Tuesday, June 19, 2018

ስደት

ስደት
ካገሩ የወጣ ካገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑበት በቅሎ ቢጋልቡት ፈረስ
ካዝማሪ አፍ አምሮ ሲለፈፍ
አምሮ ተጽፎ ጥቅሱ ሲለጠፍ
ሲዖል ሣቀች ባዝማሪ
ዐይታ ሲስት ቀባጣሪ
ሰው ቀዬውን ዘግቶ
ከቤት ካገር ሲርቅ
አልሆን ቢል ተከፍቶ
ከሰው ቤት ሲወድቅ
በሰው አገር ራሱን ሲሸጥ
ብኩርናውን ባዶ ሲለውጥ
ቤቱን በልቶት ዳዋ
ዐረፍ ቢል ከሰው ታዛ
ዕድሜ ጉልበቱን ሲሰዋ
ወርቅ ሸጦ አፈር ቢገዛ
ባይኖረው ነው ተስፋ
ባይኖረው ነው ነገ
ነገ ከነገ ወዲያ
አሻግሮ ያየ አንገቱ የሰገገ
ባይኖረው ነው ተስፋ
ባይኖረው ነው ነገ
ነገ ከነገ ወዲያ
እና ቢጭኑት ባይጭኑት
ቢሰቅሉ ቢያወርዱት
አገሩ ከቀረች ተሸርፋ በልቡ
አገሩ ከሞተች ተኝታ በልቡ
ምንስ ቢያደርጉት የለም ከቀልቡ
እግሩን ያነሳ ቀን ሞቷል በሐሳቡ
ስደት የገባ ቀን አርጓል በምናቡ
ካምላክ ነው ፍርዱ
ካምላክ ነው ጠቡ
ቤት ቤተሰብ ዘመድ ወዳጅ በትኖ
በቃ ጠፍቷል ሄዶ እንደ ውሃ ተኖ
ኋላውን ላያይ እንደ ሎጥ ሚስት
ተስፋን እምነትን ገድሎ ቀብሯል ከፊት
ሲዖልን መኖር ነው ስደት
ሲዖልን መልመድ ነው ስደት
የምን ስርየት የምን ምጻት
ስደት ማለት ነው ወጥቶ መቅረት
እያዩ ማንቀላፋት ሳይኖሩ መሞት
ሚካኤል የሰኔው 2018
ዶ/ር ዐቢይ ለመለሳቸውና ገና ለሚመልሳቸው

No comments:

Post a Comment