Thursday, May 24, 2018

ሐበሻ

ሐበሻ
ከነካኩት እንጂ ካልነኩት አይነካም
ሐበሻ ራሱን እንጂ የሰው ዘር አይጠላም
ልብ እና ኩላሊት እንደ ፊት አይታይም
አይቻልም እንጂ ቢቻል ነበር መልካም
የፊጢኝ ታስሮ በውቅያኖስ ዋና
በፋኖስ መለወጥ የፀሐይን ፋና
የነብርን ጅራት ለቆ ሩጫ
አህያ ሰፈር ገብቶ እርግጫ
ጅብን አቅፎ እንቅልፍ
እባብን አምኖ ማሳለፍ
ሐበሻን ሐበሻ በሾኬ ካልጠለፈ
ወንድሙ ላይ ታርጋ ካልለጠፈ
ቃሉን አጥፎ መንገድ ካላጠፈ
አጥፎም በሽብር ደም ካልተራጨ
ሴራ ሸርቦ እንደ ነጠላው ካልቋጨ
ጎረቤቱ በበላው ሆዱን ካልታመመ
እንዲያሽረው ኮሶ በኮሶ ካልታከመ
እንዳይበለጥ በዘመዱ ተንኮል ካልሸረበ
መርፌ ሰክቶ በግድግዳ ጠንቋይ ካልቀለበ
ባላንጣ ሆኖ መሳይ ባልንጀራ
ለታይታ ፍቅሩ መዐድ ካልተጋራ
ግራ እየገባው ካላጋባ ግራ
ዐረብን አርጎ ዲኑ
በራሱ መጨከኑ
ፈረንጅ አርጎ መልአኩ
የጠፋበት ሚዛን ልኩ
ለቀብር ከሰነፈ ጉልበቱ
በሞተ ከጨከነ አንጀቱ
ምቀኛ ካሳጣው ጸሎቱ
ጥሬ ቢያጣ ካልቆረጠመ ጥራጥሬ
ታሪኩን ካላወጋ ተቀምጦ በወሬ
እና ይኼን ሁሉ ዐውቀው እንዳይርቁት
ክፋቱን ብቻ ዐይተው እንዳይጠሉት
ገዳም ገብቶ መላክ ያናግራል
ሰማይ ቤት በምድር ያደናግራል 
የፈጣሪ ስም ጠርቶ ወኔህን ይሰልባል
ችግር ፈጥሮ ራሱ ባካል
ለነፍስ ምስጢር ይፈታል
ምሥራቅ ሲሉት ምዕራብ
ሰሜን ሲሉት ደቡብ
ያለም እንደርቢ አዋኪ ሸዋኪ
እውነትን አንቆ እምነትን ሰባኪ
ሐበሻን ዐውቃለሁ ማለት ዘበት
ብልቃጥ ያልገባ መርዝና መዳኒት
ኋላ ሲሉት ከፊት ከፊት ሲሉት ኋላ
ታንገት ተሽጦ በፍቅር አንገት የሚቀላ
እንብላ ብሎ በአንደበቱ ስተህ ብትበላ
በሆድህ ስም ሰጥቶ አፈር ድሜ የሚያስበላ
ይኼን ዘመን የማይፈታው እንቆቅልሽ
ተዉት ባለበት ሳይነጋ እንዳይመሽ
አይነኬን ነክተን ቀልባችን እንዳይሸሽ
ተሰፍርን ዝም አልን በሥዩመ እዝጊ ዘሐበሽ
ጉያችን ጣፍጦ ገብቶ ሲያቀረናን እንደ አብሽ
ዓሣን ካልበሉት በብላት
ሐበሻን ካላወቁ በሥርዓት
ሕይወትም ይሆናል ለግጥ ዕውቀትም ሁሉ ከንቱ
ሐበሻን ልብ ብለው ካላዩ ከሥር መሠረቱ
ሕይወትም ይሆናል ለግጥ ዕውቀትም ሁሉ ከንቱ
ሐበሻን ልብ ብለው ካዩ ከጥንት ከጠዋቱ
ያው ዞሮ ዞሮ ድንቅነሽ ናት እናቱ



የቅዱስ መርቆርዮስ ለታ ትሳስ 2018 
የሐበሻ ስምንት ዐመት ኋላ መቅረት፣ 
አለው አንዳች ነገር አለው አንዳች ብላት
ብሩክ በ.

No comments:

Post a Comment