(ያልተከሸነ ረቂቅ ጽሑፍ)
ለአብዛኛው አንኮ የኛ ትውልድ Facebook ላይ ያለው ቁምነገር በአጭሩ እንዲህ ነው፦
"እይ፥ ተመልከት ሕይወቴ ካንተ የተሻለ ነው። ምንም ልጻፍ ምን ፣ ሳትወድ በግድህ አንብብ ! እኔ ካንተ የተሻለ አውቃለሁ። ይኼን እውነት ማለትም እኔ ካንተ የተሻለ እንደማውቅ አንተም አሳምረህ ታውቃለህ። አይደለም ብለህ ግን አንዲት ቃል ትንፍሽ ብትል እስከ ዘር ማንዘርህ አጥረግርጌ እሞልጭኸለሁ።" በሚል ጠብ ያለሽ በዳቦ ጭብጥ የተሞላ ዘመናዊ ታዳሚውን አሳታፊ ጉራና ሽፍጥ የተሞላ መደዴ ተውኔት ነው።
እንደሚታወቀው የፌዝቡክ (ግድፈቱ ለነገር ነው) ፈልሳፊውና ባለቤት ከነጓደኞቹ ሐሳቡ የመጣላቸው በመጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ ከሚለቀለቁ ጽሑፎች እንደሆነ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። ይህ አባባል በቻይንኛ ፈስ-ቡክ (አሁንም ግድፈቱ ሆን ተብሎ ነው) ፖፖና ውኃ ፍሳሽ የሌለው በሳይበር ቴክኖሎጂ በየጉራንጉሩ የሚገባ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽም ነው ማለት ነው። ምን ለማለት ተፈልጎ ነው ፥ ብዙ ሰዎች በአደባባይ ማለት ወይም መናገር የማይፈልጉትን ወይም ማድረግ የማይችሉትን እንዲናገሩና እንዲያደርጉ ዕድል ተሰጥቶዋቸዋላ!
ፌዝቡክ ሆነ ፈስቡክ እንዲህ እንደ ዛሬው መለስተኛ ምናባዊ የጦር አውድማ ከመሆኑ በፊት፣ እንዲህ እንደ ዛሬው ራሱን የቻለ ስድስተኛ መንግሥት ከመሆኑ በፊት አጀማመሩ ላይ እንደ ዓላማ አድርጎ የተነሣው የተጠፋፉ ጓደኛሞችን ማገናኘት፣ ከዘመድ አዝማድ እንዲሁም ከባለንጀሮችና ዕውቂያዎች ጋር ወቅታዊ የግል መረጃን በመለዋወጥ እንደተቀራራቡ መቆየት የሚያስችል ቅንነት ያለው የሚመስል አዲስ የቴክኖሎጂ እመርታ ነበር። (ድርጅቱ የሰዎችን ገመና እየሸጠ ድንቡሎ ግብር ሳይከፍል ቢሊዮኔር መሆን መቻሉ ምሥጢር ለጊዜው ይቆይልን።)
መተግበሪያው ሳይውል ሳያድር ግን እንደ ፔን ፍሬንድ የመሳሰሉ ጥንታዊ ከአዲስ ሰው ጋር መተዋወቂያ መድረኮችን ሁሉ በመተካት፣ በቅፅበት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጓደኛ ተብዬ የፌዝቡክ ጀሌዎችን ማፍራት ከማስቻሉ ባሻገር እንደ ሜም፣ ጥቅሳጥቅስ የመሳሰሉ ፈጣን መዝናኛና መማማሪያዎችን በማካተት እንደ ሪያሊቲ ሾው ሁሉ ሰው ሲዘለፍ ሲሸወድ ወዘተ ማሳየት ከመቻሉ ጋር ተይይዞ ከመዝናኛነትም አልፎ ወደ ሱስነት ደረጃ ከፍ በሚል ሁኔታ የዘመኑ የሰው ልጅ አንዱና ዋንኛ መገለጫ መሆን የሚችልበት ደረጃ በፍጥነት በመሸጋገር ላይ ነው።
እኔ ፌስቡክ አልጠቀምም የሚሉ ሰዎች በተለያየ መንገድ አልጠቀምም ቢሉም አጮልቀው የሚያዩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከናካቴው ምንም የሌሉበትም ቢሆኑ እንኳ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የፈስቡክ ተፅእኖ ሰለባ ናቸው። ሐሰተኛ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ጠቅላላው የፌስቡክ ተጠቃሚ በዓለም ከሁለት ቢሊዮን በላይ እንደሚሆኑ ልብ ካሉ ዘንዳ ከዓለም ሕዝብ ብዛት ነፍስ ያወቀው አንድ አራተኛው መጠቀሙን እግረ መንገድዎን ያስታውሱ።
የፈስቡክ ልክፍትና ሱሰኝነት እንዴት እንደሚጀምርና ካንዱ ወደ አንዱ እንዴት እንደሚጋባ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ገና እያጠኑት ያለ ሰፊ ምርምርና ጥናት የሚጠይቅ ዓለማችን በዚህ ዘመን የገጠማት የጋራ ማኅበራዊ ቀውስ ዋንኛ ምንጭ ነው።
የፀደይ አብዮት በመባል የሚታወቀው ሰደድ እሳት ቱኒዚያ ውስጥ በመሃመድ ቦአዚዚ ራስን ማቃጠል ሲነሣ ከአብዮቱ ጥንስስ ጀምሮ እስከ እንደ ሊቢያና ሶሪያን ሲያፈራርስ ፈስቡክ የአብዮቱ ዋንኛ ጦር መሣሪያ ነበር። በአሜሪካና የአውሮፓ ሃገራት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የነበረው ሚናም በዋዛ አይታይም። እዚህ ባገራችንም እነ ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ ምን እንደሠሩበት የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ፌስቡክ ለሰው ልጅ ይዞት የመጣው ገጸበረከት፦ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ፣ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ፣ ፍጥነት ያለው የመልእክት ትልልፍ ዘዴ መሆን መቻሉ አንዱና ዋንኛው ነው። በተረፈ የዘመኑ ሰው ትግሥት የምትባለውን እንደ መቅበሩ በተለያየ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምክንያት ቅንዝንዝ፣ ባለበት የማይረጋ፣ ችኩል ከመሆኑ ጋር የዚህ መተግበሪያ መፈጠር ሰኔና ሰኞ ሲገጣጠሙ ዓይነት ነገር ሆኗል።
በአጭሩ ሐተታ አይወድም ትውልዱና ጊዜው። ቁንፅል ነገር በልቶ ቁንፅል ነገር ይዞ ሩጫ (ፋስትፉድና ቪትስን እዚህ ላይ ልብ ይላሉ)። ምግባችን ፋስት ፉድ፣ ትምህርታችን ገለብ፣ ገለብ፣ ሥራችን ዝምብሎ ሩጫ ብቻ።
ፈስቡክ ጥሩ የሐሜት ሱስ መወጣጫም ነው። አንዱን ታዋቂ ወይም አንዷን ባለዝና ወርተራ ጠብቆ አፈር ድቤ ማብላት ቀላል ነው። ከዚህ በተረፈ የተለያየ ድብቅ ጥምን እና ነውርን ባደባባይ ማራመጃ መንገድም ነው ፌስቡክ። (ያው እንደሚታወቀው በሕፃናት ወሲብ ልክፍት የተለከፈ ወንጀለኛ፣ ከእንስሳት ጋር አጓጉል ድርጊት የሚፈጽም፣ የሰው ደም በማፍሰስ የሚረካ፣ ወዘተ እያለን ዘርዝረን አንጨርሰውም። የሰው ልጅ ድብቅ ሱስ ብዙ ነው ብለን እንለፈው)።
ዕብደት ማለት አንድ ተመሣሣይ ነገር እያደረጉ የተለየ ውጤት መጠበቅ መሆኑን ምሁራን ደጋግመው ተናግረውታል፤ እኛም ደጋግመን ሰምተነዋል። ምን ያክሎቻችን ምንም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ፋይዳ እንደሌለው እያወቅን እንጠቀምበታለን?
ዕብደት ብቻ አይደለም ያልሆንከውን መሆን ራሱ የዕብደት ጥግ መድረስ ምልክት ነው። ስንቱን ሐሳዊ ጋዜጠኛ፣ ሐሳዊ ሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ ሐሳዊ ብሔርተኛ፣ ሐሳዊ አፍቃሪ፣ ሐሳዊ የአካባቢ አየር ተቆርቋሪ፣ ሐሳዊ ፓሊስ መርማሪ፣ ሐሳዊ ፖለቲከኛ፣ ሐሳዊ ታሪክ ጸሐፊ፣ ሐሳዊ ዐቃቤ ቅርስ፣ ሐሳዊ ታቦት አንጋሽ፣ ሐሳዊ ፓስተር ሰባኪ፣ ሐሳዊ አገር አቅኚ ሐሳዊ ወዘተ ሲሆን አይተናል። ምን ያላየነው አለ? እዚህ ዕብዶችና ወሬኞች፣ ሥራ ፈቶችና አስመሳዮች ባጥለቀለቁት የተበላሸ ምናብ መንደር ምን የሌለ አለ?
ቁርስ፣ ምሳና እራታችንን የምንበላበት ምግብ ቤት፣ አዲስ ልብስና ጫማ የምናስመርቅበት ቡቲክ፣ ቪዛ የምናስመታበት ኬላ፣ በግና ዶሮ ተራ፣ ላልታመምነውን እንዳንታመም መክረው የሚያሟርቱብን፣ ቀን መቁጠሪያ (ዛሬ እንትን ነው ነገ እንትና እንኳን አደረሳችሁ መባበያ)፣ ሚስትን ወይም ባልን እቅፍ አድርገው ፎቶ ተነሥተው መገለጫ (ፕሮፋይል) አድርገው ከመሬት ተነሥተው ትነካውና ትነካትና የሚመስል ዓይነት ዛቻ የምናሰማበትና የምናይበት፣ የልጆች ዕድገት የምንዘግብበት፣ ትኩስ የወሬ ምንጭ፣ ነጻ ጋዜጣ፣ ለቅሶ ቤት፣ ሰርግ ቤት፣ መቀጣጠሪያ፣ መጀናጀኚያ፣ ፍርድ ሸንጎ፣ ሕፃናት ማዋለጃ ክፍል፣ ሆስፒታል፣ የጽድቅና ኩነኔ መመዝገቢያ ባሕረመዝገብ ይመስል የተሳለሙትን ደብር፣ ያደረጉትን በጎ ምግባር የምንከትብበት፣ እቃ የምናሻሽጥበት፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ የባለሥልጣን ሹም ሽር የምናደርግበት . . . ምን የማይባል፣ ምን የማይደረግ ነገር አለ እዚህ መንደር? ዓለምን እንደ መርካቶ ብናስባት ምናለሽ ተራ ነው በአጭሩ ፌስቡክ።
ፌስቡክ ዕልም ያለ የቀለጠው መንደር ሆኗል። እዚህ መንደር ያገር ሽማግሌ፣ የሃይማኖት አባት፣ ታላቅ ታናሽ፣ መሪ ተመሪ፣ ዳኛ፣ ፖሊስ የሚባል ነገር የለም። በራሱ ሕግ፣ በራሱ ቴምፖ፣ በራሱ ዜማ ስልት፣ በራሱ ሥርዓት ይመራል።
ለማንኛውም ወዳጄ ልቤ ከዚህ እንደ ስሙ ፌዝቡክ ነውና ብዙ አትጠብቅ። ፈስቡክ ዳቦ አይሆንም። ለወሬ የለው ፍሬ ለአበባ . . . ይባል የለ ከነተረቱ። ዋዛና ፈዛዛም ሲበዙ ቤት ሊያፈርሱ ይችላሉና ቆጠብ ማለቱ ለሁሉም ሳይበጅ አይቀርም። ዳይ ወደ ሥራ። ሥራ ባይኖር እንኳ አንበብ ነገ የምትመነዝረውን ሀብት ይሰጥሃል።

ከሣቴ ብርሃን ቡሩህ በዕለተ ማርያም የመጋቢቷ (2019)