ቆንጆ ሴት ልጅ የወለደው ዔሊ ታሪክ
የናይጄሪያ ተረት ተረት
ባንድ ዘመን
አንድ እጅግ ኃይለኛ የሆነ ንጉሥ በሁሉም ዘንድ ተፈርቶ ይኖር ነበር። በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ የዱር አራዊት እና እንስሳት
ሁሉ በጣም ይፈሩት ነበር። በዚያን ዘመን ታዲያ ዔሊ በሁሉም የእንስሳትና የሰው ዘር ዘንድ እንደ ከሁሉም የበለጠ ብልህ እንስሳ
እና ከሰዎችም ሁሉ ይበልጥ የተሻለ ጠቢብ ተደርጎ ይገመት ነበር። ይህ በዚያ ዘመን
የነበረ ንጉሥም ሃምሳ ልጃገረዶች ሚስቶቹ እንዲሆኑ የዳረለት ኤክፔንዮን የተባለ ወንድ ልጅ ነበረው፤ ሆኖም ግን ልዑሉ ከሚስቶቹ
ማናቸውንም አይወዳቸውም ነበር። ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም ተበሳጭቶ ማንም ሰው ከልዑሉ ሚስቶች የበለጠች የተሻለች ቆንጆ ልጅ ከወለደ
እና አልጋ ወራሹ ከወደዳት ልጃገረዲቱ ራሷ እና አባቷ እንዲሁም እናቷ እንዲገደሉ የሚያዝ ሕግ አወጣ።
ታዲያ ይህን
ጊዜ ዔሊው እና ሚስቱ በጣም ቆንጆ የሆነች ሴት ልጅ ነበረቻቸው። ልዑሉ በፍቅሯ ሊያዝ ስለሚችል እናቲቱ እንዲህ የመሰለችውን መልከ
መልካም ልጅ አብራቸው እንድትኖር መፍቀዱ ጥሩ አይሆንም ብላ አሰበች። ስለዚህም ልጃቸው
መገደልና ጫካ ውስጥ በድብቅ መጣል እንዳለባት ለባሏ ነገረችው። ዔሊው ግን ፍቃደኛ አልነበረም በመሆኑም ዕድሜዋ ሦስት ዓመት እስኪሞላት
ድረስ ልጁን ደብቆ አሳደጋት።
ከእለታት አንድ ቀን ዔሊው እና ሚስቱ የእርሻ ሥራቸውን ለመሥራት ከቤት ርቀው የሄዱ ዕለት፣ የንጉሡ
ልጅ በእነርሱ ቤት አካባቢ አደን እያደነ ነበረና በእነሱ ቤት ዙሪያ ላይ ባለው አጥር ጫፍ ላይ ከላይ የተቀመጠ ወፍ ተመለከተ።
ወፉ ትንሽየዋን ሕፃን ልጅ እየተመለከተና በውበቷ በጣም ተማርኮ ስለነበረ ልዑሉ ሲመጣ ልብ አላለም። ልዑሉም ወፉን ደጋኑን ወድሮ ቀስቱን በማስወንጨፍ ወፉን መትቶ ሲጥለው ወፉ አጥሩ ውስጥ
ወደቀ። በመሆኑም ልዑሉ አንዱን አሽከሩን ወደ ግቢው ውስጥ ገብቶ ወፉን እንዲያመጣለት አዘዘው። አሽከርየው ወፉን ግቢ ውስጥ እየፈለገ
ሳለ ድንገት ሕፃኗን ልጅ አያትና በውበቷ በጣም ደነገጠ። ወዲያውኑ ወደ አለቃው ተመልሶ በመሄድ ያየውን ሁሉ ነገረው። ልዑሉ አጥሩን
አፍርሶ ገባና ሕፃኗን ልጅ አገኛት፤ እንዳያትም ወዲያውኑ በፍቅሯ ተማረከ። ሚስቱ እንደምትሆን መስማማቷን እስከምትገልጽለት ድረስ
ከርሷ ጋር ቆይቶ ለረዥም ጊዜም አዋራት። ከዚህ በኋላ ወደቤቱ ተመልሶ ሄደ ሆኖም ግን ከዔሊው ልጅ ጋር ፍቅር መያዙን በተመለከተ
ምሥጢሩን ካባቱ ደበቀው።
ሆኖም ግን
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ላይ ዐቃቤ ንዋዩን መልእክት አስላከበትና ስልሳ ቦንዳ ልብስ እንዲሁም ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ ወሰደ ከዚያም
ይህን ሁሉ ንብረት በገጸ በረከትነት ለዔሊው ላከለት። በመቀጠል ከሰዓት በኋላ ላይ ልክ ምሳ እንደተበላ ወደ ዔሊው ቤት ራሱ ሄደና
ሴት ልጁን ሊያገባት እንደሚፈልግ ነገረው። ዔሊው ወዲያውኑ የፈራው ነገር እንደደረሰና ሕይወቱም አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ገባው፤
በመሆኑም ንጉሡ ይህን ነገር ካወቀ ራሱን ዔሊውን ብቻ ሳይሆን ሚስቱን እና ሴት ልጁን እንደሚገድላቸው ለልዑሉ ነገረው። ልዑሉ ዔሊው፣ ሚስቱ እና ሴት ልጁ ከመገደላቸው በፊት ራሱ ልዑሉ እንደሚገደል ስለዚህም
ይህ እንዲሆን በምንም መልኩ እንደማይፈቅድ መልስ ሰጠው። በስተመጨረሻም፣ ከብዙ ክርክር በኋላ፣ ዔሊው መስማማቱን በመግለጽ ፍቃደኛነቱን
አረጋገጠ፤ ብሎም ልጁ ትክክለኛው ዕድሜ ላይ ስትደርስ ሚስቱ እንድትሆን እጇን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። በመቀጠል ልዑሉ ወደ ቤቱ
ተመልሶ ሄደና ምን እንዳደረገ ለእናቱ ነገራት። ንጉሡ ልጇ ትእዛዙን እንደጣሰ ያወቀ ጊዜ እንደሚገድለው ስለምታውቅ በጣም የምትወደውን
እና የምትኮራበትን አንድ ልጇን እንደምታጣ ስታስበው ከፍተኛ ጭንቀት አደረባት። ሆኖም ግን ንግሥቲቱ ምንም እንኳ ባሏ ምን ያክል
ሊናደድና ሊበሳጭ እንደሚችል ብታውቅም ልጇ ፍቅር ከያዘው ልጃገረድ ጋር እንዲጋባላት ፈለገች። ስለዚህም ወደ ዔሊው ዘንድ በመሄድ
ልጇ ከሰጠው ጥሎሽ በተጨማሪ በልጇ ፈንታ የተወሰነ ገንዘብ፣ ልብሶች፣ ስኳር ድንች እና የዘንባባ ፍሬ ዘይት ለዔሊው ሰጠችው። ይህን
ያደረገችውም ዔሊው ልጁን ለሌላ ወንድ አሳልፎ እንዳይሰጥ ለማድረግ በማሰብ ነበር።
ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ልዑሉ በቀጣይነት
ስሟ አዴት ከሚባለው ከዔሊው ልጅ ጋር በቀጣይነት ሲገናኝ ነበር እናም ዕድሜዋ ደርሶ ወደ ጫጉላ ቤት መግቢያዋ ጊዜ ሲደርስ ልዑሉ
ለአባቱ፣ ለንጉሡ አዴትን ሚስቱ አድርጎ ሊወስዳት መዘጋጀቱን ነገረው። ይህን ሲሰማ ንጉሡ
በጣም ተናደደ። የሚሰጠውን ፍርድም እንዲሰሙ ሁሉም ሰዎች በሆነ የተወሰነ አንድ ቀን ወደ ገበያ ቦታው እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ አስተላለፈ።
የቀጠሮው ቀን ሲደርስ፣ የገበያ ቦታው በሰዎች ተሞልቶ ነበር እንዲሁም የንጉሡ እና የንግሥቲቱ ድንጋዮች በገበያ ቦታው መሃል ለመሃል
ተቀምጠው ነበር።
ንጉሡ እና
ንግሥቲቱ ከቦታው ሲደርሱ ሁሉም ሰዎች ከተቀመጡበት ተነሡ እና እጅ ነሡዋቸው። ንጉሡና ንግሥቲቱም በራሳቸው ድንጋዮች ላይ ተቀመጡ።
በመቀጠል ንጉሡ አሽከሮቹን አዴት የምትባለውን ልጃገረድ ከፊቱ እንዲያቀርቡዋት አዘዛቸው። ልክ ስትመጣ ንጉሡ በውበቷ በጣም ተደመመ።
ልጁ ትእዛዙን ስላላከበረና አዴትን እርሱ ሳያውቅ ሚስቱ ስላደረጋት በጣም መናደዱን ሊነግራቸው እንደሰበሰባቸው ለሕዝቡ ተናገራቸውና
ሆኖም ግን አሁን ራሱ መልኳን ስላየውና ቆንጆ መሆኗን ማመን እንዳለበት እና ልጁ ትክክለኛ ምርጫ እንደመረጠ አመነ። በመሆኑም ለልጁ
ይቅርታ እንዳደረገለት አስታወቃቸው።
ሰዎቹ ልጃገረዲቱን
ሲያዩዋት በጣም ቆንጆ መሆኗን አዩ እና የልዑሉም ሚስት ለመሆን እንደምትመጥን ተረዱ። ለጥቀውም ንጉሡ ያወጣውን ሕግ ሙሉ በሙሉ
እንዲሰርዘው ለመኑት። ንጉሡም በሐሳባቸው ተስማማ። ሕጉ የወጣው በ”ኢግቦ” ሕግ መሠረት የወጣ ስለነበር ግን ወደ ስምንት ኢግቦዎች
መልእክት ልኮ ካስመጣቸው በኋላ በመላ ግዛቱ ትእዛዙ መሰረዙን ብሎም ማንም ከልዑሉ ሚስቶች የበለጠ ቆንጆ ልጅ ስለወለደ እንደማይገደል
ነገራቸው። ሕጉን እንዲሽሩም ለኢግቦዎቹ የዘንባባ ፍሬ ወይን
እና ገንዘብ ሰጥቶ አሰናበታቸው። በመቀጠል የዔሊው ልጅ አዴት ልጁን እንደምታገባ አዋጅ አስነግሮ ያንኑ ቀን እንዲጋቡ አስደረገ።
ለሃምሳ ቀናት የቆየ ትልቅ ድግስ ተደግሶ ግብር አበላ፣ ንጉሡ አምስት ላሞችን አሳርዶ ለሕዝቡ እስኪበቃቸው እንዲበሉ እና እንዲጠጡ
ብዙ ምግብ እና የዘንባባ ፍሬ ወይን በገንቦ አቀረበላቸው። ሕዝቡም እንደፈለገ በየጎዳናው ላይ ጠግቦ ሰከረ። ሴቶቹ በንጉሡ ቅጽረ
ግቢ ዘፈን እና እስክስታ ጨዋታ እየተጫወቱ ሌት ተቀን ለሃምሳ ቀናት ግቢውን አደመቁት። ልዑሉ እና ጓደኞቹም በገበያ ቦታው ላይ
ጨፈሩ። ድግሱ ሲጠናቀቅ ለዔሊው ግዛቱ ሆኖ እንዲያስተዳድር ግማሽ ግዛቱን ሰጠው፤ በተጨማሪም ሦስት መቶ ባርያዎችን በእርሻው እንዲሠሩለት
በስጦታ መልክ አበረከተለት። ልዑሉ በተጨማሪ ለአማቹ ሁለት መቶ ሴቶችን እና አንድ መቶ ልጃገረዶችን ገረዶቹ ሆነው እንዲያገለግሉት
ሰጠው። በዚህም ምክንያት ዔሊው በግዛቲቱ ውስጥ ካሉት ሃብታሞች መካከል አንዱ ሆነ። ልዑሉ እና ሚስቱ ንጉሡ እስኪሞት ድረስ በደስታ
አብረው ኖሩና ንጉሡ ሲሞት ልዑሉ በንጉሡ እግር ተተክቶ ነገሠ። እና ይህ ሁሉ ዔሊው ከሁሉም ሰዎች እና እንስሳት ሁሉ ይልቅ ይበልጥ
ብልጥ እንደሆነ ያሳያል።
ከታሪኩ
የሚገኘው ትምህርት፦ የፈለገውን ያክል ድሀ ብትሆንም ቆንጆ ሴት ልጆችን ከመውለድ አትቦዝን፣ የንጉሡ ልጅ በፍቅራቸው ሊወድቅና የልዑላን
ቤተሰብ አባል ሆነው ብዙ ሀብት ሊያፈሩ ይችላሉና።
No comments:
Post a Comment