Friday, June 29, 2018

አንቺና እርስዎ

አንቺና እርስዎ

አንቺ ባለማለቴ ምነው መቀየምዎ
በሆዴ ባይገቡ ባልገባ በሆድዎ
ባይሆን የሚያምርብዎ በጣም እንድቀርብዎ
እሷን ይተውልኝ ፥ አለኝ ጉዳይ ከዛች ልጅዎ



ሰኔ ሁለት ሁለት አንድ ላይ ሲጻፍ ኡራኤል ለት [2018]
ብሩክ በ.

Tuesday, June 19, 2018

ስደት

ስደት
ካገሩ የወጣ ካገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑበት በቅሎ ቢጋልቡት ፈረስ
ካዝማሪ አፍ አምሮ ሲለፈፍ
አምሮ ተጽፎ ጥቅሱ ሲለጠፍ
ሲዖል ሣቀች ባዝማሪ
ዐይታ ሲስት ቀባጣሪ
ሰው ቀዬውን ዘግቶ
ከቤት ካገር ሲርቅ
አልሆን ቢል ተከፍቶ
ከሰው ቤት ሲወድቅ
በሰው አገር ራሱን ሲሸጥ
ብኩርናውን ባዶ ሲለውጥ
ቤቱን በልቶት ዳዋ
ዐረፍ ቢል ከሰው ታዛ
ዕድሜ ጉልበቱን ሲሰዋ
ወርቅ ሸጦ አፈር ቢገዛ
ባይኖረው ነው ተስፋ
ባይኖረው ነው ነገ
ነገ ከነገ ወዲያ
አሻግሮ ያየ አንገቱ የሰገገ
ባይኖረው ነው ተስፋ
ባይኖረው ነው ነገ
ነገ ከነገ ወዲያ
እና ቢጭኑት ባይጭኑት
ቢሰቅሉ ቢያወርዱት
አገሩ ከቀረች ተሸርፋ በልቡ
አገሩ ከሞተች ተኝታ በልቡ
ምንስ ቢያደርጉት የለም ከቀልቡ
እግሩን ያነሳ ቀን ሞቷል በሐሳቡ
ስደት የገባ ቀን አርጓል በምናቡ
ካምላክ ነው ፍርዱ
ካምላክ ነው ጠቡ
ቤት ቤተሰብ ዘመድ ወዳጅ በትኖ
በቃ ጠፍቷል ሄዶ እንደ ውሃ ተኖ
ኋላውን ላያይ እንደ ሎጥ ሚስት
ተስፋን እምነትን ገድሎ ቀብሯል ከፊት
ሲዖልን መኖር ነው ስደት
ሲዖልን መልመድ ነው ስደት
የምን ስርየት የምን ምጻት
ስደት ማለት ነው ወጥቶ መቅረት
እያዩ ማንቀላፋት ሳይኖሩ መሞት
ሚካኤል የሰኔው 2018
ዶ/ር ዐቢይ ለመለሳቸውና ገና ለሚመልሳቸው

Wednesday, June 13, 2018

ጭንቅላት

ጭንቅላት
ዐውቃለሁ ግድየለም ፥ ጥንትም መታወቁ
በድፍን አገር ዞሮ ፥ ባደባባይ ጣይ መሞቁ
ያኔም እንደሚታወቅ ፥ ከወገብ በላይ ጥጋብ
ያመጣል አይቀርም ፥ ከወገብ በታች እራብ
እና ያቺ ልጅ እንዲያ ጭንቅ ያላት
ባይኖራት ነው ማሰቢያ ጭንቅላት
ቁንጣን ከያዛት በቅበላ
ተዋት ትጥገብ ኣላንድ ቀን አትበላ
ባንጎል ትታ ብታስብ በ*ላት
ግድነው ጭንቅ ቢላት
ግድነው ጭንቅላት
ሬብ ቆሽት ምን አቅም አላት

ብሩክ በ. በዕለተ ስላሴ የሰኔው 2018 [በራሴ አቆጣጠር]

ለምን?

ለምን ?
ለምን የሚል ጅል ጥያቄ አለኝ 
እንደ ልጅነቴ
ለምን ግን ለምን እቴቴ
ለምን ግን አጎቴ
ለምን ሁለት አፍንጫ ቀደዳ 
ባንድ ሰርን አንዴ ለማሽተት
ለምን ሁለት ጆሮ ግራና ቀኝ 
ባንድ ጆሮ ግንድ ለመስማት
ለምን ሁለት ዓይን ግራና ቀኝ የማይተያዩ
ሌላውን አማርጠው የሚያዩ
ለምን ሁለት እጅ አንዱ ምንም ላይበጅ
ለምን ሁለት ኩላሊት አንዱ ምንም ላይበጅ
ለምን ሁለት እግር
ለምን ሁለት አንጀት ታላቅና ታናሽ
ለምን ሁለት ሳንባ አየር አመላላሽ
ለምን ሁለት ልብ ደም ቀጂ ፥ ደም መላሽ
ለምን ሁለት መንታ አንጎል ግራና ቀኝ የተጣብቁ
የማይላቀቁ፣ ምንነታቸው ያልታወቁ
ሁለንተናችን ፥ ነገር ዓለማችን ሁለት ሆኖ
መጨረሻው ባንድ የማይታይ ተበይኖ
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካልገባን እንላለን
እነሱ እኛን ፈጥረውን
ብሩክ በ. ሰኔ 6፥ 2018 [በራሴ አቆጣጠር] 
ክፍል ፩ ነው
ያውጣኝ ከክፍል ፪
ያውጣኝ በይ እቴቴ
ያውጣኝ በል አጎቴ

እግዚአብሔርም ብሔር አለው ብለሽ

እግዚአብሔርም ብሔር አለው ብለሽ
በብሔር ራስሽን የገለፅሽ
እግዜር ሁሉም ጋ ከፍ ብሎ
ወደ ላይ ወጣልሽ
ከአድማስ በላይ
ርቆ ከሰማይ ሔደልሽ
አንቺ ግን አሁንም እዚያው ነሽ
የማይዘረጋ ሰንደቅሽን
ሟች ባንዲራሽን
ከታች ገና ትቋጥሪያለሽ
ብሩክ በ. ሰኔ 5/2018

Thursday, June 7, 2018

ነገረ ሰብ

ነገረ ሰብ

በጣም ብዙዎች
አንዲት ኢንች ስትሰጣቸው
አንድ ማይል አይቀር መውሰዳቸው
እና ሌሎች ብዙዎች
አንድ ማይ ሲሰጣቸው
የታለ ኢንቹ አይቀር ማለታቸው
ዝም ብለህ ብቻ ገሥግሥ
ከነፈሰው አትንፈስ
ምንም ቢደረግ እንደማይረካ
ታይቷልና ያኔ ዕፀበለሱን ሲነካ
ያዳምን ዘር አርካለሁ ብለህ አትኳትን
ሔዋንን ዘር አርካለሁ ብለህ አትቦዝን
ሥራህን ብቻ ሥራ የፊት የፊትህን
ሕሊናህን ታዘዝ አስደስት ቀልብህን

ብሩክ በየነ ሰኔ 1/ 2018 [በራሴ አቆጣጠር]
 
 

የባይተዋር ቀብር ብሎ ነገር

የባይተዋር ቀብር ብሎ ነገር

የሰዎችን አጭር የሕይወት ታሪክ
ቀብራቸው ላይ ሰምቼ ፥ ሰምቼ
ሁሉንም አንድ ሆኖ አግኝቼ
ገነት እንደሞላ ገብቶኝ
ተስፋ ቆርጪያለሁ ወገኖቼ።
ይላል ምስኪን ታዛቢ ተመራማሪ
ምናልባት ከባይተዋር ቀብር ተቀባሪ

ብሩክ በ. ሰኔ 1/2018 [በራሴ አቆጣጠር]

ምስል አርዕስት ፦ ከንቱ ያለፉ ግመሎች