Monday, November 14, 2016

መዘዘኛው እረኛ



መዘዘኛው እረኛ
ያ እረኛ!
በአርያም ምድር . . . በሰዶም ጐመራ
ምስኪን በጐቹን ደፍሮ ያሠማራ
ምሱ ሊተርፍ ደሞ ለእኛ . . . ያ እረኛ!
“ደሞ ማነህ?” ያሉት
ፈጥነው ቀንድ የነከሱት
በስላቅ የጠየቁት
እውነቱ የቅርብ ሩቅ . . . ያ እረኛ!

ንፅሕናው እጥፍ ቢያሳድፋቸው
ድርብ ቢያጐድፋቸው . . . እንደ ከርስ ቢያሸት ቢያገማቸው
ቀይ ዓይናቸውን ቢጠነቁል
ሐቁ ቢደንቁላቸው፣ ቢኮሰኩሳቸው!

መስሎዋቸው . . .  የፈታቸው
ክብር ነፍጐ የተፋባቸው
የግልገል በግ ዋጋ እንኳ ያሳጣቸው
ተነሡበት ድንገት፣ ሐቁ እሬት ሆኖባቸው

እናም ከነበጐቹ እንደ ልቡ ላይፈነጭ
ራሱ የጠመቀውን እንዲጐነጭ
ምድር በሞላ ለብሳ እሳት
እረኛው ተደቆሰ በክህደት።

ምድርም ልትበጅ አፉን ላሞጠሞጠ . . . በደሙ ለተጉመጠሞጠ
የሰላሙን ባሕር አብሮ ለናጠ . . .  ላናወጠ . . . ላቀላወጠ
እረኛው ተተፋ በወጀቡ! እጅጉን ተገፋ
ሕልሙ እንደ ዋዛ ብን ብሎ ጠፋ።

ባፍ ይጠፉ እንዲሉ ሆኖበት
ቁልቁል ወረደ! ወረደ ከድጠት!
ቅኔም ዘረፉለት . . .  አንድ አዲስ ቅኔ
ግዳይ ጥለው እየጨፈሩ በወኔ
በሐሙስ ምሽቱ ጀብዱ፣ በታላቁ ሴራ
በአርያም ምድር የሞት ብርሃን በራ
ከሳሽም የለባቸው! ደግሞ ለአንድ ተራ እረኛ
ማን ሊሆነው ዋስ ማን ሊቆምለት ጠበቃ
ስንዴው በአርም አውድማ አብሮ ተወቃ።

እነርሱው ገዝተው
እነርሱው ሸጠው
እነርሱው ወግረው
እነርሱው ሰቅለው

የክፋታቸው ክርፋት
የገበናቸው መብዛት
ለእኛም ተርፎ . . . ይኸው በስሙ ቆዳችን ተገፎ
ከበሮ ሊሠሩን ወጠሩን፣ ዝንት ዓለም ሊደልቁን
ዕድሜ ልክ ሊያለፉን! እኛ ጥቁሮቹን. . .
እሱም በጐቹን በትኖ ሔደ!
እኒያ የተኩላ ለምድ የለበሱ በጐቹን
አደራውን ለእኛ ጥሎልን።
ይኸው አለን እስካሁን
እነሱም እኛም ሰላም እንቅልፍ እንደ ራቀን
እንደ ዓሣ እርስ በርስ እየተባላን።

አበጅቶ ፍፁም ላያበጃጃት
ፉንጋዋ ላይ ውበት ላይጨምርላት
ዓለምን እንደ ሕልም ዐለም አድርጓት
ፍፁም ላያስተሰርያት፣ ከበሽታዋ ላያድናት
በሽታ ጨምሮላት፣ ይባስ አሳምሟት
በጐቹን የሰቀሉትነት ለተኩላነት
እኛንም ለዘላለም ባርነት!
ፍቅርን ዘምሮ . . .  አስቀረን ባዶ ቤት!
ኦና ቤት!

ከአዝመራችን አምና የገባው ነጭ ዝንጀሮ
አለ ይኸው ዛሬም ዘንድሮ
ያ እረኛ! ያ ጦሰኛ!
በአርያም ምድር . . . በጐመራ
በሰዶም በጐቹን ያሠማራ
ምሱ ለእኛ ተርፎ . . . በስሙ ቆዳችን ተገፎ
ስለ ፍቅር፣ ቤታችን ሆኖ ቀፎ
ይኸው አለን እስተዛሬ
በከበሮነታችን ስንሰዋ ዝማሬ!
                  1998 እ.አ.አ

Friday, November 11, 2016

የናፍቆት ሰላምታ



የናፍቆት ሰላምታ
ሲለኝ ከፊትሽ
ሲለኝ ከኋላሽ
ሲለኝ በቁምሽ
እንዳሻኝ የማገኝሽ
አንቺ የኔ ብቻ
የሌለሽ አቻ
ደሞም በጀርባዬ
ደሞም በደረቴ
ከደረትሽ አረፍ የምልብሽ
በጆሮሽ ምሥጢሬን የማዋይሽ
እንባዬን የምታብሽ
በሐሴት የምፈስብሽ
ሰማየ ሰማያትን የማይብሽ
ሲለኝም የምሸናብሽ
በህልመ ሌሊት የምተኮስብሽ
ታምሜ የምታስታምሚኝ
ከጨለማው የምታስጠይኝ
ታማኝ ወዳጄ
ሁሉን የማይብሽ
ስሞትም የማርፍብሽ
አንቺ፣ የኔ ፍራሽ
በእጅጉ እንደምን አለሽ?
ኖቨምበር 6፣ 2016

Thursday, November 10, 2016

ሥጋና ቸኮሌት



ሥጋና ቸኮሌት
ልገዛ ብዬ ሥጋ፣ ያውም ጠፈፍ ያለ
ፀዳ ብሎ ለስለስ፣ በደንብም ቀላ ያለ
“ሱፐርማርኬት” ከሚሉት የፈረንጅ ገበያ ገብቼ
ከበሬ፣ ከበጉ፣ ከዶሮው፣ ከአሣማው ሥጋ ዐይቼ
ከሞርቶዴላው፣ ከሞዘሬላው ባይነት ባይነቱ
ማቀዝቀዣ ገብቶ ቀዝቅዞ ወጥቶለት ብልቱ

«ቶሎ ገዝታችሁ በልታችሁ፣
ረፍቴን ስጡኝ ባካችሁ
በቁምም በሞቴም
ከንቱ አታስቀሩኝ
ውሻ ከሚበላኝ፣
ገንዳ ከምትጥሉኝ
እናንተው እናንተው፣ አደራችሁ
ጨርሱኝ እንደ ጀምራችሁ! »
ይል ይመስል፣ በሰው ሠራሽ ብርሃን ደምቆ
ለዛውን አጥቶ ክብሩን ሁሉ፣ ከላዩ አወላልቆ
ፍጡር እንዳልነበር ትናንት፣ እንደ ዕቃ ታጭቆ
መላ መላውን ወጥቶ ዛሬ፣ እስታጥንቱ ታርቆ

ሥጋ ቆራጩ እየተንጐማለለ፣ ሲያፏጭ ቢላውን
ሲያቁለጨልጭ፣ አላፊ አግዳሚ፣ ሸማች ተረኛውን
ሊያጠምድ የራበውን፣ የቸኮለ፣ ለሥጋ የሴሰነውን፣

ይኼን ውዳቂ ሥጋ እኔም ልገዛ ዳዳሁና
ጠጋ አልኩ ከመደቡ፣ አንዱን መረጥኩና

ግና ግና ከወዲያ ማዶ፣
ከዚያ ከሌለበት በረዶ
ከመደርደሪያው ላይ
የካካዎን ልጅ፣
ቸኮሌትን ድንገት ባይ
ራሴኑ በራሴ
በቅፅበት ሞገትኩ

ግርማ ሞገሷን ዐይቼ እሷኑ ወደድኩ፣
ዐይቼታም አልቀረሁ፣ እሷኑ መረጥኩ
በምትሃቷ ተስቤ ወደሷ ቀረብኩ

ብትሸጥም፣ ዛሬም እንደትናንቱ
ብትለወጥም ዛሬም ብትሆን ከንቱ፣
ክብሯን አላጣችም አሁንም
በደራው፣ በዚህ በሸቀጡ ዓለም፣

ሻጭ ከገዢ መልሶ የሚያሽሞነሙናት
ሥጋውን አራቁቶ እሷን የሚያልብሳት
የሚያሽሞነሙናት
የሚያቀናጣት
አንዳች ረቂቅ ነገር
አንዳች ምትሃት አላት
11/9/2016