ብስለት እንዲህ ዝምብሎ የሚገኝ የዋዛ ነገር አይደለም።
ሁሉም ሰው በየራሱ መንገድ፣ ያጣጥመዋል። ብስለት ደረጃ ላይ የምንደርስበት ዕድሜ እንደ መልካችን ሁሉ ካንዳችን ላንዳችን የተለያየም
ነው። አንዳንድ ሰዎች ገና ጨቅላ እያሉ የብስለት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሌሎች በምድር ላይ ዘመናትን ቢያስቆጥሩም ይህ ነው የሚባል
የአእምሮ ብስለት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ያልፋሉ። እንግዲያው የዛሬው ወጋችን የሚያጠነጥነው ካንተና ከኔ ቀድሞ ገና በስድስት ዓመቱ
የብስለት ደረጃ ላይ ስለ ደረሰ ብላቴና ይሆናል። ለምን እንዲህ እንዳልኩ እስከ መጨረሻው አንብብና በፍረጃዬ ትስማማለህ ብዬም ተስፋ
አደርጋለሁ።
ብስለት
ወጋችንን ከመጀመራችን በፊት ስለ ብስለት ትንሽ
ነገር ለመናገር ያክል “ብስለት” አንድን ሰው እንዲህ ነው ብለህ ልታሳየውና ልታስተምረው ወይም አንተም ራስህ ከሌላ ሰው ልትማረው
የምትችለው ነገር አይደለም። ከጊዜ ጋር የምትደርስበት የአእምሮ ጥንካሬ ደረጃ ነው። ለአንዳንድ ሰዎች፣ ገና በአፍላ ዕድሜያቸው
ሲጎበኛቸው፣ ለአንዳንዶች ግን ከመምጣቱ በፊት ሊዘገይባቸው ይችል ይሆናል!
ይህን የስድስት ዓመት ብላቴና እንደ
አብነት እንውሰደው። ይህን ታሪክ አንብብና ስለምን እያወራን እንዳለን ይበራልሃል!
ታሪኩ
እንግዲህ ታሪክ በአጭሩ ይህን ይመስላል...
የስድስት ዓመት ልጅ ከታናሽ እህቱ
ጋር የቀለጠ የገበያ ማዕከል ውስጥ ብቻቸውን ወዲህና ወዲያ በእግራቸው እየተንሸራሸሩ ነበሩ። ብዙ ከተንሸራሸሩ በኋላም ትንሿ እህቱ
አንድ ሱቅ መስኮት ላይ ቆም አለች። እህቱ ወደ ኋላ መቅረቷን ያስተዋለው ታላቅየው ወንድሟ ወደ ኋላው መለስ ይልና ምን ወደ ኋላ
እንዳስቀራት ተመለከተ። ቀልቧን የሰረቀው ነገር ምን እንደሆነም ወዲያው ገባው። እህቱ እንዲያ በተመስጦ የምታየው ያለችው በሱቁ
ውስጥ ያለውን የሚሸጥ አሻንጉሊት እንደሆነ ለመረዳት ቅጽበት እንኳ ጊዜ አልወሰደበትም።
ብላቴናው እህቱ አሻንጉሊቱን በርግጠኝነት መፈለጓን
መረዳቱን በሚያሳይ መልኩ “ምን የሆነ የምትፈልጊው ነገር አለ አንዴ?” ሲል ጠየቃት። እህትየውም ምን እንደምትፈልግ ዓይኗን ከሱቁ መስኮት ላይ ሳታነሳ በእጇ አሻንጉሊቷን
በመጠቆም አሳየችው። ብላቴናውም አሻንጉሊቷን ዐየት አደርጎ እንደ ቁምነገረኛ ታላቅ ወንድም እህቱን በእጇ ይዞ
ወደ ሱቁ ይዟት ገባ። ከመደርደሪያው ላይ ፍጹም በሆነ በራስ መተማመን መንፈስ አንሥቶ ለእህቱ አሻንጉሊቷን ሰጣት። እህትየው ወንድሟን
ቀና ብላ ዐየችውና ፈገግ አለች። በጣም መደሰቷን ከፊቷ ላይ ማንበብ ይቻላል።
ባለሱቁ ይህ ሁሉ ሲሆን ከመጀመሪያው ጀምሮ በጥንቃቄ
እያንዳንዷን ነገር እየተመለከተ ነበር። በዚህ ልጅ ሁኔታ በጣም ተገርሟል። እህቱ በመደሰቷ የረካው ትንሹ ልጅ ወደ
ሱቁ ሒሳብ መክፈያ ሣጥን መጣን ባለሱቁን ኮራ ብሎ “ ጋሼ፣ የዚህ አሻንጉሊት ዋጋ ስንት ነው? !” ሲል ጠየቀ።
ይህ ባለሱቅ እንደ ዕድል ሆኖ ፍጹም
ደግ ሰው መሆኑን ከግምትህ አስገባና ምን ሊያደርግ እንደሚችል ገምት። የነዚህን ወንድምና እህት ፍቅር በማየት ልቡ በርህራሄ ቀለጠ።
ረጋ ባለ ድምፀት ቀስ ብሎ ለትንሹ ገራሚ ልጅ “ስንት መክፈል ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
የቀንድ አውጣ ቅርፊቶች
ልጁ ምንም ገንዘብ እንዳልያዘ ያው የታወቀ ነው።
ግን ከባሕሩ ዳርቻ የለቃቀማቸውን የቀንድ አውጣ ቅርፊቶች በኪሱ ይዞ ነበር። እህቱ ለወሰደችው አሻንጉሊት ሒሳቡን ለመክፈል ሁሉንም
የቀንድ አውጣ ቅርፊት ከኪሱ አወጣና ለባለ ሱቁ ተንጠራርቶ ጠረጴዛው ላይ ዘረገፈለት።
ባለሱቁም የእውነት ገንዘብ የተከፈለው ይመስል ቅርፊቶቹን አንድ ባንድ እያነሳ
ቆጠራቸው። ቆጥሮ ሲጨርስም ሕፃኑን ልጅ ቀና ብሎ ዐየው፣ ልጁም እንደ መጨነቅ አለና “ምነው አይበቃም?” ሲል በፍራቻ ጠየቀው። የልጁን ጭንቀት ያስተዋለው
ባለሱቅ “ኧረ እንዲያውም… የሰጠኸኝ ከዋጋው በላይ ነው።
ስለዚህ ትርፉን እንካ መልሼልሃለሁ፣ ያንተ ነው ያዘው” አለው። እንዲህ ብሎ ሁሉንም መልሶለት ለራሱ ያስቀረው ዐራት የቀንድ አውጣ ቅርፊት ብቻ ነበር። ብላቴናው
በጣም ተደሰተና ከትንሿ እህቱ ጋር አመስግኖ ከሱቁ ወጥቶ ሔደ።
እውነተኛው ጥያቄ
ከባለሱቁ ጋር የሚሠራ ሌላ ተቀጣሪ ሠራተኛ ባለሱቁ
እየሠራ ያለውን ሥራ እየተከታተለ ነበርና በነገሩ በጣም ተገረመ። ወደ ባለሱቁ ጠጋ አለና “አለቃ! ያን የመሰለ ውድ አሻንጉሊት
እንዴት በዐራት የቀንድ አውጣ ቅርፊት ትለውጣለህ ???” ሲል ጠየቀው። ባለሱቁ ፈገግ ብሎ ለሠራተኛው “እንዴት መሰለህ፣ እነዚህ ለኛ የማይረቡ የቀንድ አውጣ ቅርፊቶች ናቸው። ግን ለዚያ ትንሽዬ
ልጅ ከምንም በላይ ውድ ነገር ናቸው። እና በዚህ ዕድሜው፣ ገንዘብ ምን ማለት እንደሆነ አይገባውም። ሆኖም ሲያድግ የገንዘብ ትርጉም
ምን እንደሆነ ያኔ ያውቃል። በገንዘብ ሳይሆን በቀንድ አውጣ ቅርፊት አሻንጉሊት እንደገዛ ትዝ ሲለው ቀን እኔን ያስበኛል። በዚህም
ዓለም ሁሉ በቀና ሰዎች የተሞላች ስለመሆኗ ያስባል። በዚህም ቀና አመለካከት በውስጡ እንዲያጎለብትና ጥሩ ሰው ለመሆን እንዲችል
ይበረታታል።”
ሁላችንም ከዚህ አንድ ወይም ሁለት
ጥሩ ነገር መማር አለብን። ሁላችንም ቀና መንፈስን ብናሠራጭ እና መልካም ባሕሪ ለማሳየት ብንታትር፣ ዓለማችን ምንኛ ደግ በሆነች
ነበር ?!
ሱሃስ ከተባለ/ች ጸሐፊ በበይነመረብ ላይ ተገኝቶ
በከሣቴ ብርሃን ቡሩክ ወደ አማርኛ ስለ ቀናነት ዋጋ ለመክፈል ጊዜ ተሰውቶ የተተረጎመ ኅዳር 22፥ 2018 (በራስ አቆጣጠር)