Tuesday, February 27, 2018

ምንተስኖት




(የፋኖ እዚህ ምን አመጣው ቊጥር ፪)
ብርንዶ ቆራጩ፣ ግብርም ቀራጩ
ወርቅ ባሌስትራ አድርጊ ቀጥቃጩ
ጫኝና አውራጅ ሿሚና ሻሪ
ገድሎ ቀባሪ፣ ፈቺና አሣሪ
ራስህ ከሳሽ ራስህ መርማሪ
አንተው አስተማሪ፣ አንተው ተማሪ
ሲልህ ኮማንደር ሲልህ ደግሞ ዶክተር
አያልቅብህ ማዕረግ ክቡር ፕሮፌሰር
ካምቦሎጆ አርቢትር ችሎት ደግሞ ዳኛ
የሰው ቅን አሳቢ ድንበር የለሽ አርበኛ
ሲሻህ ዐቃቤ ሕግ፣ ሲሻህ ዐቃቤ ንዋይ
ከሊቀ ጳጳሱም በላይ ረቂቅ ኤልሻዳይ
ለሙዕሚኑ ሟች ከሙፍቲውም በላይ
የጠቅላዮች ሁሉ ጠቅላይ
እየታየህ የማትታይ፣
ሁሉን ግን የምታይ
አውራጅ ሰቃይ፣
ሰውን እንደ ብቅል አብቃይ
ሲሻህ ደግሞ እንደ ተህዋስ በካይ
ቢራ ጠማቂ ኢንጂነር፣ አንባቢ ጋዜጠኛ
አቻ የሌለህ አትሌት፣ የምንም አንደኛ
የከያኒያኑ ቁንጮ፣ ድምፀ-መረዋ ጓዴ
ምንተስኖት ያልኩህ የማታጣ ዘዴ
አስመጪና ላኪው፣ ቱጃሩ ነጋዴ
ገብተህ ካንጀት ከሆዴ
ሥጋ የምትበልት በሁዳዴ
የጋኔል ታናሽ ወንድም
አንተ አይደለህ እንዴ?
ለካቲት ፩፮ (ኪዳነ ምህረት) ፳፲፯

No comments:

Post a Comment