የማፊያ ዕድገትና ጥንካሬ
ለበርካታ ክፍለ ዘመናት
ዕድሜ ያስቆጠሩት የማፊያ ኑሮ ዘይቤ በርካታ አባለ ነገሮች በሲሲሊ ውስጥ ከፊውዳል ሥርዓት ወደ ዘመናዊ የመንግሥት ሥርዓት
ለመለወጥ ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ የተፈጠሩ ናቸው። ኮዛ ኖስትራ (cosa nostra) ወይም “የኛ መንገድ” የሚለው ሐረግ በሲሲሊ
የነበሩትን የማፊዮሶ ሰዎችን አኗናኧር ዘይቤ ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለ ሐረግ ነበረ። በሲሲሊ ውስጥ በወቅቱ የነበረው በማፊያ
እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ያለው ከፍተኛ ምሥጢርን የመጠበቅ አባዜና ያልተጻፈ ጥብቅ ሕግ ኦመሬታ (omerta) ወይም የጸጥ ማለት
ደንብ በመባል መታወቅ ጀመረ። የማፊያ አለቆች ይህንን ደንብ በድርጅቱ ውስጥ ከእነርሱ በታች ካሉ ወንጀለኞች እንቅስቃሴዎች
ራሳቸውን ለመጠበቅ ተጠቅመውባቸዋል። ወጣት ወንድ ልጆችን ወደ ማፊያ የመመልመሉ እና በመጨረሻም የመጨረሻውን ፈተና የመስጠት
ሂደት በመጀመሪያ የተጀመረው እዚህ ሲሲሊ ውስጥ ነበረ።
በ1900ዎቹ መባቻ ላይ፣
የተደራጀ ወንጀል የሲሲሊን የዕለት ተዕለት ሕይወት አንድ መገለጫ ከመሆኑ የተነሣ ከማፊያው ቡድን ጋር በአንድ ወይም በሌላ
መልኩ ግንኙነትን ላለመፍጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር። አምባገነኑ ቤኒቶ መሶሎኒ ከባድ ብዙውን ጊዜ ዘግናኝ የሆኑ
እርምጃዎችን በመውሰድ የማፊያውን እንቅስቃሴ ለማሽመድመድ ችሎ ነበር። ሆኖም ግን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጨረሻ የአሜሪካ
ወታደሮች ሲሲሊን ሲቆጣጠሩ በእስር ቤት የነበሩትን አብዛኛዎቹን ወንጀለኞች እንደ ፖለቲካ እስረኛ አድርገው በመቊጠር ከባድ
ስህተት ተሳሳቱ። በዚህም እነዚህን ወንጀለኞች ከእስር ነጻ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹን እንደ ከተማ ከንቲባዎች እና የፖሊስ
መኮንኖች አድርገው ሹመት ሰጡዋቸው። ብዙም ሳይቆይ፣ ማፊያው የጣሊያንን ዲሞክራት ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረው ቻለ።
ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት
ዓመታት የተለያዩ እርስ በርስ ይፎካከሩ የነበሩ የሲሲሊ ቤተሰቦች የእነርሱ የማያቋርጥ ጦርነት ከፍተኛ ገንዘብ እያስወጣቸው
እንደሆነ ለመገንዘብ ቻሉ። ወዲያውኑ የተኩስ ማቆም አዋጅ በማወጅ የሁሉንም ቤተሰቦች የሥራ እንቅስቃሴዎች በበላይነት
የሚቆጣጠርና ዋንኛ ድርጅቶችን እና ነፍስ ግድያዎችን የበላይ ሆኖ የሚያጸድቅ ኩፖላ (Cupola) የሚባል ቡድን
አቋቋሙ። ተመሳሳይነት ያለው ሥርዓት በ1950ዎቹ በአሜሪካ የሚገኙ ቤተሰቦችም ተቋቋሞ ነበር። እነዚህ ኮሚቴዎች የእርስ በርስ
የወንበዴ ጦርነትን ለጊዜው ጋብ እንዲል ለማድረግ ከመቻላቸው ባሻገር ካፑላ ባለበት አለቆች በግላቸው ነፍስ ግድያዎችን
እንዲያጸድቁ ስለሚያስችሉ አለቆች እራሳቸውን ለግድያ የተጋለጡ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።
በሲሲሊ ማፊያ ላይ
የሚደረገው መንግሥታዊ ጦርነት በ1980ዎቹ ላይ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። በማፊያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ
ያደረጉ ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ዓቃቤ ሕጎች በቦምብ ጥቃት እንዲገደሉ ተደረጉ። ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ተቆጣ፣ መንግሥትም
በስተመጨረሻ ማክሲ ፍርድ (Maxi trial) በሚባል ዘመቻ አጸፋ ምላሽ ሰጠ። ከአራት መቶ የሚበልጡ ማፊዮሶዎች በልዩ ሁኔታ
በተዘጋጀ ችሎት ላይ ለፍርድ ቀረቡ። በፍርድ ቤቱ ጀርባ ላይ በተዘጋጁ ሰፋፊ ክፍሎች ውስጥ ተከሳሾች እንዲገቡ ይደረጉና
ተከሳሾቹ በእነርሱ ላይ ለመመሥከር በሚቀርቡት ምሥክሮች ላይ የፍርድ ሂደት እየተከናወነ ይጮኹባቸውና ያስፈራሩዋቸው ነበር።
በድምሩ፣ ከተከሳሾቹ መካከል 338ቱ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው ተፈርዶባቸዋል።
ይህ እርምጃ ለብቻው ግን
የሲሲሊን ማፊያ ጠራርጎ ለማጥፋት በቂ አልነበረም። በ1992 የኢጣሊያ መንግሥት ቊጥራቸው 7000 የሆኑ ወታደሮችን ወደ ሲሲሊ
ላከ። ወታደሮቹም ደሴቲቱን እንደተቆጣጠሩ እስከ 1998 ድረስ ቆዩ። የሲሲሊ ማፊያ ዛሬም ድረስ ያለ ሲሆን አሁንም ድረስ ሙሉ
በሙሉ አልሞተም። ሆኖም ግን ከበፊቱ አንጻር ሲታይ በጣም ጸጥ ያለ እና አመፀኛነቱም በእጅጉ የተመናመነ ነው።
በሚቀጥለው ክፍል ላይ
ማፊያ እንዴት ወደ አሜሪካ ሊመጣ እንደቻለ እንመለከታለን።
የአሜሪካ ማፊያ
ሲሲሊዎች እና ሌሎች
ኢጣሊያዊያን በ1800ዎቹ ላይ ወደ አሜሪካ መሰደድ ጀምረው ነበረ፤ ሆኖም ግን ቊጥሩ ከፍተኛ የሆነ ስደተኛ ወደ አሜሪካ ባሕር
ዳርቻዎች የደረሰው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ነው። አብዛኛዎቹ ከነዚህ ስደተኞች መካከል ለቤተሰባቸው አዲስ ሕይወትን
ለመመሥረት በሕጋዊ መንገድ ሲፈጉና ሲታትሩ አንዳንዶቹ ግን የሲሲሊ ማፊያ አኗኗር ዘይቤያቸውን ወደ አሜሪካ ይዘው በመግባት
በዚሁ መንገድ መዝለቁን መረጡ።
የመጀመሪያው ትልቁ
የማፊያ ነክ ክስተት የተፈጠረው በ1890ዎቹ ውስጥ በኒው ኦርሊያንስ ውስጥ ነበር። ሲሲሊያዊ ወንጀለኛ ቤተሰብ በአካባቢው
የፖሊስ አለቃ ከፍተኛ ግፊት ሲያርፍበት ፖሊሱን ገደለው። የማፊያው ቡድን አለቆች ለፍርድ በቀረቡ ጊዜ ምሥክሮችን ጉቦ በመስጠት
ከቀረበባቸው የነፍስ ግድያ ወንጀል ነጻ ሊሆኑ ቻሉ። ፀረ ኢጣሊያዊያን አመፅ ፈነዳ፤ አጥቂ የመንጋ ፍርድ ሰጪ ኃይል ወደ እስር
ቤቱ አመራ። መንጋው ፍርድ ሰጪ ኃይል ታስረው ከነበሩት ሰዎች 16ቱን ሰዎች በጠመንጃ ተኩሶ ወይም በገመድ ሰቅሎ ገደላቸው።
የማፊያ ቤተሰቦች
በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በመላው አገሪቱ ተሠራጩ፤ ኒው ዮርክን እንደ ዋንኛ የማዘዣ ማእከላቸው በማድረግ
በዚህ ከተማ ውስጥ አምስት ቤተሰቦች በዋንኛነት ተደራጁ። የክልከላ ዘመን (era of Prohibition) የሚባለው ጊዜ
ማፊያዎች በመላው አገሪቱ በሚገኙ ድብቅ የመጠጥ ግሮሰሪዎች ሕገወጥ አልኮልን እንዲሸጡ ሁኔታዎችን ስላመቻቸላቸው በክልከላው
ተጠቅመው እነዚህ የማፊያ ቤተሰቦች ከፍተኛ ገንዘብ በማጋበስ ወደ ካዝናቸው ለመክተት ቻሉ። በዚህ ጊዜ የነበራቸው ጉልበት
በሚያስገርም ሁኔታ ወደ ከፍተኛ ደረጃ አደገ። ዕድገቱንም ተከተሎ በቤተሰቦች መካከል ተቀዛቅዞ የነበረው ጦርነት እንደገና
አገረሸበት። በ1930ዎቹ መባቻ ላይ የማፊያ አመፅ ከፍተኛ
ወረርሽኝ በሽታ ነበር። አለቆች እና ዋንኛ የበታች አለቆች በመደበኛነት በተከታታይነት ይገደሉ ነበር። ከመገደላቸው በፊት
ቤተሰባቸውን ለጥቂት ወራት ያክል እንኳ መምራት የቻሉት ጥቂት አለቆች ብቻ ሆኑ። የሉቼዝ (The Luchese) ቤተሰብ በ1930 ዓ.ም.
ብቻ ከሦስት እስከ ዐራት የሚደርሱ አለቆችን አስተናግዷል።
በዚህ እልቂት መካከል (አብዛኛውን እልቂት በማቀናባበር ቁልፍ ሚና የነበረው) ዕድለኛው ሉቺያኖ ("Lucky" Luciano)
የሚባል የማፊያ መሪ
ነበር።
ሉቺያኖ በላ ኮዛ ኖስትራ
ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግን የማፊያ እንቅስቃሴ ፈቃድ የሚሰጥ የበርካታ
ቤተሰብ የጋራ ኅብረት የሆነ ኮሚሲዮን እንዲቋቋም ይወተውት ከነበረና ለተወሰነ ጊዜ ተቀባይነት ከነበረው ሐሳብ ጀርባ ሉቺያኖ
ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ አበርክቷል።
ኮሚሲዮኑ
በቺካጎ የተደረገ ስብሰባ
ከበርካታ ቤተሰቦች የተውጣጣ የማፊያ ኮሚቴ እንዲቋቋም መሠረቱን ጣለ። በመጀመሪያ የተቋቋመው የዚህ ከበርካታ ቤተሰቦች የተውጣጣ
የማፊያ ኮሚቴ ሰባቱ አባላት ከአምስቱ የኒው ዮርክ ቤተሰቦች ከተውጣጡ አለቆች እና ከቺካጎው አል ካፖን (Al Capone) እና ከስቴፋኖ ማጋዲኖ የቡፋሎ ቤተሰብ (Buffalo family) የተውጣጡ አባላት ነበሩ። የኮሚሲዮኑ አባላት ለሌሎች ቤተሰቦች ልክ እንደ ሴናተር
ሆነው ያገለግሏቸው ነበር። ቤተሰቦቹ የሚያሳስቧቸውን ነገሮች እንደ ሕዝብ ተወካይነታቸው ለሌሎቹ የሴኔቱ አባላት በማምጣት
ድምፃቸው እንዲሰማ ያደርጉላቸው ነበር። ለምሳሌ በምዕራባዊው ዳርቻ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት ቤተሰቦች ሁሉም በሚቻል
ደረጃ በቺካጎው አለቃ የተወከሉ ነበሩ። ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያለባቸው የገንዘብ ማግኛ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ነፍስ ግድያዎች
እና የሰው ጠለፋዎች በኮሚሲዮኑ ድርጊቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት ፈቃድ ማግኘት ነበረባቸው። የኮሚሲዮን አባልነት በየአምስት ዓመቱ
በሚደረግ የማፊያ ስብሰባ ላይ የሚወሰን ጉዳይ ነበር።
ከነዚህ የማፊያ
ስብሰባዎች መካከል በማፊያ ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትዕይንት የተፈጸመው -- የአፓላቺን ወረራ (the Apalachin
Raid) በሚባለው ስብሰባ ወቅት
ነው። ኖቨምበር 14 ቀን
1957 ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ
ዋና አለቆች (ዶኖች) ከፔንሲልቫኒያ ድንበር አጠገብ በምትገኝ አንዲት ሚጢጢ አነስተኛ የኒው ዮርክ ስቴት ከተማ ውስጥ
ለስብሰባ ተሰብስበው ነበር። በሁኔታው የተጠራጠረ የስቴት ፖሊስ ኃይል ድንገት ወረራውን በመፈጸም 58 የማፊያ ከፍተኛ አባላትን
ከሕግ ፊት አቀረባቸው -- በአብዛኛዎቹም ላይ የክስ መዝገብ ከፍቶ እንዲከሰሱ
ለማድረግ ቻለ። ወረራው በማፊያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ እንዳለ ሆኖ ከዚህም የከፋ ከባድ ተጽዕኖ ፈጥሮ ነበር። የአሜሪካ
ሕዝብ ከዚህ በኋላ ማፊያ የሚባል ነገር የለም ብሎ መካድ እንዳይችልና እውነታውን በፀጋ እንዲቀበል ተገደደ።
ከምሥረታው
በኋላ ኮሚሲዮኑ ቀስ በቀስ ጉልበቱን እያጣ ሔደ -- አንዳንድ ቤተሰቦች የነበራቸውን ኃይል ከማጣት አልፈው ከናካቴው ተወካዮቻቸውን
መላክ አቆሙ። በዛሬው ጊዜ፣ አሁንም ድረስ ኮሚሲዮኑ እንዳለ የሚወራ ወሬ ቢኖርም፣ በዕድለኛው ሉቺያኖ (Lucky Luciano) ጊዜ የነበረውን
ያክል ጉልበት ቅንጣት ታክል እንኳ የለውም።
በኬኒዲ ላይ የሚወራው ወሬ
በኬኔዲ ቤተሰብ እና በማፊያው ወገን መካከል ቅርብ
ግንኙነት እንዳለ የሚናገሩ ወሬዎች መናፈስ የጀመሩት ከጆን ኤፍ ኬኒዲ አባት ከጆ ኬኒዲ ጊዜ ጀምሮ ነው። አባትየው የቤተሰቡን
አብዛኛውን ሀብት ያከማቹት በከፍተኛ የወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ እንደሆነ እና እንደ ሜየር ላንስኪ ከመሳሰሉ የማፊያ አባላት
ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበራቸው በከፍተኛ ደረጃ ይወራል። ጆን ኤፍ ኬኔዲ በ1960 በዲሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያ ዙር
የውስጥ ምርጫ ላይ ከሁበርት ሃምፍሬ ጋር ለውድድር ሲቀርቡ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አስተማማኝ የመራጭ ድምፅ ማግኘት እንዲችሉ የኬኔዲ
ቤተሰቦች የማፊያውን ኃይል ስውር ድጋፍ እንደጠየቁ ብዙዎች የሚስማሙበት ነጥብ ነው። ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከፕሬዝዳንትነት ከሪቻርድ
ኒክሰትን ጋር ሲፎካከሩና ጆን ኤፍ ኬኔዲ በጠባብ የድምፅ ልዩነት ሲያሸንፉ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
በርካታ መላ ምቶች የጆን ኤፍ ኬኒዲን የነፍስ ግድያ
ከማፊያ ጋር ያገናኙታል። ጆን ኤፍ ኬኒዲን የገደለውን ሊ ሃርቪ ኦስዋልድ የገደለው ጃክ ሩቢ ከማፊያ ጋር ግንኙነት እንዳለው
በደንብ የታወቀ ነበር። ከነዚህ መላ ምቶች መካከል ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሊገደሉ
የቻሉት በኩባ የፒግስ ባሕር ሰርጥ ወረራ (Bay
of Pigs invasion of Cuba) ምክንያት የተነሣ እንደሆነ ያትታል። ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከፍተኛ ገንዘብ ያጋብሱበት ከነበረው የካዚኖ
ቁማር ንግድ ከኩባ እንዲወጡ ባደረጋቸው ፊደል ካስትሮ እጅ ኩባ መተዳደርዋን ማፊያዎች አልወደዱትም። ወረራውን ለመፈጸም ኩባ
የተደፋፈረችው ኬኔዲ ለምድር ኃይሉ የአየር ኃይል ድጋፍ እንዲደረግ ሳይፈቅድ በመቅረቱ የተነሣ እንደሆነ በአንዳንዶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ታምኖበት ነበር።
አንድ ሌላ መላ ምት ደግሞ የግድያውን ምክንያት ከጆን
ኤፍ ኬኔዲ ወንድም ከሮበርት ጋር ያገናኘዋል። ሮበርት በወቅቱ ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንደ ፕሬዝዳንት ሲመርጡ እሱ ደግሞ እንደ
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተሹሞ ነበር። አንድ ጊዜ ሹመቱን ካገኘ በኋላ ሮበርት ኬኔዲ ወዲያውኑ ማፊያን ጠራርጎ ለማጥፋት እንቅስቃሴ
ማድረግ ጀመረ። ሮበርትም ራሱ የተገደለው በቅጥር ነፍሰ ገዳይ በተተኮሰበት ጥይት ነው።
ሌላ ወሬ በበኩሉ ጆን ኤፍ ኬኔዲ በርካታ ውሽሞች እና
የሴት ጓደኞች እንደነበሩትና እነዚህ ሴቶች ከማፊያ አለቆች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ያትታል። የፌደራል ፖሊስ የተጠለፉ
የስልክ ንግግሮችን ጨምሮ አንዳንድ ማስረጃዎች የማፊያ አባሉ ሳም ጂያንካና ፕሬዚዳንቱ ከጋብቻ ስለ መወስለታቸው በቂ ማስረጃ
ከማሰባሰብ ባሻገር ሆን ብሎ ጆን ኤፍ ኬኔዲን ከበርካታ ሴቶች ጋር እንዲዳሩ ሁኔታዎችን ሳያመቻችላቸው አልቀረም። የሴራ
ፖለቲከኞች የጆን ኤፍ ኬኔዲ አንዷ ቁምጥ የነበረችውን የፊልም ተዋናይዋን ማርሊን ሞንሮን ተኩሶ የገደላት በጂያንካና የተላከ
ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ነው። ጂያንካና ራሱ በማፊያ/ኬኔዲ መካከል ስለነበረው ግንኙነት ምሥክርነት ቃሉን ሊሰጥ ትንሽ ሲቀረው ነበር
በነፍሰ ገዳይ ለጥቂት የተገደለው።
ቬጋስ እና ማፊያ
ላ ኮስታ ኖስትራ
ከበርካታ የቁማር ጨዋታዎች ጀምሮ እስከ ስፖርት ውድድሮች ውርርድ ድረስ በበርካታ ዓይነት የቁማር ጨዋታዎች ላይ በቀጥታ
ሁልጊዜም ሲሳተፍ ኖሯል። ማፊያዎች በመላው አሜሪካ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ውድ ሕገወጥ ካዚኖዎችን ያንቀሳቅሳሉ፤ ለዚህም
የአካባቢውን ፖሊሶች ጉዳዩን ችላ ብለው እንዲያውም ከሌላኛው ሕጋዊ አካል ሊቃጣ የሚችለውን ጥቃት በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ከፍተኛ
ጉቦ ይከፈላቸዋል። ኔቫዳ በ1931 ቁማር መጫወትን ሕጋዊ ስታደርግ በዕድሉ በመጀመሪያ የተጠቀሙት የማፊያ አባላት አልነበሩም። ከነሱ
መምጣት ቀደም ብሎ ታዋቂው ራቁት ዳንስ (Strip) እያቆጠቆጠ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ ጥቂት ቄንጠኛ
ሆቴሎች/ካዚኖዎች ማፊያ በመጣ ጊዜ በቦታው ላይ ነበሩ።
ማፊያዎች ከቦታው ላይ
ሲደርሱ፣ የተለመዱት በፖሊስ ተፈላጊ ወንጀለኞች አይደሉም የመጡት። በምትኩ፣ አብዛኛዎቹ የመጀመሪያዎቹ የቬጋስ ካዚኖዎች መነሻ
ወጪያቸው የተሸፈነው እንደ ቡግሲ ሴጋል እና ሜየር ላንስኪ በመሳሰሉ የአይሁድ ዝርያ ባላቸው ማፊያዎች ነበር። ካዚኖዎችን
ለመገንባት የትየለሌ ገንዘብን ወጪ ማድረግ ይጠይቃል፤ እና እነዚህ ባለሀብቶች ለበርካታ የካዚኖ ቤት ሠሪዎች አከፋፈላቸው
እንዴት እንደሆነ ግልፅ ያልሆኑ ብድሮችን አቅርበዋል። ከነዚህ ብድሮች መካከል አንዳንዶቹ ፊት ለፊት የተፈጸሙ ሲሆኑ ማፊያው
ካዚኖን እና ሆቴል ግንባታ ፕሮጄክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ የቲምስተር (Teamsters) ሠራተኛ ማኅበርን በመቆጣጠር የጡረታ ገንዘቡን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅሞበታል። ይህ ሁኔታ በ1975 የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳዩ ላይ ደርሰውበት ጣልቃ ሲገቡ ሙሉ በሙሉ ቆሟል።
ካዚኖዎች ከፍተኛ ትርፍ
የሚያስገኙ እንደመሆናቸው የማፊያ አባላቱ (ብልጦቹ ሰዎች) ከሚገኘው ትርፍ ምን ያክል ድርሻ ለእያንዳንዳቸው እንደሚደርሳቸው
ለማስላት ሆነ እንዴት ትርፉን ሊያገኙ እንደሚችሉ ብዙም አላስጨነቃቸውም። በከፊል በባለቤትነት ከያዙዋቸው ካዚኖዎች ጥሬ ገንዘብ
እንደ ላም ወተት ያልባሉ ወይም ከካዚኖ ባለቤቶች በማስፈራራት የሚያስፈልጋቸውን ያክል ገንዘብ በጉልበት ያገኛሉ። አብዛኛዎቹ
የማፊያ አለቆች የካዚኖ ባለቤቶቹ ወደዱም ጠሉም ከካዚኖ ባለቤቶች ጋር በጋራ የሚሠሩ “የንግድ ሥራ ሽርካዎች” ነበሩ።
ከ1970ዎቹ ጀምሮ፣
መንግሥት ማፊያውን ከቬጋስ ካዚኖዎች ለማስወጣት ጥብቅ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ ላይ ትላልቆቹ ካዚኖዎች
በማፊያ ተጽዕኖ ሥር እንዳልሆኑ ይገመታል። ከተደራጀ ወንጀል ጋር ግንኙነት እንዳለው ትንሽ ፍንጭ ከተገኘበ አንድ ካዚኖ የሥራ
ፈቃዱን እንዲያጣ በቂ ምክንያት ሊሆንበት ይችላል።
ፀረ
ማፊያ ትግል፦ ሕግ
መንግሥት የተደራጀ
ወንጀልን ለመዋጋት ከሚጠቀምባቸው በጣም ወሳኝነት ካላቸው መሣሪያዎች አንዱ ሪኮ (RICO) ይባላል።
ሪኮ (RICO) በማፊያ ላይ የምሥክርነት ቃል የሚሰጥ እምጃ አይደለም -- ሕግ ነው፤ የተጽዕኖ ፈጣሪ ሕገወጥ ድርጅት የሚሠሩ እና ሙሰኛ ድርጅቶች ሕግ (Racketeer Influenced and Corrupt Organizations
(RICO) Act) ርእስ 18፣ የአሜሪካ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ ክፍል 1961-1968 ማለት ነው። ይህ ሕግ በተለይ ማፊያን ለመዋጋት ተብሎ የፀደቀው በ1970 ነበር። ሕጉ በማፊያ ላይ የሚደረገውን ጦርነት ለማገዝ ዓቃቤ ሕጎች ድርጅቶችን በሙሉ
እንዲመረምሩ ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ከሕጉ ጋር የተፈጠረው ራኬተሪንግ የሚባለው ወንጀል የተገኘው ከማፊያዎች የተለምዶ እንቅስቃሴ
ወይም “ራኬትስ” ከሚለው ቃል የመጣ ነው። ይህ ወንጀል የሚፈጸመው ይህን የመሰለ ሕገወጥ የገንዘብ ማግኛ እንቅስቃሴ በሚያደርግ
ሕገወጥ ድርጅት አማካኝነት ገንዘብን ማግኘትን ይመለከታል።
ሁለት ወይም ከዚያ በላይ
እንዲህ ያለው ወንጀል ለመሠራቱ በቂ ማስረጃ ከተገኘ እና ፍርድ ቤት እንደ ወንጀለኛ ብያኔ ከሰጠ ወንጀለኛው ቢያንስ 15 ዓመት
በፅኑ እስር እንዲቀጣ ይደረጋል። በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ላይ ተጨማሪ በርካታ ወንጀሎች ከተገኙ በዚያው መጠን የእስር
ጊዜው በእጥፍ እየጨመረ እንዲሔድ ይደረጋል። ከነዚህ በከባድ ወንጀል ከሚያስጠይቁ የማፊያ ወንጀሎች መካከል የሠራተኛ ማኅበር
ወኪልን ጉቦ መስጠት፣ አልተባበርም ያለ የንግድ ሥራ ድርጅት ባለቤትን መግደል፣ እና ከኮንስትራክሽን ኩባንያ ሥራ ተቋራጮች
አስፈራርቶ ገንዘብን መቀበል በራኬተሪንግ (racketeering) ወንጀል ላይ እንደ ተጨማሪ ከባድ ጥፋት ይቆጠራሉ። ለእያንዳንዱ የጉቦ፣ የነፍስ ግድያ
እና የማስፈራራት ወንጀለኛነት በዐሥርት ዓመታት የሚቆጥር ፅኑ እስራትን ይስጨምራል። በተጨማሪ፣ የወንጀለኛው ድርጅት አባላት በግለሰብ ደረጃ በወንጀሉ
በቀጥታ ያልተሳተፉ እንኳ ቢሆኑ በራኬቴሪንግ
(racketeering) ወንጀል ተከሰው ሊቀጡ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ በማፊያ ዶኖች ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውን
ራስን መከላከያ ዘዴ አስቀርቷል -- በፊት ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ወንጀለኞችን በመላክ
ትልቁን ወንጀል እንዲፈጽሙ በማድረግ በወንጀሉ እንዳይጠየቁ ማድረግ ይቻላቸው ነበር።
ዛሬ
ላይ ሪኮ (RICO) ጠበቆች
ትላልቅ የወንጀል ክስን በማሸነፍ ከኮርፐሬሽኖች እና ሌሎች ቡድኖች ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅም እንዲያገኙ እያስቻለ ከመሆኑ ባሻገር
የተደራጀ ወንጀልን በመከላከል ረገድ እምብዛም ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ያለው።
ማፊያን
መዋጋት፦ ስውር ፖሊስ
የሕግ አስከባሪ
ባለሥልጣናት የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመያዝ እና ክስ ለመመሥረት እንዲችሉ በድርጅቱ ውስጥ ምን እየተደረገ እንዳለ በመጀመሪያ
ማወቅ ይኖርባቸዋል። የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎችን ወይም የከባድ መኪና ሹፌሮችን ጠላፊዎችን ሊይዙ ይችሉ ይሆናል ሆኖም ግን ማፊያ
ቤተሰቦች ሁልጊዜ አዳዲስ አባላትን ያገኛሉ። አንድን ማፊያ ቤተሰብ ሙሉ በሙሉ ለማሽመድመድ የቤተሰቡን ቁንጮዎች ማደንና መያዝ
ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ምርጡ ዘዴ ወደ ቤተሰቡ ስውር ፖሊስን አባል እንዲሆን በሚያስችል መልኩ ሰርጎ
እንዲገባ ማድረግ ነው።
እንደ የማፊያ አጋር ሆኖ
የሚሠራ ስውር የኤፍቢአይ ሠራተኛ የሚሠራው ሥራ እጅግ አደገኛ ሥራ ነው። ይህ የኤፍቢአይ ሠራተኛው ጆሴፍ ፒስቶን ለስድስት
ዓመታት በተከታታይ እንደ የዶኒ ብራስኮ (Donnie
Brasco) የማፊያ ረዳት ሆኖ
እየሠራ የኖረው ኑሮ ነው።
ከ Mafia-International.com የተባለ የድር ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ
ፒስቶን እንዴት የስውር ፖሊስ ሊሆን እንደቻለ አብራርቶ ነበር፦
እኔ ያደግኩት ከብልጦቹ ሰዎች ጋር በኒው ጀርሲ፣ ፓተርሰን አካባቢ ነው፤ ሆኖም ግን ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረኝም። ሁልጊዜ ማናቸውንም ዓይነት የጉልበት ሥራዎችን እሠራ ነበር፤ በግንባታ፣ በቡና ቤቶች፣ የትራክተር ተሳቢዎችን በመንዳት ወዘተ የተለያየ ሙያ ነበረኝ። ስለዚህ ወደ ኮሌጅ ከመግባቴ በፊት ብዙ ነገሮችን በማየት ብዙ ትምህርት ለማግኘት ችዬ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ስቀጠር ሥራዬ እንደ የባሕር ኃይል የደኅንነት ክፍል አባል ሆኖ ማገልገል፣ አደንዛዥ ዕፆችን፣ ስርቆትን እና የስለላ ተግባራትን መከታተል ነበር። የኤፍቢአይ የመግቢያ ፈተናን ካለፍኩ በኋላ በ1969 ልዩ ኤጀንት ሆንኩ። በነበረኝ የኋላ ታሪክ እና ሥልጠና ምክንያትም መሆን የነበረብኝ የግድ ልዩ ስውር ፖሊስ መሆን እንዳለበት ግልፅ ነበር።
ፒስቶን በሥራው በጣም
ስኬታማ ነበር። እርሱ የመራው ኦፐሬሽን በደርዘኖች የሚቆጠሩ የማፊያ አለቆችን እስር ቤት እንዲወረወሩ ቢያደርጋቸውም የእሱ
የማፊያ ጓደኞቹ ግን አሁንም ድረስ እሱ የኤፍቢአይ ኤጀንት ሳይሆን የማፊያው ክዶ የወጣ መሥካሪ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። የእሱ ታሪክ ዶኒ ብራስኮ "Donnie Brasco" የሚባል ፊልም ተሠርቶበታል።
ስውር የክትትል ሥራ ኤፍቢአይ
በማፊያው ላይ የሚያደርገው ጦርነት ወሳኝነት ያለው ሥራ መሆኑን ቀጥሏል። በክሌቭላንድ በስውር ፖሊስ የተመራ ኦፐሬሽን በ1998
ከ40 በላይ ሙሰኛ ፖሊሶችን በቊጥጥር ሥር እንዲውሉ አስደርጓቸዋል። እንዲህም ሆኖም ግን ስለ ስውር የፖሊስ ክትትል ሥራ ብዙም
ላትሰማ ትችል ይሆናል። የሥራው ባሕሪ ሆኖ በስውር የክትትል ሥራ ላይ የሚሠማሩት ኤጀንቶች ሐሰተኛ ስሞችን ይጠቀማሉ፣ ፎቶግራፍ
ላለመነሳት እምቢ ይላሉ እና ማንነታቸውን ከሕዝብ ዓይን ይሰውራሉ።ብሩክ በየነ (ጥር 21 ቀን 2019 በራስ አቆጣጠር)