ተረት ተረት
የላም በረት
አይጥ ትከምርህ እመመሩ መሬት
ከዕለታት አንድ ቀን ከጓጉንቸር ወገን የምትወለድ በምድርም በውሃም የምትኖር ዥራት የሌላት እንቁራሪት የሚሏት እቡይ ጥላ ቢስ ፍጥረት ነበረች። ዝሆንን ትልቅ ወንዝ ሲሻገር አግኝታው እባክህ በጀርባህ ተሸክመህ አሻግረኝ አለችው። ዝሆንም በየዋህነት እግረመንገዴን ይዤያት ብሻገር ምን ክፋት አለው ይልና በጀርባው አስቀምጧት ወንዙን አሻገራት።
ከባሕሩ ዳርቻ ስትደርስ ግን የጓጉንቸር ዘር ያው ጓጉንቸር ነችና ልቧ ክፋት ዐሰበ። በጫንቃው ተሸክሟት ስለነበረም የበላይነትም ተሰማት። እሱን እሱን የሆነች መምሰል ብቻ ሳይሆን እንደልቧ ልታዘው የምትችል ሁሉ መሰላት። ይህ ብቻ አይደለም ወይዘሪት እንቁራሪት ውሃ አብዝቼ ብጠጣ እሱን ራሱ አክላለሁ ብላ አሰበች።
አስባም አላቆመች ያገር ውሃ ልጋ፣ ልጋ ጠጣችና ተሰንጥቃ ሞተች። በዚህም አባቶች እንቁራሪት ዝሆን አክላለሁ ብላ ተሰንጥቃ ሞተች አሉ ይባላል።
ተረቴን መልሱ
አፌን በዳቦ አብሱ።
መልመጃ ጥያቄ፦
በዘመናችን ማን ይሆን ዝሆኑ ማን ትሆን እንቁራሪቷ?
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
በዕለተ 13 ጥር 2019 (በራስ አቆጣጠር)
No comments:
Post a Comment