ካልሲና ጫማ
ዕድሜው በግምት ወደ ዐሥር ዓመት የሚጠጋ
ሕፃን፣ ባዶ እግሩን ከአንድ የጫማ መደብር መግቢያ በር ጎን ባለው መስታውት ውስጥ የተሰቀሉትን ጫማዎችና ካልሲዎች አንድ ባንድ
አማርጦ እያየ ነበር። ጊዜው ክረምት ስለነበር ብርዱ ቆፈን ያስይዛል። እያንዘፈዘፈውም ቢሆን ብላቴናው ከሱቁ በር ላይ ቆሞ በተመስጦ ጫማዎቹን አንድ ባንድ ያያል።
በዚህ መሀል ታዲያ በሱቁ አጠገብ ታልፍ
የነበረች አንዲት ደርባባ ሴትዮ ድንገት ልጁን ዐየችውና በሁኔታው ልቧ ተነካ።
“ማሙሽዬ፣ ምንድነው በመስታውቱ ውስጥ
እያየህ ያለኸው?” ስትልም ጠየቀችው።
“እግዚአብሔርን ጫማ እንዲሰጠኝ እየጠየቅኩት
ነው!”
የሰጣት መልስ ውስጧ ድረስ ገብቶ እንደ
ኤሌክትሪክ ሲነዝራት ተሰማት። ልጁን በእጇ ወዲያውኑ አፈፍ አድርጋ ይዛው ሳታመነታ ወደ ሱቁ ውስጥ ገባች። ባለሱቁንም ግማሽ ደርዘን
ካልሲ እንዲያመጣላት አዘዘችው። ባለሱቁም የረዥም ጊዜ ደንበኛውን ለማስደስት ወዲያው እንደተባለው አደረገ። ቀጠለችና ደግሞ ውኃ
በማስታጠቢያና ፎጣ እንዲያዘጋጅላት ጠየቀችው። ባለሱቁም ይህንንም ግራ እየተጋባ ታዘዛት። ሕፃኑን ከመደብሩ ጓሮ ባለው ቦታ ይዛው
ገባችና ከንዱ ጥግ አስቀመጠችው። እግሮቹን ማስታጠቢያው ውስጥ እንዲነክራቸው ካደረገችው በኋላ እጅጌዋን ሰብስባ በመንበርከክ እግሮቹን
አጠበችውና በፎጣው አደራረቀቻቸው።
ምልክት ስትሰጠው ባለሱቁ ቅድም የጠየቀችውን
ካልሲዎቹን ይዞላት መጣ። ከካልሲዎቹ መካከል ደስ ያለውን እንዲመርጥ ለልጁ ሰጠችው። አዲስ ካልሲም እሷ እያገዘችው እግሩ ላይ አጠለቀ።
አዲስ ጫማም ቀጥላ አስደረገችው። አንድ ሁለቴ ወደፊትና ወደኋላ እንዲራመድ ካደረገችው በኋላ፦
__ “ማሙሽዬ፣ አሁን መቼስ፣ ያለጥርጥር
ደስ ብሎሃል?” አለችው እንዲያው ለወጉ ያህል። ደስ እንዳለው ምን ያጠራጥራል ?
ልጁ በርግጥ ምንም መናገር ሆነ ምንም
ዓይነት መልስ መስጠት አልቻለም። እየሆነ ባለውና እያየው ባለው ነገር ሁሉ እውነትነት እጅግ ተጠራጥሯል። በደስታ ብዛት አንደበቱ
ክዶታል። ደንዝዞ እንደ ሐውልት ቆሟል።
ሴትየዋ የሚከፈለውን ከፍላ ልጁን እዛው
ሱቁ ውስጥ እንደተገተረ ትታው ልትሔድ ስትል ከኋላዋ ሮጦ ደረሰባት። እጇን ነካ፣ ነካ አድርጎ ጠራትና ዞር ስትል፤ እንባ ባረገዙ
ዓይኖች ዓይን ዓይኗን እያያት፣ ሳግ እየተናነቀው፦
“እትዬ
! የእግዚአብሔር ሚስት
አንቺ ነሽ እንዴ ?” ብሎ ጠየቃት።
No comments:
Post a Comment