Monday, April 9, 2018

የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ 101

የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ 101 የበዓል ቀን ዝግጅት ፕሮግራም አመራር ጥበብ (ከገጽ 23 እስከ 24) ላይ የተወሰደ፦
1. የሃገር በዓል ልብስ መልበስ
2. ፋውንዴሽን መለቅለቅ፣ አርቴፊሻል ጸጒር ማጥለቅ ወንድ ከሆነ ቀለም መነከር
3. የሚከተለውን እንድ አስፈላጊነቱ በመቀያየር በቃል መያዝን እና ማነብነብ
"እንደምን አደራችሁ/ዋላችሁ/አመሻችሁ ክቡራት እና ክቡራን ተመልካቾቻችን ይህ ፕሮግራም እየተላለፈላችሁ ያለው ከምናምን ቴሌቪዥን ከምናንምን ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ነው። ይህ ፕሮግራም እየተላለፋላችሁ ያለው ፕሮግራሙን በፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ካደረገላችሁ [ፕላቲኒየም ምን ማለት ነው ብሎ ጠያቂ ስሌለ አይዞህ አትፋራ/አትፍሪ] ከእንቶኔ ሆቴል ሲሆን ይህ ፕሮግራም ስፖንሰር አድርጎ በአንደኛ ደረጃ ስፖንሰር ያደረገላችሁ
ምናምን ቢራ
ምንትሶ ውሃ
ምናምንቴ ፍራሽ
ምናምን ሞል [ስማቸውን እንደአስፈጊነት እየተኩ ማነብነብ ነው]
አብሮነታችሁ አይለየን።
የበዓሉን ታሪክ አውራ። ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ይከበራል? ለምን?
በመቀጠል የምናቀርብላችህ ታዋቂውንና ተወዳጁን አንጋፋውን/ እገሌ/እገሊት ይሆናል። [አዲስ ከሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን በማግኘት ከፍተኛ አድናቆትን እየተጎናፀፈ ያለውን በሚል ይተካ] ለበርካታ ዓመታት ቅብርሶ ሆኖ ሠርቷል፣ ሠርታለች አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። ተወዳጁ እና አንጋፋው ምናምን ወደ መድረክ [ጩኽ/ጩኺ]። ጭብጨባ [ጭብጨባ ከሌለ በኤዲቲንግ ይድመቅ]
እንኳን ወደ ምናምን ያለህን ጠባብ ጊዜ አጣበህ መጣህ በፕሮግራማችን እና በስፖንሰሮቻችን [ስማቸው ይዘርዘር] እንዲሁም እዚህ እና በየቤታቸው በሚከታተሉን ተመልካቾች ስም እናመሰግናለን።
ጥያቄ ጠይቅ
ዕድገትህና ውልደትህን ትነግረን [ታዋቂ ስለሆነ ሲወለድ የነበረውን ሁሉ በደንብ ያስታውሳል እንደሌላው ፉዞ አይደለም]
ምን ወደዚህ ሥራ ገፋፋህ
በቅርቡ የሠራኸው ሥራ ላይ እንዲህ ይባላል እውነት ነው
አግብተኸል ለምን?
በቅርቡ ውጭ አገር ሄደህ ነበር እንዴት ነው ጉዞው።
ምን ይሰማሃል [ሙቀት ካለ አናፍስለት]
ወደፊት ምን አስበሃል
ጨርሰናል ወደሚቀጥለው ፕሮግራም ስፖንሰሮች ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንመለሳለን የሚል ማስታወቂያ በኋላ ይዘርዘሩ
. . . .
ቀጣይ ፕሮግራም
አሁን ደግሞ የምንገኘው ከታመመው ከእገሌ ቤት ነው። [ላገር ያለውን ፋይዳ ዘርዝር/ ዘርዝሪ] ለምሳሌ፦ [ለበርካታ ዓመታት ዘፍኗል፣ በመድረክ ተውኗል፣ ጋዜጠኛ ነበር፣ እግር ኳስ ተጫዋች ነበር ወዘተ]
በድጋሚ ስፖንሰሮችን አስተዋውቅ
ምናምን ቢራ
ምንትሶ ውሃ ወዘተ
አብራችሁን ስለቆያችሁ በጣም እናመሰግናለን። በሚቀጥለውም ዓመት በዓላችሁን ሐዘን ቤት ለማስመሰል ያለንን ቁርጠኛ አቋም ከወዲሁ እየገለጽን ለመላው የእንትን ተከታዮች መልካም በዓል በድጋሚ በመመኘት ፕሮግራምችንን በዚሁ እናጠናቅቃለን።
[ክላይ ካለው ፕሮግራም ላይ መጠነኛ የቅርጽና የአቀራረብ ለውጥ ማድረግ ይቻላል። ዋናው ቁምነገር ግን በየቤታቸው በግ፣ በሬ ዶሮ ወዘተ ጨፍጭፈው የበሉ ተመልካቾች የበሉት ብቻቸውን ስለሆነ ኃጢያተኛ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይገባል። በክፋታቸውም ሲሆን ተጸጽተው ሆነ በሌላ አዝነው በማናቸውም መልኩ እንዲያለቅሱ ማድረግ ከተቻለ የፕሮግራሙን ስኬት ያሳያል]።

No comments:

Post a Comment