Wednesday, December 13, 2017

Miss Me But Let Me Go [Translated into Amharic as a dedication to Ras Empis Fred, the great French artist]



A picture containing photo, building, indoor

Description generated with high confidence
Miss Me But Let Me Go
                [To Sir Fred]


When I come to the end of the road
And the sun has set for me
I want no rites in a gloom-filled room
Why cry for a soul set free?

Miss me a little-but not too long
And not with your head bowed low
Remember the love that we once shared
Miss me-but let me go

For this is a journey that we all must take
And each must go alone.
It's all part of the Master's plan
A step on the road to home

When you are lonely and sick of heart
Go to the friends we know
And bury your sorrows in doing good deeds
Miss me but let me go.


Author: Anonymous English Poem
Translation in Amharic By Brook Beyene
To my beloved brother His Honor Great Artist Empis Fred (Ras Fredo), and his beloved spouse Ariane Le Lay, the lover of Ethiopia and Ethiopians
On the day of his last journey out today December 13, 2017
እቴ ትንሽ ናፍቂኝ፣ ግን ልሂድበት! እዚህ ቆይ አትበይኝ

ለአያ ፍሬድ


ከመንገዱ ጫፍ ላይ ስደርስ፣ መንገዴ ሲያልቅ
ፀሐይዋ ከሰማይ ለእኔ ስታዘቀዝቅ ልትጠልቅ
ደብዛዛ ብርሃን በተሞላ ቀዬ፣ አያሻኝም ፍትሃት
ለነፍስ ምን ያረጋል ለቅሶ፣ አግኝታ ሳለ ሃርነት?


ትንሽ ብቻ ናፍቂኝ ብዙ እንዳይሆን ግን አደራሽን
ባጎነበሰ አንገትሽ ሸጉጠሽ፣ እንዳትቀብሪው ፊትሽን
ስላለፈ ፍቅራችን ብለሽ፣ መቼም እንዳትረሺኝ!
እቴ ትንሽ ናፍቂኝ፣ ግን ልሂድበት! እዚህ ቆይ አትበይኝ


እነሆ ዛሬ ተራዬ ደርሶ መሳፈር አለብኝና ለዚህ ጉዞ
ለብቻ እንጅ፣ አይኬድምና እዚህ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ
እንደ ፈጣሪያችን ዕቅድ ሐሳብ፣ አንዱ መገለጫ ምክንያት
ከዋናው ቤታችን ለመድረስ፣ ይኸው አንድ እርምጃ ወደፊት


ብቸኝነት ሲውጥሽ ሲከፋ ክፉኛ ልብሽ
ጓደኞቻችን እንደኔ፣ ላንቺ ዛሬም አሉልሽ
እናም ያን ሐዘንሽ ገንዘሽ፣ በጎ ሥራ እየሠራሽ ቅበሪልኝ
እቴ ትንሽ ናፍቂኝ፣ ግን ልሂድበት! እዚህ ቆይ አትበይኝ



ደራሲው ያልታወቀ የእንግሊዝኛ ግጥም
ትርጉም በብሩክ በየነ
ለውድ ወንድሜ ክቡር ታላቅ አርቲስት
ኤምፒስ ፍሬድ (ራስ ፍሬዶ) እና ለውድ ባለቤቱ ኧሪያን ለ ሌይ፣
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ወዳጅ በዕለተ ሕልፈቱ ዛሬ ታህሳስ ፬፣ ፳፻፲








Sunday, August 6, 2017

ሰው ሆይ ስማ!

ሰው ሆይ ስማ! መቼም ስለማትሰማ
ሰው ሆይ ስማ! ጆሮህ ስለማይረባ
ሰው ሆይ አትስማ! አሁን ስለምትሰማ
የሚያገባህን ትተህ በማያገባህ ስትገባ
መታሰቢየነቱ ለአባባ ተስፋዬ ሐምሌ 30, 2017 ያው ወደ ኋላ አልቀርም

Friday, August 4, 2017

ጠጡ






ጠጡ!

ቅዱስ ሆሄያት . . . በፊደል ገበታ መባቻ ሠመሩ




ለሰው ልጅ ሁሉ. . . ጠቃሚ አግባቢ ቃል ሠሩ


. . . ጠ-ጡ !
. . . ጠ-ጡ !

 . . . ጠ-ጡ!


ታለም ስትመጡ ጠጡ ሽርት ውሀ

ባለም ስትኖሩ ጠጡ የግዜር ውሀ

ሻይ፣ ቡና፣ አረቂ፣ ሌላም ብዙ ብዙ

ጠጡ ጨልጡት ዋንጫውን ያዙ

ግን አደራ የራሳችሁን ብቻ ጠጡ

መዘዝ አለው የሰው አትቀላውጡ

መርዝ፣ ደም፣ ጥይት እንዳትጠጡ

ጽዋችሁን ብቻ ጠ-ጡ!

 



የካቲት ፳፪፣ ፳፻፲፰


Albert Camus

አንድና አንድ ብቻ ያልተመለሰ ከባድ የሥነ አስተሳሰብ ጥያቄ አለ፦ እሱም ራስን የማጥፋት ጉዳይ ነው። ሕይወትን መኖር ወይም አለመኖር ልክ ነው ወይም አይደለም ማለት መሠረታዊውን የሥነ አስተሳሰብ ያልተመለሰ ጥያቄ ከመመለስ ጋር ይስተካከላል። ---- አልቤር ካሙ "የሲሲፈስ ምሥጢር" (1942)

Wednesday, July 5, 2017

ላይ ከራስ ዱሜራ. . .




ላይ ከራስ ዱሜራ፣ ራስ ካሳር አቋርጦ ሃገረ ኤርትራ
የኑብያ አሸዋን ጠፍጥፎ በናስር ውሃ ጋዛ ፒራሚድ የሠራ
ካታንጋ ከታላቁ ካሮ ኬፕታውን ኮይኮይና ሳን ስልተ ቀመሩ
ታች ካልሃሪ፣ ሳህራ፣ ቲምቡክቱ ሰንጥቆ ዳካር ጫፍ ድንበሩ
ሰፊው እግሬ አንድ አገር በአንድ ጊዜ ረጋጩ
ጣና፣ ቪክቶሪያ፣ ቮልታ፣ ቻድ ውሃ መጣጩ
ከኪሎማንጃሮም በላይ የሰፋ፣ የረዘመ ደረቴ
ከነዳሽን፣ ከነካሜሩን በላይ የዘለቀ አንገቴ
በቀኝ አንድሮሜዳን ጨብጦ በግራ ስድስቶ
አፍሶ የሚያድር እጄ ከዋክብት አስፈርቶ
ጠቆር ብዬ ቡና፣ እልፍ ምእልፊት ደቂቃኑን የማቃና
ራሴ ላይ የሚታሰረው ምልክት የሰማዩ ቀስተ ደመና
ልቤ ገር ስንት አገር አስልጦ፣ አሳልጦ ሳይገዛ ተገዢ
ደሜ እንዲሁ ደመ መራር ሕዋሱ እንደ ፍል ተባዢ
የጥፍሬ ጥጋጥግ ረዝሞ ጥቁር የቀለመው
ሜዳና ሸንተረር ጋራ ቧጭሮ የሚያፈርሰው
በቶም ቶም ጉባዔ ቃና ባልፉን ካሊምባ መትቼ
በኮራ ገመድ ክራር ማሲንቆ ራሴን አጫውቼ
ድቤ አታሞ ከበሮውን ጀምቤውን ደብድቤ
ስለው ዳንሱን በድንበር በአጥር መች ተገድቤ
ሺ አፍሼ ሺ የምዘራ ዛፎችን በአንድ እፍኝ ቀጣፊ
የእግዜሮች ባርያ ታማኝ ጥቁር አጋፋሪ ጥቁር አሳላፊ
ምሥጢሬን ሳንሶላስል በዜማ በዳንኪራ
የጠራች እውነት በራሴ ኩራዝ ሳበራ
እነማን ቀድመው ሰሙ? እነማን ቀድመው ሰገዱ
ወይስ ስተው፣ ነጭ እንዲቀልም ጥቁር ሰው አረዱ?  

ዕለተ አማኑኤል ሰኔ፣ 2017