Thursday, October 27, 2016

ምርኮ

ትላንት በዚህች ሰዓት
ትላንት በዚህች ቅጽበት
እንደ ገደል ናዳ
እንደ ርዕደ መሬት
እንደ ኤሌትሪክ ፍጥነት
እንደ መሬት ስበት
እንደ ጐርፍ ክስተት

ከየት ነው ሳልለው
እስተኔውን ሳላውቀው
ደርሶ ያንበረከከኝ
ልቤን የሰለበኝ

ትላንት በዚህች ሰዓት
ትላንት በዚህች ቅጽበት

ዛሬም እንደዚያው ነው
አለ ከስፍራው
ልቤን ተቆጣጥሮ፣ በቀልቤ ላይ ነግሦ
ተንሰራፍቷል፣ ቀዬውን ቀይሦ

ነገም በዚህች ሰዓት
ነገም በዚህች ቅጽበት
አይለወጥም ቃሌ
ይኼ ነው ዓመሌ

ወድጄ ገብቼያለሁ፣ ከድጥ ወደ ማጡ
ምርኮዬን አምኜያለሁ፣ እስቲ ምን ታመጡ


በወርሐ ቅዱስ (አውጉስቶስት) ዕለተ 29፣ 2016 አ/አ


Friday, October 21, 2016

የባህር ላይ ኩበት


አይ ያንቺ ነገር
የባሕር ላይ ኩበት
ወይ አይፈረፈር
ወይ ሰምጦ 'ማይተዉት
ወዲህና ወዲያ እየተላጋ
ሌት ተቀን ከንቱ እያተጋ
መዋተት ብቻ ምንም ላያተርፉ
ከከንቱ አብረው እየተንሳፈፉ
ያንቺ ነገር የባሕር ላይ ኩበት
እያየን፣ እያወቅን ዕድሜ ፈጀንበት

በወርሐ ሽሞኒም ዕለት 27፣ 2016 አዲስ አበባ ተጻፈ
መታሰቢየነቱ ለጋሽ ፀጋዬ በዳሶ (ሐሳቡን ለሰጡኝ)

የጠፋ ልብ



የጠፋ ልብ

አፍቅሬሽ ነበረ
እውነት ያን ሰሞን
ወድጄሽ ነበረ
አምና ያኔ ልክ እንደ ዘንድሮ
አልገባሽም ግን አንቺ
ከልቤ እንደሆን 
አሁን  ግን . . . አሁን ግን
ልቤም ተስፋ ቆርጦ
በሮ ሄዷል የለም ከቦታው
ወጥቷል ከሰገባው
ላይመለስ ላይገባ ከስፍራው
እና አሁን ከረፈደ ጊዜው
እንኳንስ ላንቺ፤ ለኔም
እንኳንስ ላንቺ፤ ለኔም
ጠፍቶኛል አድራሻው

በወርሐ ሽሞኒም የፈረንጆቹ ዕለት 21
2016 አዲስ አበባ ተጻፈ

Thursday, October 13, 2016

ባብኤል

ባብኤል

አንድዬ ጠቢቡ፣ የማይመረመር
ላዳም ለፍጡሩ፣ አበጀለት በር
ገነትን ያውቅ ዘንድ እንዳይመራመር
እንዳይከጅልበት ያንን የራሱን በር
በትንሹ ጠግቦ በሰላም እንዲኖር

* * * * *

አዳም አልጠግብ ባይ ሁለት ፍሬ አይቶ
ትልቁን ተመኘ ትንሹን ዘንግቶ
አንድዬም ተቆጣ ክፉኛ አዘነ
ይኼንን እቡይ ሊቀጣው ወሰነ
የቅጣቱም ፍሬ እዛው ተበር ላይ ሆነ

* * * * *

ትልቁን በር ሊሰጥ፣ ትንሹን ሲነሳው
አዳም ነፍላላው ቅጣቱ መች ገባው
በትንሽ በር ገብቶ በትልቅ መውጣቱ
ከበር ወደ በር መንከራተቱ
አልገባውም መቼም ምንእን'ደው ቅጣቱ

* * * * *

በበር እየወጣ በበር እየተዘጋ
በር እያመረተ አልተወም ፍለጋ
እነዚያ ሁለት ፍሬዎች ሲያወጡ ሲያወርዱት
እንደ ችግኝ አብቅለው እንደ ግንድ ሲጥሉት
አለ እስተ ዛሬ በር በሩን እያሳዩት

* * * * *

አዳም አልጠግብ ባይ ካንድም ሁለት ፍሬ ያየው
ትንሽ በሩን ትቶ ትልቅ በር የተመኘው
እኒያ ሁለት ፍሬዎች ከላይ ሲያጃጅሉት
ንቆ የተዋትን ገነት እያዘካከሩት
ይስቁበታል ቁልቁል በሯ ሥር ጥለውት

* * * * *

በር ነውና ርግምቱ በር ነውና ክህደቱ
ዓይን ላጠፋ ዓይን የአንድዬ ቅጣቱ
በበር እየገባን በበር እንወጣለን
በር ላይ ተኝተን ተበር እንገባለን
እስከዚያው ግና ብዙ በር እንሠራለን

* * * * *

እኛ የአዳም ልጆች አይከፋንም ከቶ
እንጨፍራለን አባታችን ሁለት ሞት ሞቶ
የበሩን ነገር ለእኛ ተዉት
እንሠራዋለን ገና ባይነት ባይነት
ትልቅ ነው መሆን ትልቅ ነው መመኘት

በወርሐ ሽሞኒም የፈረንጆቹ ዕለት 11
2016 አዲስ አበባ ተጻፈ