Thursday, October 13, 2016

ባብኤል

ባብኤል

አንድዬ ጠቢቡ፣ የማይመረመር
ላዳም ለፍጡሩ፣ አበጀለት በር
ገነትን ያውቅ ዘንድ እንዳይመራመር
እንዳይከጅልበት ያንን የራሱን በር
በትንሹ ጠግቦ በሰላም እንዲኖር

* * * * *

አዳም አልጠግብ ባይ ሁለት ፍሬ አይቶ
ትልቁን ተመኘ ትንሹን ዘንግቶ
አንድዬም ተቆጣ ክፉኛ አዘነ
ይኼንን እቡይ ሊቀጣው ወሰነ
የቅጣቱም ፍሬ እዛው ተበር ላይ ሆነ

* * * * *

ትልቁን በር ሊሰጥ፣ ትንሹን ሲነሳው
አዳም ነፍላላው ቅጣቱ መች ገባው
በትንሽ በር ገብቶ በትልቅ መውጣቱ
ከበር ወደ በር መንከራተቱ
አልገባውም መቼም ምንእን'ደው ቅጣቱ

* * * * *

በበር እየወጣ በበር እየተዘጋ
በር እያመረተ አልተወም ፍለጋ
እነዚያ ሁለት ፍሬዎች ሲያወጡ ሲያወርዱት
እንደ ችግኝ አብቅለው እንደ ግንድ ሲጥሉት
አለ እስተ ዛሬ በር በሩን እያሳዩት

* * * * *

አዳም አልጠግብ ባይ ካንድም ሁለት ፍሬ ያየው
ትንሽ በሩን ትቶ ትልቅ በር የተመኘው
እኒያ ሁለት ፍሬዎች ከላይ ሲያጃጅሉት
ንቆ የተዋትን ገነት እያዘካከሩት
ይስቁበታል ቁልቁል በሯ ሥር ጥለውት

* * * * *

በር ነውና ርግምቱ በር ነውና ክህደቱ
ዓይን ላጠፋ ዓይን የአንድዬ ቅጣቱ
በበር እየገባን በበር እንወጣለን
በር ላይ ተኝተን ተበር እንገባለን
እስከዚያው ግና ብዙ በር እንሠራለን

* * * * *

እኛ የአዳም ልጆች አይከፋንም ከቶ
እንጨፍራለን አባታችን ሁለት ሞት ሞቶ
የበሩን ነገር ለእኛ ተዉት
እንሠራዋለን ገና ባይነት ባይነት
ትልቅ ነው መሆን ትልቅ ነው መመኘት

በወርሐ ሽሞኒም የፈረንጆቹ ዕለት 11
2016 አዲስ አበባ ተጻፈ

No comments:

Post a Comment