Tuesday, January 29, 2019

ነገረ ማፊያ እና የማፊያ ሥራ


ነገረ ማፊያ እና የማፊያ ሥራ
ዝግጅት በብሩክ በየነ
ማፊያ ምንድን ነው?
በየጎዳናው ጥጋጥግ ከሚሸጥ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ድረስ ሁሉንም ነገር “ማፊያ” ተቆጣጥሮታል። የማፊያ አለቆች በፊልሞችና በቴሌቭዥን ጣቢያዎች ስማቸውና ድርጊታቸው ገኖ ሲቀርብ ኖሯል፤ ዛሬም በተለያየ መንገድ እየቀረበ ነው። ዛሬም ሕግ አስከባሪ አካላት እነዚህን የድብቁ ዓለም ሰዎችን ያሳድዳሉ። የጎብዝ አለቆቹ በየራሳቸው ሕገወጥ ፍርድ ቤት አንዳቸው ለአንዳቸው የሞት ፍርድ እርስ በርስ ተፈራርደው፣ የሞት ፍርዱን የሚያስፈጽሙላቸውን አስፈጻሚ ቅጥረኞች ሰደው እየተፈላለጉ፤ እርስ በርስም እየተጠፋፉ አሁንም ድረስ እየኖሩ ይገኛሉ። የወንበዴ መንጋ አለቆች ብዙውን ጊዜ አመጽ የተሞላ አጭር ዕድሜ ብቻ በዚህች ዓለም ይኖራሉ። በድብቁ “የማፊያ” ዓለም ውስጥ አንድ ነገር ብቻ የጋራ ጉዳይ ነው፤ ገንዘብ። እንዲህም ሆኖ ግን ሁላችን ልናውቃቸው የሚገቡን የዚህ ዓለም ምሥጢራዊ ሥነ ምግባር ደንብ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ እጅግ የተወሳሰቡ የውስጥ ደንቦች እና የተወሳሰቡ የቤተሰብ ታማኝነትና የደም ትስስሮች አሉ።
ይህ መጽሐፍ ሰዎች እንዴት ወደ “ማፊያው” ድብቅ ዓለም እንደሚገቡ እና “ማፊያው” ምን እንደሚያደርግ እንዲሁም ሕግ አስከባሪው አካል የዚህን ድብቅ መንግሥት እንቅስቃሴ ለማስቆም ከፍጥረቱ እስከ ዛሬው ታሪኩ ያደረገውን ጥረት ለመቃኘት ይሞክራል። በዚህ ሂደት ውስጥ እጅግ ገዝፈው የወጡትን የገሃዱንና የድብቁን ዓለም የተለያየ ሚና ያላቸውን ሰዎች ታሪክ እና የታሪክ ክስተቶች እንመለከታለን።
“ማፊያ”፤ አጠቃላይ ዕይታ
ዛሬ፣ ዛሬ “ማፊያ” የሚለው ቃል በአጠቃላይ አነጋገር ለማናቸውም “የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን” መገለጫ በመሆን በማገልገል ላይ ያለ ቃል ነው። አንዳንድ ጊዜ ከወንጀል ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የሌላቸውን ቡድኖችንም ለመግለፅ ቃሉ ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህ መጽሐፍ በተለምዶ “ማፊያ” ስለሚባለው ቃል ብቻ ትኩረት እናደርጋለን፤ ይኸውም ከጣልያን ወይም ከሲሲሊ የተጀመረውን የተደራጀ ውንብድናን እንመለከታለን።
በተደራጀ ውንብድና ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው አባላት እስከታች የወንጀሉ ቤተሰብ አባላት ድረስ የሚወርድ ትእዛዝ እንዲሰጡ የሚያስችላቸው ራሱን የቻለ የሥልጣን ተዋረድ ሠንሠለት አለ። “ማፊያ” ሲባል አንድ ብቻ ቡድን ወይም ጋንግ አይደለም። ይልቁንስ በሆነ ጊዜ ላይ እርስ በርስ የለየለት ደም አፋሳሽ የከተማ ጦርነት ያደረጉ ብዙ ሰው ያለቀባቸውን ውጊያዎች የመሩ በርካታ በጎበዝ አለቆች የሚመሩ በርካታ ቤተሰቦችን በአንድ ላይ የያዘ ስያሜ ነው። ደግሞ ሌላ ጊዜ፣ በሌላ ሁኔታ የሁሉንም ቤተሰቦች ጥቅም በሚነካ መልኩ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ ሲባል አንድ ላይ ሆኖም ግን በተናጠል “ኮሚሽን” ማግኘትን በተመለከተ የጋራ ውሳኔን ሲሰጡና ሲያስፈጽሙም ሊስተዋሉ ይችላሉ። ሆኖም ግን አብዛኛውን ጊዜ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታዩ “የማፊያው ሥርወ መንግሥት” ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሆነ የሃይማኖት ድርጅትነት ጸባይ ሆነ ደጋፊነት እንደሌለው ሁሉም “የማፊያ” ወገኖች በውስጠ ታዋቂነት ይስማሙበታል። አብዛኛዎቹ የማፊያ ድርጅቶች ምንጫቸው ከጣልያን እንደመዘዙ፤ በርካታዎቹ “ማፊዮሶዎች” ሃይማኖታቸው ካቶሊክ ቢሆንም አንድ ሰው “የማፊያ አባል” ወይም “ወታደር” ሆኖ ሲመለመል ቃል ኪዳን ሲገባ “ማፊያ” ከሥጋ ቤተሰቦቹ ሆነ ከእግዚአብሔር እንደሚበልጥበጥ አስረግጦ ቃል በመግባት ሥራውን እንዲጀምር ይደረጋል።

“ማፊያ” ነክ ቃላት
·         ላ ኮዛ ኖስትራ (La Cosa Nostra) - ኮዛ ኖስትራ (cosa nostra) የሚለው ቃል ከጣልያኛ የመጣ ሆኖ ወደ አማርኛ በቀጥታ ሲተረጎም "የእኛ ነገር" የሚል ጥሬ ትርጉም የሚሰጥ ቃል ሆኖ በመጀመሪያ ቃሉ ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምር ትርጉሙ በሲሲሊ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የተደራጁ ወንጀለኞች አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ የሚገልፅ ቃል ነበር። ማፊያዎች ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ፣ የኤፍቢአይ የደኅንነት ሠራተኞች ቃሉን በተጠለፉ የስልክ ንግግሮች መካከል ሲነገር ሊሰሙት ቻሉ። እነርሱም በፊናቸው ላ ኮዛ ኖስትራ የሚለውን (በሰዋሰው ዓይን ሲታይ ስህተት የሆነውን) ቃል ማፊያን ለመግለፅ ይጠቀሙበት ጀመሩ። በጊዜ ሂደት፣ ላ ኮዛ ኖስትራ በተለይ የአማሪካ ማፊዮሶዎችን መጀመሪያ ከነበሩብት ከዱሮው ድብቁ ዓለም ማፊያዎች ለመለየት በቀጥታ ጥቅም ላይ ይውል ጀመር።
·         ኦሜረታ - Omerta (ኦሜረታ) ጸጥ ማሰኘት ወይም ጸጥታ የሚል ትርጉም ያለው የማፊያ ኮድ ነው።
·         የማፊያ አባል (ሜድ ማን (Made man)) - ይህ በይፋዊ መንገድ ወደ ማፊያ ቤተሰብ እንዲቀላቀል የተደረገ ግለሰብ ነው።
·         ካቦ - ካፖ (capo) በመጀመሪያ በሲሲሊ ለሚገኘው ቤተሰብ አውራ ነበር። አሁን ላይ ግን ካቦ ሲባል የቤተሰቡን አውራ በዋንኛነት እንደ ቀኝ እጅ ሆኖ የሚያገለግለው ምክትል ኃላፊ ወይም ሌፍተናንት ነው።
·         ቤተሰብ - እያንዳንዱ በማፊያ ውስጥ ያለ የወሮበላ ቡድን ወይም ጋንግ ቤተሰብ በመባል ይታወቃል። በቤተሰብ ውስጥ ያለው ሁሉም ሰው የግድ በሥጋ ዝምድና የተሳሰረ መሆን የለበትም። ሆኖም ግን በአንድ የማፊያ ጋንግ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ አባላት እንደ አባት ወይም እንደ ወንድም ማእረግ ተሰጥቶዋቸው በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የጭፍራ አለቆቹ የቅርብ ወይም የሩቅ ዘመድ መሆን የመቻላቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።
·         ብልጡ ሰው (Wiseguy) - ይህ ከማፊያ ጋር በአንዳች መልኩ ግንኙነት ያለው ሰው ነው።
የላ ኮዛ ኖስትራ መዋቅር
ከዚህ በታች የቀረበው መዋቅር በተለይ የላ ኮዛ ኖስትራን አደረጃጀት ያሳያል። ሌሎች ቡድኖች ተመሳሳይ መዋቅሮች ቢኖሯቸውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ትንሽ ለየት ሊሉ ይችሉ ይሆናል።
እያንዳንዱ ትልቅ ቡድን ቤተሰብ በመባል በሚታወቁ አነስተኛ በርካታ የወሮበላ ቡድኖች ወይም ጋንጎች የተዋቀረ ነው። በአንድ ቡድን ውስጥ የሚኖሩት የቤተሰቦች ብዛት ከዐሥር ቤተሰብ ያነሱም ከመቶ ቤተሰብ የበለጡም ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ አዲስ ቤተሰብ ወደ ጨዋታው መድረክ ሲመጣ በሌሎች ቤተሰቦች ኃላፊዎች በመጀመሪያ ዕውቅና ሊሰጠው እና ሊፈቀድለት ይገባል። ሆኖም በአንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎች አንድ ቡድን ከአንድ በፊት ከነበረ ቤተሰብ ተገንጥሎ ሊወጣ እና ኃይሉን በማጠናከር በጊዜ ሂደት እንደ አዲስ ቤተሰብ ሊታወቅ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እያንዳንዱ ቤተሰብ የየራሱ የሆነ የሚተዳደርበት ወይም በበላይነት የሚቆጣጠረው ራሱን የቻለ ሌላ ሊቀናቀነው የማይችል የራሱ የንግድ ሥራ ዓይነት አለው። እንዲህም ሆኖ ግን የማፊያ ቤተሰቦቹ ንግዶች እርስ በርስ ሊቀላቀሉና ወጥ የሆነ አንድ መጠነ ሰፊ ሽፋን ሊኖራቸውም ይችላል። ይህ ሲሆን በቤተሰቦቹ መካከል ያለው ቅርበትና ወዳጅነት እንዲሁም የሚሠራው ሥራ ተመሳሳይነት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የእያንዳንዱ ቤተሰብ መሪ አለቃ ወይም ዶን በመባል ይታወቃል። ሁሉም ከፍተኛ ውሳኔዎች የሚወሰኑት በዚህ አለቃ ወይም ዶን በሚባለው ሰው ይሆናል። በቤተሰቡ የሚገኘው ገንዘብ በቀጥታ ወደሱ ካዝና ይገባል። የአለቃው ሥልጣን በቤተሰብ መካከል የሚነሳ አለመግባባትን ለመፍታት እና ሁሉንም ሰው ሥርዓቱንና ደንቡ ጠብቆ መጓዝ እንዲችል ማድረግ ነው።
ከእያንዳንዱ አለቃ ሥር አንድ ዋና የበታች አለቃ አለ። ይህ ዋና የበታች አለቃ በሥልጣን ተዋረዱ ላይ ሁለተኛው ቁልፍ ሰው ነው። ሆኖም ግን ይህ ሰው የሚኖረው የሥልጣን መጠን ከአንዱ ቤተሰብ ከሌላኛው አንጻር ሲታይ የተለያየ ሊሆን ይችል ይሆናል። አንዳንድ ዋና የበታች አለቆች ዋናው አለቃ ሳይገባበት የተነሡ አለመግባባቶችን መፍታት ይቻላቸዋል። አንዳንዶች ኋላ ላይ ዋናውን አለቃ ሲያረጅ ወይም እስር ቤት የመግባት አደጋ ካጋጠመው ወዲያው መተካት በሚችሉበት ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተገሩ የሚዘጋጁ ይሆናሉ።
ከዋናው የበታች አለቃ ሥር እንደገና በርካታ ካቦዎች ይገኛሉ። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩት ካቦዎች ብዛት እንደ ቤተሰቡ ብዛት የሚወሰን ይሆናል። አንድ ካቦ እንደ ምክትል ወይም ሌፍተናንት ሆኖ ያገለግላል። እያንዳንዱ ካቦ የራሱ አነስተኛ ቤተሰብ በሥሩ የሚይዝ ይሆናል። እሱ ራሱ የሚያንቀሳቅሳቸው የተወሰኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች ይኖሩታል። የአንዱ ካቦ የግዛት ክልል በጂኦግራፊያዊ መንገድ የተከለለ ሊሆን ይችላል (ለአብነት ከ14ኛው ጎዳና በስተምዕራብ ያለ ሁሉ ለልዊ “ቁልፉ ሰው” ወይም “ዲባርቶሎ” (DiBartolo) የተከለለ) ወይም እሱ በሚሠራው የሥራ መደብ የተለየ (ማለትም “አልፎንዝ” (ቢግ አል ማጂዮሊ) ሕገወጥ ቁማርን የሚያስተዳድር) ሊሆን ይችላል። አንድ ስኬታማ ካቦ ስኬታማነቱ የሚለካው ለቤተሰቡ በሚያስገባው የገንዘብ መጠን ነው። እያንዳንዱ ካቦ በተመደበበት ክልል ወይም የሕገወጥ ንግድ ወንጀል ሠርቶ ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነውን ለራሱ ያስቀርና የተረፈውን ገንዘብ በቀጥታ ለዋናው የበታች አለቃ እና ለዋናው አለቃ ድርሻቸውን ያስተላልፋል።
“ቆሻሻው ሥራ” ወይም “ወንጀል ድርጊቱ” የሚሠራው በወታደሮች ነው። ወታደር ከማፊያ አባላት (ሜድ ሜን) መካከል ዝቅተኛው ማእረግ ያለው ግለሰብ ነው። ወታደሮች የቤተሰቡ አባላት ናቸው፤ ሆኖም ግን ያላቸው ሥልጣን ትንሽ እንደመሆኑ የሚያገኙትም ገንዘብ መጠን ያንኑ ያክል ያነሰ ነው። በአንድ ካቦ ሥር ያሉ ወታደሮች ብዛት በሌላኛው ካቦ ሥር ካሉ ወታደሮች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ የተለያየ ሊሆን ይችላል።
ከወታደሮች በተጨማሪ ማፊያዎች “ተባባሪዎችን” ይጠቀማሉ። ተባባሪዎች የማፊያ አባላት አይደሉም ሆኖም ግን በበርካታ የተለያዩ የወንጀል ድርጅት መዋቅሮች ውስጥ ከማፊያ ወታደሮች እና ካቦዎች ጋር በትብብር ይሠራሉ። አንድ ረዳት በሕዝብ መካከል የሚኖር ተራ ሰው ሆኖ ከተራ ቤት ሰርሳሪ ሌባ ወይም የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴ ጀምሮ እስከ ጠበቃ፣ የኢንቬስትመንት ባንክ ከፍተኛ ባለሙያ፣ የፖሊስ መኮንን ወይም ፖለቲከኛ ድረስ የተለያየ ሙያና ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች ሊወክል ይችላል።
በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኮንሲጀሌሪ (consigliere) የሚባል የሥልጣን ድርሻ ያለው ሰው አለ። ኮንሲጀሌሪው በቤተሰቡ የሥልጣን ተዋረድ ላይ አይካተትም። የሥራ ድርሻው ቤተሰቡን በአማካሪነት ማገልገል እና ለማንም ሳያዳላ ከግል ስሜት ወይም ከበቀል ስሜት ውጭ ፍትሐዊ ውሳኔን የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ይህ ሥልጣን የሚሰጠው ሰው በቤተሰቡ አባላት የሚመረጥ እንጂ በዋናው አለቃ የሚሾም ሰው አይደለም። ሆኖም ግን ኮንሲጀሌሪዎች አንዳንድ ጊዜ ሲሾሙ እና የመድልዎ ውሳኔ ሲሰጡ ሊታዩ ይችሉ ይሆናል።

የማፊያ ዲቪዝዮኖች
ማፊያ እንደ ማንኛውም ተራ ድርጅት ዓይነት ቁመና ያለው ድርጅት አይደለም። ማንም ይኼ ነው የሚባል ራሱን የቻለ የማፊያ አለቃ የለም። ከዚህ ይልቅ፣ ማፊያ የሚለው ቃል የዘር ግንዳቸውን ከወደ ጣሊያን ወይም ከሲሲሉ ለሚስቡ የወሮበላ (ጋንጊስተር) ማናቸውም ቡድኖች እንደ ዣንጥላ ሆኖ የሚያገለግል የጋራ ስያሜ ነው።
ሰፋ ባለ አነጋገር፣ በሚንቀሳቀሱባቸው ክልሎች ወይም ከመጡባቸው ክልሎ በመነሳት ተለይተው የታወቁ ትላልቅ አምስት የማፊያ ቡድኖች አሉ። አምስቱም ቡድኖች ዓለምን እንደ እንዝርት በሚያዞሩ የወንጀል ድርጊቶች (ኦፕሬሽኖች) ላይ እጃቸው አለበት። እንዲሁም በበርካታ ሃገራት ውስጥ የየራሳቸውን ወኪል ወንጀል ፈጻሚ ቡድኖች አቋቁመዋል። የሲሲሊው ማፊያ ምንጩ የሲሲሊ ደሴት ነች። የካሞራ ማፊያ በኔፕልስ የጀመረ ሲሆን የካላብሪያን ማፊያ መነሻው በጣሊያን ካላብሪያን ክልል ነው። በጣም በቅርቡ የተፈጠረው የሳክራ ኮሮና ዩኒታ ማፊያ ቡድን መነሻው የጣልያኑ ፑግሊያ ክልል ነው። በስተመጨረሻ፣ ላ ኮዛ ኖስትራ የአሜሪካ ማፊያ ቡድን ቢሆንም ታሪኩ ግን በቀጥታ ከሲሲሊ ኣና ሌሎች የጣልያን ቡድኖች ጋር ጋር የተያያዘ ነው።
የማፊያ ቤተሰቦችን በተመለከተ ይኼ ነው የሚባል ወጥ አሰያየም ዘዴ የለም። ማፊያ መጀመሪያ ሥራውን መሥራት ሲጀምር የነበሩ ቤተሰቦች እንደ መጡበት የጣሊያን ክልል ወይም ከተማ በመጠቀም ይጠሩ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ፣ የቤተሰቡ ስም በዋናው አለቃ ስም ሊለወጥ ይችላል፤ በተለይ ዋናው አለቃ ለረዥም ጊዜ የቆየ ወይም በጣም ኃይለኛ አለቃ ከነበረ። አምስቱ ታላላቅ የኒው ዮርክ ቤተሰቦች ስማቸውን ያገኙት በ1962 እና በ1963 የአሜሪካ ሴኔት ንዑስ ኮሚቴ ፊት የምሥክርነት ቃሉን ከሰጠው ጆ ቫላቺ ከሰጠው የምሥክርነት ቃል በመነሳት ስያሜያቸውን ያገኙ ናቸው። ቤተሰቦቹ ስማቸውን በወቅቱ ዋና አለቆቻቸው ከነበሩ ሰዎች አኳያ ያገኙ ሲሆን አንዱ ቤተሰብ ግን የነበረው አለቃ በመጀመሪያ የሁሉም ቤተሰቦች መለያ ነበረ። እነዚህ አምስቱ ቤተሰቦች ቦናኖ፣ ጄኖቬዝ፣ ጋምቢኖ፣ ሉቼዝ እና ፕሮፋሲ በመባል ይታወቃሉ። የፕሮፋሲ ቤተሰብ ከትንሽ ዓመታት በኋላ በጆሴፍ ኮሎምቦ ቤተሰብ የተተካ ሲሆን ይኸው ግለሰብ በጣም ዝነኛ ከመሆኑ የተነሣ ቤተሰቡ በስተመጨረሻ የኮሎምቦ ቤተሰብ በመባል ይታወቅ ጀመረ። በጋምቢኖ ቤተሰብ ላይ በጆን ጎቲ ቊጥጥር ሥር ሲወድቅ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞታል፤ ሆኖም ግን የጎቲ ቤተሰብ ከመባሉ በፊት ጎቲ በፖሊስ ቊጥጥር ሥር  ውሎ ማፊያን በካደው ሳሚ “ዘ ቡል” (በሬው) በሚባለው በግራቫኖ በተሰጠ የምሥክርነት ቃል ላይ በመመርኮዝ በተደራጀ ወንጀል እና ነፍስ ግድያ ጥፋተኛ ተብሎ ተፈርዶበታል።

አብዛኛዎቹ ሌሎች በአሜሪካ ያሉ ቤተሰቦች በሚንቀሳቀሱበት ከተማ ስም የሚጠሩ ናቸው። በመሆኑም የፊላዴልፊያ ቤተሰብ፣ የቡፋሎ ቤተሰብ፣ የክሌቭላንድ ቤተሰብ ወዘተ የመሳሰሉ ቤተሰቦች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ።

የማፊያ ምልመላ ሥነ ሥርዓት
ሰዎች እንዴት በማፊያ እንደሚመለመሉ እና የማፊያ አባል የሚደረጉበት ሥነ ሥርዓት ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት በምሥጢር ተይዞ ቆይቷል። በ1960ዎቹ መባቻ ላይ ከሴኔት ንዑስ ኮሚቴ ፊት የተሰጠው የጆ ቫላቺ የምሥክርነት ቃል በስውሩ ዓለም እንቅስቃሴ እና ቁመና ላይ አንዳች የብርሃን ጭላንጭል እንዲፈነጥቅ አድርጓል። እዚህ ላይ የተብራራው የማፊያ ምልመላ ሥነ ሥርዓት በሲሲሊ ማፊያ እና በአብዛኛዎቹ የአሜሪካ ማፊያ ቤተሰቦች ጥቅም ላይ የሚውለው የማፊያ የምልመላ ሥነ ሥርዓት ነው። በእስር ቤት ውስጥ እንዳለ መመልመል ወይም በጋንግ (ወሮበላ) ጦርነት ጊዜ በሚደረግ ፈጣን ምልመላ በመሳሰሉ ሁኔታዎች የምልመላ ሥነ ሥርዓቱ ዝርዝር ሂደት የተለያየ ሊሆን የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ።
በመጀመሪያ፣ ወደፊት የማፊያ አባል እንዲሆን የተመለመለው “ወሮበላ” ወይም “ጋንጊስተር” በቀላሉ “እንዲለብስ” ወይም “ልብሱን  ለብሶ እንዲዘጋጅ” ይነገረዋል። ወደ አንድ ማንም የማይኖርበት የተለየ ቦታ ይወሰድ እና ከዋናው አለቃ አጠገብ ከአንድ ረዥም ጠረጴዛ ፊት ለፊት እንዲቀመጥ ይደረጋል። በቦታው ያሉ ሌሎች ማፊዮሶዎች እጅ ለእጅ ይያያዙ እና የታማኝነት ቃል ኪዳናቸውን በቃላቸው ይወርዳሉ። ተመልማዩ ወታደር ይህን ጊዜ የሚቃጠል ወረቀት በእጅ መያዝ አለበት። በአንዳንድ ቤተሰቦች አዲሱ ምልምል ወታደር እንደ “ጡት አባቱ” ሆኖ በማፊያ የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ከሚመራው የማፊያ አለቃ ጋር እንዲጣመር ይደረጋል። ምልምሉ ወታደር ለቤተሰቡ ዕድሜ ልኩን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ አባል ሆኖ እንደሚያገለግል ቃል መግባት አለበት። ይህን ካደረገ በኋላ የጥይት ቃታ ከሚስብበት ጣቱ በመርፌ ተወግቶ ወይም በምላጭ ተቆርጦ ደም እንዲፈሰው ይደረጋል።
ሆኖም ግን የማፊያ አባል ለመሆን ቃለ መሃላ መፈጸምና የጣት ደምን ማንጠባጠብ ብቻ አይበቃም። የጣልያን ዝርያ ያለባቸው ሰዎች ብቻ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ይፈቀድላቸዋል። በአንዳንድ ቤተሰቦች ሁለቱም ወላጆች የግድ ጣልያናዊያን መሆን ያለባቸው ሲሆን በአንዳንድ ሌሎች ቤተሰቦች ግን አባትየው ብቻ ጣልያናዊ ከሆነ በቂ ነው። ወደፊት የማፊያ አባል የሚሆነው ዕጩ ገንዘብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥም ያለው መሆኑን ይህንንም ለማድረግ ወደ ኋላ የማይል ሰው መሆኑን ወይም ቢያንስ ሲታዘዝ ማናቸውንም የአመጽና የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የማያቅማማ ሰው መሆኑን ማረጋገጥ መቻል አለበት። ብዙውን ጊዜ፣ ወንጀለኛው ሰው ምልምል ወታደር መሆን ከመቻሉ በፊት ፈተና ማለፍ ይኖርበታል። ይህ ፈተና አብዛኛውን ጊዜ በነፍስ ግድያ ድርጊት ላይ በቀጥታ ተሳትፎ የማድረግ ፈተና እንደሆነ ወሬ ይወራል።
አንዳንድ የማፊያ አባላት የማፊያ አባል ወይም ሜድ ማን መሆን ከመቻላቸው በፊት መጋፈጥ ያለባቸው አንድ የመጨረሻ እንቅፋት ወይም ከባድ ፈተና አለ - ይኸውም ኮሚሽኑ ነው። በ1920ዎቹ እና 30ዎቹ በአሜሪካ ያሉት የማፊያ ቤተሰቦች ሁልጊዜ በሚቻል ደረጃ እርስ በርስ ጦርነት ላይ ነበሩ። ጠላቶቻቸው የሆኑ ቤተሰቦች እንደ ጠላት ለይተው እንዳይከታተሉዋቸው ለማድረግ እንዲችሉ ብዙውን ጊዜ በደርዘኖች የሚቆጠሩ አዳዲስ ወታደሮች ይመለምሉ ነበር። እነዚህ አዳዲስ ምልምል ወታደሮች የሌሎች ቤተሰቦች አባላትን በቀላሉ ሊደርሱባቸውና ሊያጠፏቸው ይችሉ ነበር። ይህንን ማስቆም እንዲቻል፣ ኮሚሽኑ ሁሉንም ዕጩ አባላት ስም ዝርዝር መጠየቅና ለሌሎች ቤተሰቦች ይህንኑ ዝርዝር ማደል ጀመረ። የማይታወቁ የቤተሰብ አባላትን ከማስወገድ በተጨማሪ ሌሎች ቤተሰቦች ችግር ናቸው ያሉዋቸውን ዕጩ ምልምሎች መንግሎ ለማጥፋት ለቤተሰብ አለቆቹ በተጨማሪ አስችሎዋቸዋል። እነዚያ ዕጩ ወታደሮች የማፊያ አባል ወይም ሜድ ሜን ከሆኑ በግለሰብ ደረጃ የነበሩ አለመግባባቶች የቤተሰብ ጦርነት ወደ የሚሆኑበት ደረጃ ሊሸጋገሩ ይችላሉ።
የማፊያ እንቅስቃሴዎች
የአንድ ማፊያ የመጨረሻ ግቡ ገንዘብ ማግኘት ነው። ቤተሰቦች ይህንን ግብ ለመምታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ። ከነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በጣም የተለመደው እና ለማድረግም ቀላል የሆነው አስፈራርቶ ገንዘብ መቀበል ነው። አስፈራርቶ ገንዘብ መቀበል ወይም extortion ሲባል ሰዎችን ባንድ የሆነ ዘዴ በማስፈራራት ገንዘባቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ የማድረግ የወንጀል ድርጊት ነው። ማፊያ የሚሰጠው “የጥበቃ አገልግሎት” ራሱን የቻለ ገንዘብ አስፈራርቶ መቀበያ ዘዴ ነው። አንዲት የሱቅ ባለቤትን ሱቋን ሊያወድሙ ወይም ቤተሰቧን ሊጎዱ ከሚችሉ ወንጀለኞች ጥበቃ እንዲደረግላት በየሳምንቱ $100 ዶላር እንድትከፍል ሊጠይቋት ይችላል። እውነታው ግን እንደዚያ የሚያደርጉት ወንጀለኞች ራሳቸው የማፊያው አባላት ናቸው።
ማፊያ በማናቸውም ሕገወጥ በሆነ እንቅስቃሴ ላይ በመሳተፍ ገንዘብ ያገኛል። ሕገወጥ ሸቀጦች እንደሚታወቀው ሁልጊዜም ቢሆን ውድ ከመሆናቸው ባሻገር ምንም ዓይነት ግብር አይከፈልባቸውም ብሎም ቊጥጥር አይደረግባቸውም። በዓመታት ሂደት፣ መጠጥ ተከልክሎ በነበረበት ዘመን አልኮል ንግድ ላይ በመሰማራት፣ ከዚያም በኋላ በአደንዛዥ ዕፅ ንግድ፣ ሴትኛ አዳሪነት እና ሕገወጥ ቁማር ላይ የማፊያ አለቆች ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፤ አሁንም በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።
አንዳንድ ጊዜ የቤት ስርሰራ ሌብነት እና ዝርፊያ ገቢ ያስገኛሉ ሆኖም ግን እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት ስለመቻሉ እርግጠኛ ለመሆን እንዲቻል ከፍተኛ ኦፐሬሽን እንደሚጠይቁ ካቦዎቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህም ስለሆነ ነው ቤት ከመዝረፍ ይልቅ ጭነት የተጫኑ የጭነት መኪኖችን አስገድዶ በመጥለፍ የያዙትን እቃና ሸቀጥ በሙሉ መስረቅን ይመርጣሉ። ሌላው በማፊዮሶዎች ቅም ላይ የሚውለው ዘዴ የከባድ መኪና ሾፌሮችን ወይም የወደብ ሠራተኞችን በገንዘብ በመደለል እቃ የጫኑ ሣጥኖችን እንደተሳሳቱ አስመስለው ያለቦታቸው እንዲያራግፉ ወይም እንዲያስቀምጡ በማድረግ እቃዎቹ በማፊያው እጅ እንዲገቡ ማስደረግ ነው። የተሰረቁት ሸቀጦች ከሙዚቃ ማዳመጫ ስቴርዮ መሣሪያ ጀምሮ እስከ ሴቶች አልባሳት   የሚደርሱ ማናቸውም ዓይነት ሸቀጦች ሊሆኑ ይችላሉ (የሴት አልባሳትን መዝረፍ ጆን ጎቲ የውንብድና ሥራውን ሲጀምር ይወደው የነበረው የዝርፊያ ዓይነት ነው)።
ሌላው የማፊያ አደገኛ እንቅስቃሴ በሠራተኛ ማኅበራት ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት፣ ሁሉም በኒው ዮርክ ከተማ የነበረ የኮንስትራክሽን ፕሮጄክ በማፊያ ቊጥጥር ሥር የሚከናወን ሥራ እንደነበረ ይታመናል። የማፊያ አለቆች የሠራተኛ ማኅበር መሪዎችን አንድ የሠራተኛ ማኅበር ሥራ ተወዳድሮ ሲያሸንፍ በንዑስ የሥራ ተቋራጭነት ሥራ ለማፊያው ቡድን እንዲሰጡ በገንዘብ ይደልሏቸዋል ወይም ያስፈራሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሌላው ሳይቀር ራሳቸው የማፊያ አለቆቹ የሠራተኛ ማኅበሩ ከፍተኛ አመራር ላይ በመሪነት ደረጃ በመግባት ማኅበሩን እንደፈለጉ ይዘውሩታል።
ማፊያው አንድን የሠራተኛ ማኅበር አጥብቆ ያዘ ማለት ሙሉውን ኢንዲስትሪ በቊጥጥሩ ሥር አዋለ ማለት ነው። ማፊዮሶዎች ሥራ ተቋራጮች ወይም አስገንቢ ድርጅቶች ትክክለኛውን ክፍያ እስካልፈጸሙ ድረስ ሠራተኞችን በማሳመጽ ሥራው እንዲያጓተት ወይም ከናካቴው እንዲቆም የማድረግ አቅም አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ በሠራተኛ ማኅበሩ በሚያዘው የሠራተኛው የጡረታ ገንዘብ ላይ እንደፈለጋቸው ለማድረግ የሚያስችል አቅምና ጉልበት ሁሉ አላቸው። ማፊያው በአንድ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ የነበረን ሁሉንም የኮንስትራክሽን ሥራ እና የመርከብ ጭነት መጫንና ማራገፍ ሥራ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ቀጥ አድርጎ ማስቆም ሁሉ የሚያስችል ጉልበትን አግኝቶ ነበር። ሆኖም ባለፉት 20 ዓመታት ፌደራል መንግሥት በማፊያና ሠራተኛ ማኅበራት መካከል የነበረውን አንድነትና ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለመበጣጠስ  ችሏል።
አሁን ያለው የማፊያ መዋቅር አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ በክፍለ ዘመናት የሚቆጠር ጊዜን ወስዷል። ስለ ማፊያ ታሪክ ለመረዳት እና ሕግ አስከባሪው በነዚህ ሁሉ ዓመታት የተደራጀ ወንጀልን ለማስቀረት ምን እርምጃዎችን እንደወሰደ ለማወቅ ማንበብህን ቀጥል።
ታሪክ
አሁን ያለው የማፊያ መዋቅር አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ በክፍለ ዘመናት የሚቆጠር ጊዜን ወስዷል። የማፊያ ታሪክ የሚጀምረው ሲሲሊ በምትባለው የጣልያን ደሴት ላይ ነው። ምንም እንኳ በሌላ የጣሊያን ክፍላተ ሃገራት ውስጥም እንዲሁ የተደራጁ ትላልቅ ወንጀል ቡድኖች ቢኖሩም የሲሲሊ ማፊያ የሌሎች የማፊያ ድርጅቶች ሁሉ ቁንጮ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።
በሲሲሊ ውስጥ የተደራጀ ወንጀል እንዲያብብ እና ፍሬ እንዲያፈራ በርካታ ምክንያቶች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይች ደሴት በሜድትራኒያን ባሕር ላይ በቀላሉ ሊደረስበት በሚችል እና ከስትራቴጂ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ባለው ቦታ ላይ ትገኛለች። ይህ በመሆኑም፣ ሲሲሊ በእጅግ አደገኛ ጠላት ኃይሎች ለበርካታ ጊዜያት ተወራ፣ ተሸንፋለች እንዲሁም በቊጥጥር ሥር ተይዛ ቆይታለች። እነዚህ ገጠመኞች በሲሲሊ በሚኖረው ሕዝብ ዘንድ በማእከላዊ መንግሥት ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ እና በሕግ የበላይነት እንዳያምን የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከማእከላዊ መንግሥት ይልቅ ቤተሰቡ የሲሲሊ ሕይወት አስኳል ሆነ። በሰዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች ሕግ ካስቀመጣቸው ገደቦች በላይ ሊያልፉ በሚችሉ የመፍትሔ መስጫ ዘዴዎች አማካይነት መፍትሔ ያገኙ ጀመሩ።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የአውሮፓ የፊውዳል ሥርዓት ለመጨረሻ ጊዜ የተገረሰሰው በሲሲሊ ነበር። ምንም ዓይነት ይኼ ነው የሚባል መንግሥት ወይም ሥልጣን ያለው አካል በሌለበት ሁኔታ ደሴቲቱ ወደ የለየለት ሕገወጥነት አዝቅት ወረደች። የተወሰኑ ባለባቶች እና ሌሎች ጉልበት ያላቸው ሰዎች የየራሳቸውን ዝና እና ገናናነት ያጎለብቱ ጀመሩ። በስተመጨረሻም እንደ አካባቢው መሪዎች ይታዩ ጀመሩ። ስማቸውም ካቦዎች (capos) በመባል ይታወቁ ጀመሩ። ካቦዎቹ በእነርሱ የሥልጣን ክልል ሥር ካሉ ገበሬዎች ግብር ለማስከፈል ይህንኑ ሥልጣናቸውን ይጠቀሙበት ጀመሩ (ልክ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት የፊውዳል ባላባቶች ሁሉ)። የእነርሱ ሥልጣን ተፈጻሚ የሚሆነው ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ሰው እንዲፈራ በማድረግ ነበር። የወንጀል እንቅስቃሴያቸው በጭራሽ ሕግ እንዲያውቀው ተደርጎ አያውቅም፤ የዚህም ምክንያት ሕግ እንዲያውቀው ለማድረግ የሞከረው ሰው ሊደርስበት የሚችለውን የበቀል ቅጣት ገና ለገና ስለሚፈራው ነው። ይህ የሲሲሊ ማፊያ የመጀመሪያው መጀመሪያ ነበር።
(ይቀጥላል)





No comments:

Post a Comment