥቱ ገመቹ፤ “ቁም ! ቁም !” እያለ ሲጮህ ሰውዬው በመሮጥ ላይ እያለ “እንዳይገቡ ! እንዳይገቡ ! ሊገድሏቸው ነው !” ብሎ ጮኸ። በዚህን ጊዜ መንግሥቱንና ካስትሮን አቅጣጫ አስቀየሯቸውና ወደ ታጠቅ አዳራሽ ይዘዋቸው ሔዱ። በዚህ አጋጣሚ ሻለቃ እሸቱና ሻለቃ ሀብቱ አድፍጦ የተቀመጠውን ፈጣን መቺ ኃይል ይዘው መጥተው ካፊቴሪያውን ከበቡ። በዚህ ወቅት ነበር አንዱ የካስትሮ አጃቢ በሬዲዮ ሌላ ሥፍራ ከሚገኝ የኩባ የደህንነት አባል ጋር የመልእክት ቅብብል ሲያደርግ የሰማሁት ፤
ያልታወቀው ሰው ድምፅ ኮሞፓሶ ላ ኦራ ዴል ፕሮግራማ (ምነው የፕሮግራሙ ሰዓት ተራዘመ ?)
ከርመንቴ-ቡዌኖ ሙሶ አቬር ኤሶ ! (እስቲ ለማንኛውም እንመልከት ፤)
ያልታወቀው ሰው ድምፅ አይ ኬ ኩይዳር ! (ብቻ ጠንቀቅ በሉ !)
ከርመንቴ - ኤስታ ቢየን ኮምፓኜሮ ! (እሺ ጓድ! )
ይህ የሬዲዮ ቅብብል ፈጠን ባለ ሁኔታ እየተካሔደ ሳለ ሻለቃ እሸቴና ሻለቃ ሀብቱ ወታደሮቻቸውን ይዘው ካፊቴሪያውን ከበቡ። በዚሁ ጊዜ ሁለት ቀልጣፋ ወታደሮች (የስፔሻል ፎርስ አባላት) ዘለው ወደ ካፊቴሪያው በመግባት በመሥመር የቆሙትን እነዚያን ስድስት ሰዎች ፋታ በማይሰጥ ሁኔታ አስደንግጠው “እጅ ወደ ላይ !” ሲሉ ጮኹባቸው።
ከነዚህ ስድስት ሰዎች መሀል አንዳቸውም ሳይንቀሳቀሱ በዚህ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ፥ ሻለቃ እሸቱ ገብረሕይወት ከነበሩበት ወደ ካፊቴሪያው መጡ። ከዚያም የሰዎችኑን ካፖርት ቁልፎች ፈትተው ከብብታቸው ሥር ማክ 32 ፥ ኡዚ ፥ ኮልት ነጥብ 38 ፥ ኮልት 45 ሽጉጦችንና ነጥብ 22 ድምፅ አልባ ሽጉጥ ከነጠቁዋቸው በኋላ ወታደሮች በሜዳ ቴኒስ መጫወቻው በኩል በሰደፍ እየተገፈተሩ ወደ “ሞርታር” እስር ቤት ወሰዷቸው።

እስረኞቹ መራቃቸውን ካረጋገጡ በኋላ ሻለቃ እሸቱ ኰሎኔል መንግሥቱንና ፊደል ካስትሮን ወደ ካፊቴሪያው አስገቡ። ከዚያም ያን ጓደኞቹን ያጋለጠ ሰውዬ ይዘው ወደ ቢሮአቸው ሔዱ። ከዚህ በኋላ ግብዣው ደርቶ ጨወታው ሞቆ አመሸ። እኩለ ሌሊት ላይም የግብዣው ሥነ ሥርዓት በመልካም ሁኔታ ተፈጸመ። መንግሥቱንና ምናልባትም ፊደል ካስትሮን ለመግደል ተቀናብሮ የነበረው ሤራ ያለ ብዙ ግርግር ሊኮላሽ ችሏል።

በማግሥቱ እነዚያ ስድስት ሰዎች ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት በሾክስዋገን መኪና ከእስር ቤት ተጭነው ተወሰዱ። ያ ሰውዬ ግን ለአገልግሎቱ የሹመት ሽልማት ሳያገኝ የቀረ አይመስልም። ይህን የግድያ ሙከራ ባስታወስኩ ቊጥር ድርጊቱ ተራ ግድያ ወይስ ሶሻሊዝምን በኢትዮጵያና በኩባ ለማዳከም በሲአይኤ የተጠነሰሰ ሤራ ? የሚል ጥያቄ በውስጤ ያቃጭላል። ሲአይኤ ፊደል ካስትሮን ለመግደል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል እየተባለ ከሚወራው አንፃር ፥ በማንም ተቀናበረ በማን ይኼኛው ለውጤታማነት የተቃረበ ከመሆኑ አንፃር ቀላል ቅንብር መስሎ አልታየኝም። እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ ? ለምንስ በድብቅ ከፊደል ጋር እንዲተዋወቁ ተፈለገ ? የነፍስ ወከፍ መሣሪያቸውንስ እንዴት ሊገቡ ቻሉ ወይስ መሣሪያ ይዞ የመግባት መብት ነበራቸው ? ስለዚህ የግድያ ሙከራ ዝርዝር መረጃ ካለዎት “አቢሲኒያ” እንደምታስተናግድዎ ተስፋ አደርጋለሁ። በነገራችን ላይ ያ ጓደኞቹን ያጋለጠ ሰው ዛሬም በሕይወት አሉ። በስም ባላውቀውም በመልክ ግን አይጠፋኝም።

አሻጋሬ ጣሰው

አቢሲኒያ ኅዳር 1986 ቅጽ 1 ቊጥር 9
ዋና አዘጋጅ ሙሉጌታ ጉደታ
አሳታሚ
አቢሲኒንያ የሕትመትና የማስታወቂያ ድርጅት



No comments:

Post a Comment