Wednesday, March 7, 2018

Boats and Birds by Gregory and the Hawk in Amharic

                                                                        ጀልባዋና አዕዋፍ
 
ለእኔ ኮከቤ ብትሆኚ
ሰማይሽ እሆናለሁ ላንቺ
ከኔ በታች ተደብቀሽ ሰርክ ማታ ድምቀሽ እንድትወጪ
እኔ ድብን ብዬ ስከስል ስጠቆር
ብርሃንሽ ገና ወጥቶ ልብን ሁሉ እንዲቆጣጠር
አንቺ እንድታበሪ እጠፋለሁ ላንቺ
አንቺ እንድታበሪ እጠፋለሁ ላንቺ
ካሻሽ ግን እንደ መንኮራኩር መመንጠቅ ከኔ ርቆ መሄድ
ላትመለሺ ብትሄጅ አግኝተሽ ሌላ ፍኖተ ሃሊብ፣ ሌላ የሚወደድ
ከዚህ በጣም ርቆ የሚገኝ ብዙ የሚበሩበት ሰማይ
ጣፍጦኝ እንዳጣጣም የፍቅርሽን ስቃይ
የኮከብሽን ብናኝ ብቻ አደራ እንደ ማስታወሻ ተይው እኔ ጋራ
አንቺ የኔ ታንኳ ብትሆኚ
እሆናለሁ ያንቺ ባሕር
ጥልቅ ንፁሕ ሰማያዊ፣ ውስጡ የሚያጓጓ
የሚፈስ የሚወርድ ቀስ ብሎ እየተንጓጓ
በስስ ነፋስ ቀስ ብዬ ተገፍቼ
አንቺን ነጻ ለማድረግ እኖራለሁ ላንቺ
አንቺን ነጻ ለማድረግ እኖራለሁ ላንቺ
ካሻሽ ግን አሁንም ወደ ምዕራብ ትችያለሽ መቅዘፍ
ከዓይኔ እስክትጠፉ ርቀሽ መሄድ አድማሱን ጥሰሽ ማለፍ
ከዚህ በጣም ርቀሽ መሄድ የፈለግሽ ለታ
የባሕር ዳርቻዎቹ ሰፊ ከሆኑበት ቦታ
የታንኳሽን ጭራፊ ብቻ ተዪልኝ ለኔ ለልቤ ትዝታ
ለእኔ ኮከቤ ብትሆኚ
ሰማይሽ እሆናለሁ ላንቺ
ከኔ በታች ተደብቀሽ ሰርክ ማታ ደምቀሽ እንድትወጪ
እኔ ድብን ብዬ ስከስል ስጠቆር
ብርሃንሽ ገና ወጥቶ ልብን ሁሉ እንዲቆጣጠር
አንቺ እንድታበሪ እጠፋለሁ ላንቺ
አንቺ እንድታበሪ እጠፋለሁ ላንቺ
ካሻሽ ግን እንደ መንኮራኩር መመንጠቅ ከኔ ርቆ መሄድ
ላትመለሺ ብትሄጅ አግኝተሽ ሌላ ፍኖተ ሃሊብ፣ ሌላ የሚወደድ
ከዚህ በጣም ርቆ የሚገኝ ብዙ የሚበሩበት ሰማይ
ጣፍጦኝ እንዳጣጣም የፍቅርሽን ስቃይ
የኮከብሽን ብናኝ ብቻ አደራ እንደ ማስታወሻ ተይው እኔ ጋራ
[በግሪጎሪ ኤንድ ዘ ሃውክ ተጽፎ ከተዘፈነ ዘፈን ላይ ወደ አማርኛ የተመለሰ - ብሩክ በየነ ለራሴ በልደቴ ቀን 2009]
Boats and Birds
If you'll be my star 
I'll be your sky 
You can hide underneath me and come out at night 
When I turn jet black 
And you show off your light 
I live to let you shine 
I live to let you shine
But you can skyrocket away from me 
And never come back if you find another galaxy 
Far from here with more room to fly 
Just leave me your stardust to remember you by
If you'll be my boat 
I'll be your sea 
A depth of pure blue just to probe curiosity 
Ebbing and flowing 
And pushed by a breeze 
I live to make you free 
I live to make you free
But you can set sail to the west if you want to 
And pass the horizon, 'til I can't even see you 
Far from here 
Where the beaches are wide 
Just leave me your wake to remember you by
If you'll be my star 
I'll be your sky 
You can hide underneath me and come out at night 
When I turn jet black 
And you show off your light 
I live to let you shine 
I live to let you shine
But you can skyrocket away from me 
And never come back if you find another galaxy 
Far from here with more room to fly 
Just leave me your stardust to remember you by
Stardust to remember you by
[Song written and sang by Gregory and the Hawk]

Tuesday, March 6, 2018

እንትን



እንትኖቼ! የገረመኝ ይኼ እንትን ነው። "እንትን" ብሎ ዐማርኛ "እንትን" ለማለት ተፈልጎ "እንትን" የሚል ትርጉም ተሰጥቶት "እንትን" ሰምቶ "እንትን" እንዳያደረግ "እንትን" እስከሚሆን ድረስ "እንትን" አለማድረግ "እንትንነት" ሳይሆን አይቀርም። በሉ እንግዲህ መልካም እንትን! ወይ እንትን አለች እንትን. . .

Wednesday, February 28, 2018

አምቡላንስ

አምቡላንስ መሄዱ እያለ ዋይ ዋይ
መቼ ለራሱ ሆኖ የበዛበት ስቃይ
የራሱ አርጎት እንጂ የሰውን ጉዳይ
እሪ ማለቱ እንዲያ በጎዳና ባደባባይ

Tuesday, February 27, 2018

ምንተስኖት




(የፋኖ እዚህ ምን አመጣው ቊጥር ፪)
ብርንዶ ቆራጩ፣ ግብርም ቀራጩ
ወርቅ ባሌስትራ አድርጊ ቀጥቃጩ
ጫኝና አውራጅ ሿሚና ሻሪ
ገድሎ ቀባሪ፣ ፈቺና አሣሪ
ራስህ ከሳሽ ራስህ መርማሪ
አንተው አስተማሪ፣ አንተው ተማሪ
ሲልህ ኮማንደር ሲልህ ደግሞ ዶክተር
አያልቅብህ ማዕረግ ክቡር ፕሮፌሰር
ካምቦሎጆ አርቢትር ችሎት ደግሞ ዳኛ
የሰው ቅን አሳቢ ድንበር የለሽ አርበኛ
ሲሻህ ዐቃቤ ሕግ፣ ሲሻህ ዐቃቤ ንዋይ
ከሊቀ ጳጳሱም በላይ ረቂቅ ኤልሻዳይ
ለሙዕሚኑ ሟች ከሙፍቲውም በላይ
የጠቅላዮች ሁሉ ጠቅላይ
እየታየህ የማትታይ፣
ሁሉን ግን የምታይ
አውራጅ ሰቃይ፣
ሰውን እንደ ብቅል አብቃይ
ሲሻህ ደግሞ እንደ ተህዋስ በካይ
ቢራ ጠማቂ ኢንጂነር፣ አንባቢ ጋዜጠኛ
አቻ የሌለህ አትሌት፣ የምንም አንደኛ
የከያኒያኑ ቁንጮ፣ ድምፀ-መረዋ ጓዴ
ምንተስኖት ያልኩህ የማታጣ ዘዴ
አስመጪና ላኪው፣ ቱጃሩ ነጋዴ
ገብተህ ካንጀት ከሆዴ
ሥጋ የምትበልት በሁዳዴ
የጋኔል ታናሽ ወንድም
አንተ አይደለህ እንዴ?
ለካቲት ፩፮ (ኪዳነ ምህረት) ፳፲፯

ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?





ግራ አጋቢ ነው ዘንድሮ የፅጋቡ ነገር
ጤፍ ቆልቶ ምላሱ ወርቅ ይሠራል ካፈር
ማዕረግና መመረግ ሆሄ ተምታቶ ከዛ ታች ሠፈር
እንደ ጭስ ሾልኮ ወጥቶ ከላይ፣ ሲገን ደፋር ባገር
ጫንቃው ተሸክሞ ዲሞፍተር፣ ደፍተር ሳይዝ ጉያው
 ወሽቆ ክፋቱን በብብቱ፣ ሳያነሣ ጣቱን ከቃታው
እንዴት ነው ተማሪ ቤት ገብቶ ትምርት ያማረው ?
እና ጥያቄው. . .
ባለዲሞፍተር ሺ ጊዜ ቢማር ቢመራመር
ምን ይሆናል? ዶክተር ወይስ ዶፍ-የጠር?
እዛ እንጃ !
ካረገው ሳንጃ !
እዛ እንጃ እንጂ
አስረግጦ ፈንጂ !
ፋኖ እዚህ ምን አማረው ?
ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?
እምቧይ ግን ላይሆን ሌላ፣ ላይጠፋ ማንነቱ
ካብን እሠራ ብሎ ጭራሽ ካብ እብስ ማለቱ
ዕውር ቢጤውን ሊመራ ደፍሮ መነሣቱ
ባንድ ጊዜ እኮ ሆነ፣ አምስት ጊዜ ጥፋቱ !
አቅልን ነስቶ
ልክ አሳጥቶ
ያለቅጥ ሲያቅበጠብጥ
ልብን የሳበጠ ነፍጥ
አንጎል መጦ ሲያናፍጥ
አንጋች ያኔ በባዶ እግር የረገጠውን ኮረኮንች
መጫሚያ ሲያግኝ ቢረግጠው መች ሊሰለች ?
እዛ እንጃ !
ካረገው ሳንጃ !
እዛ እንጃ እንጂ
አስረግጦ ፈንጂ !
ፋኖ እዚህ ምን አማረው ?
ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?
መታሰቢያነቱ በዘመኑ ጉዶች እጅ ሰጥተው ለጀዘቡ፣ ማንነታቸው ለጠፋ ምስኪን የቀድሞ ዘመን ምሁራን - ታህሳስ ፮፣ ፳፲፩፯

Thursday, February 22, 2018

አጉል እምነት ወይስ . . .?




ነውር የሆኑ ወይም ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች
1.      ግራ መዳፍን ካሳከከህ ገንዘብ ታገኛለህ፤ ቀኙን ከሆነ ደግሞ ገንዘብ ታወጣለህ።
2.     ቡና ወይም ሻይ ስትጠጣ ስኳር ከግራ ወደ ቀኝ የምታማስል ሰው ከሆንክ ገንዘብ አጥፊ፣ በታኝ ነህ በተቃራኒው የምታማስል ከሆነ ማለትም ከቀኝ ወደ ግራ (ወደ ውስጥ ወይም ወደ ራስህ አቅጣጫ) የምታማስል ከሆነ ገንዘብ ሰብሳቢ፣ ቆጣቢ፣ ወይም አሳዳጅ ነህ።
3.     ሙቀጫ ላይ መቀመጥ አጎትን ወይም የቅርብ ዘመድን ይገላል።
4.     ማታ ቤት አይጠረግም። አለበለዚያ የቤቱ ሲሳይ ተጠርጎ ይሄዳል።
5.     ማታ ማታ ጥፍር አይቆረጥም፣ የሚወዱት የቅርብ ሰው ይሞታል።
6.     ሳሙና መቀባበል የአንዱን ሲሳይ ወይም መጥፎ ዕድል ከአንዱ ወደ አንዱ እንዲተላለፍ ያደርጋል።
7.     እንጀራ፣ ልጅ፣ ከብት ብዛታቸው ለሰው አይነገርም። ብዛቱን ቆጥሮ የተናገረ መዓት ይመጣበታል።
8.     የልደታ ቀን ቤቱ ሙሉ የሆነ ወሩን ሙሉ ቤቱ ሙሉ ይሆናል። ልደታ ቀን ወጪ የሚያወጣ ሰው ወሩን ሙሉ ወጪ ሲያወጣ ይከርማል።
9.     ዘነዘና መቀባበል መጥፎ ምልክት ነው። ያጨካክናል።
10.    ከመሸ ለጎረቤት ጨው፣ በርበሬ፣ ክብሪት ማዋስ መጥፎ ነው። ለዚያኛው ቤት እሳት እንደ መስደድ ይቆጠራል።
11.     ቢላ በስለቱ ለሰው ማቀበል መጥፎ ነው። ከተሳሳትክ በአፍንጫው ወዲያው መሬት መውጋት አለብህ።
12.    እርጉዝ ሴት ድንጋይ ላይ መቀመጥ የለባትም። የምትወልደው ሰው አይሆንም።
13.    ቃሪያን ሁለት ቦታ ከፍሎ ተካፍሎ መብላት ነውር ነው፤ ያቆራርጣል።

የጥሩ ዕድል ምልክቶች ወይም የመጥፎ ነገር ምልኪዎች
1.      ቤት ውስጥ አይጥ ከገባ ምቀኛ ሰው ቤትህን አይቶታል ማለት ነው።
2.     ውሻ ሌሊት ካላዘነ ሰፈር ውስጥ የሆነ ሰው ይሞታል።
3.     ቡና ሲቀዳ አረፋ ከሠራ የተቀዳለት ሰው ሲሳይ አለው፣ ቀኑ የተቃና ነው፣ ገንዘብ ያገኛል ማለት ነው።
4.     ዓይን ቆብ እርግብግብ ካለ የጠፋ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ወይም ሩቅ አገር ያለን ሰው በቅርቡ ታያለህ።
5.     ቤት ውስጥ የጫማ ሶል ተገልብጦ በሶሉ በኩል መሬት ላይ መጣል የለበትም። መጥፎ ነገር በዚያ ቤት ውስጥ ያጋጥማል።