Wednesday, February 28, 2018

አምቡላንስ

አምቡላንስ መሄዱ እያለ ዋይ ዋይ
መቼ ለራሱ ሆኖ የበዛበት ስቃይ
የራሱ አርጎት እንጂ የሰውን ጉዳይ
እሪ ማለቱ እንዲያ በጎዳና ባደባባይ

Tuesday, February 27, 2018

ምንተስኖት




(የፋኖ እዚህ ምን አመጣው ቊጥር ፪)
ብርንዶ ቆራጩ፣ ግብርም ቀራጩ
ወርቅ ባሌስትራ አድርጊ ቀጥቃጩ
ጫኝና አውራጅ ሿሚና ሻሪ
ገድሎ ቀባሪ፣ ፈቺና አሣሪ
ራስህ ከሳሽ ራስህ መርማሪ
አንተው አስተማሪ፣ አንተው ተማሪ
ሲልህ ኮማንደር ሲልህ ደግሞ ዶክተር
አያልቅብህ ማዕረግ ክቡር ፕሮፌሰር
ካምቦሎጆ አርቢትር ችሎት ደግሞ ዳኛ
የሰው ቅን አሳቢ ድንበር የለሽ አርበኛ
ሲሻህ ዐቃቤ ሕግ፣ ሲሻህ ዐቃቤ ንዋይ
ከሊቀ ጳጳሱም በላይ ረቂቅ ኤልሻዳይ
ለሙዕሚኑ ሟች ከሙፍቲውም በላይ
የጠቅላዮች ሁሉ ጠቅላይ
እየታየህ የማትታይ፣
ሁሉን ግን የምታይ
አውራጅ ሰቃይ፣
ሰውን እንደ ብቅል አብቃይ
ሲሻህ ደግሞ እንደ ተህዋስ በካይ
ቢራ ጠማቂ ኢንጂነር፣ አንባቢ ጋዜጠኛ
አቻ የሌለህ አትሌት፣ የምንም አንደኛ
የከያኒያኑ ቁንጮ፣ ድምፀ-መረዋ ጓዴ
ምንተስኖት ያልኩህ የማታጣ ዘዴ
አስመጪና ላኪው፣ ቱጃሩ ነጋዴ
ገብተህ ካንጀት ከሆዴ
ሥጋ የምትበልት በሁዳዴ
የጋኔል ታናሽ ወንድም
አንተ አይደለህ እንዴ?
ለካቲት ፩፮ (ኪዳነ ምህረት) ፳፲፯

ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?





ግራ አጋቢ ነው ዘንድሮ የፅጋቡ ነገር
ጤፍ ቆልቶ ምላሱ ወርቅ ይሠራል ካፈር
ማዕረግና መመረግ ሆሄ ተምታቶ ከዛ ታች ሠፈር
እንደ ጭስ ሾልኮ ወጥቶ ከላይ፣ ሲገን ደፋር ባገር
ጫንቃው ተሸክሞ ዲሞፍተር፣ ደፍተር ሳይዝ ጉያው
 ወሽቆ ክፋቱን በብብቱ፣ ሳያነሣ ጣቱን ከቃታው
እንዴት ነው ተማሪ ቤት ገብቶ ትምርት ያማረው ?
እና ጥያቄው. . .
ባለዲሞፍተር ሺ ጊዜ ቢማር ቢመራመር
ምን ይሆናል? ዶክተር ወይስ ዶፍ-የጠር?
እዛ እንጃ !
ካረገው ሳንጃ !
እዛ እንጃ እንጂ
አስረግጦ ፈንጂ !
ፋኖ እዚህ ምን አማረው ?
ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?
እምቧይ ግን ላይሆን ሌላ፣ ላይጠፋ ማንነቱ
ካብን እሠራ ብሎ ጭራሽ ካብ እብስ ማለቱ
ዕውር ቢጤውን ሊመራ ደፍሮ መነሣቱ
ባንድ ጊዜ እኮ ሆነ፣ አምስት ጊዜ ጥፋቱ !
አቅልን ነስቶ
ልክ አሳጥቶ
ያለቅጥ ሲያቅበጠብጥ
ልብን የሳበጠ ነፍጥ
አንጎል መጦ ሲያናፍጥ
አንጋች ያኔ በባዶ እግር የረገጠውን ኮረኮንች
መጫሚያ ሲያግኝ ቢረግጠው መች ሊሰለች ?
እዛ እንጃ !
ካረገው ሳንጃ !
እዛ እንጃ እንጂ
አስረግጦ ፈንጂ !
ፋኖ እዚህ ምን አማረው ?
ፋኖ እዚህ ምን አመጣው ?
መታሰቢያነቱ በዘመኑ ጉዶች እጅ ሰጥተው ለጀዘቡ፣ ማንነታቸው ለጠፋ ምስኪን የቀድሞ ዘመን ምሁራን - ታህሳስ ፮፣ ፳፲፩፯

Thursday, February 22, 2018

አጉል እምነት ወይስ . . .?




ነውር የሆኑ ወይም ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች
1.      ግራ መዳፍን ካሳከከህ ገንዘብ ታገኛለህ፤ ቀኙን ከሆነ ደግሞ ገንዘብ ታወጣለህ።
2.     ቡና ወይም ሻይ ስትጠጣ ስኳር ከግራ ወደ ቀኝ የምታማስል ሰው ከሆንክ ገንዘብ አጥፊ፣ በታኝ ነህ በተቃራኒው የምታማስል ከሆነ ማለትም ከቀኝ ወደ ግራ (ወደ ውስጥ ወይም ወደ ራስህ አቅጣጫ) የምታማስል ከሆነ ገንዘብ ሰብሳቢ፣ ቆጣቢ፣ ወይም አሳዳጅ ነህ።
3.     ሙቀጫ ላይ መቀመጥ አጎትን ወይም የቅርብ ዘመድን ይገላል።
4.     ማታ ቤት አይጠረግም። አለበለዚያ የቤቱ ሲሳይ ተጠርጎ ይሄዳል።
5.     ማታ ማታ ጥፍር አይቆረጥም፣ የሚወዱት የቅርብ ሰው ይሞታል።
6.     ሳሙና መቀባበል የአንዱን ሲሳይ ወይም መጥፎ ዕድል ከአንዱ ወደ አንዱ እንዲተላለፍ ያደርጋል።
7.     እንጀራ፣ ልጅ፣ ከብት ብዛታቸው ለሰው አይነገርም። ብዛቱን ቆጥሮ የተናገረ መዓት ይመጣበታል።
8.     የልደታ ቀን ቤቱ ሙሉ የሆነ ወሩን ሙሉ ቤቱ ሙሉ ይሆናል። ልደታ ቀን ወጪ የሚያወጣ ሰው ወሩን ሙሉ ወጪ ሲያወጣ ይከርማል።
9.     ዘነዘና መቀባበል መጥፎ ምልክት ነው። ያጨካክናል።
10.    ከመሸ ለጎረቤት ጨው፣ በርበሬ፣ ክብሪት ማዋስ መጥፎ ነው። ለዚያኛው ቤት እሳት እንደ መስደድ ይቆጠራል።
11.     ቢላ በስለቱ ለሰው ማቀበል መጥፎ ነው። ከተሳሳትክ በአፍንጫው ወዲያው መሬት መውጋት አለብህ።
12.    እርጉዝ ሴት ድንጋይ ላይ መቀመጥ የለባትም። የምትወልደው ሰው አይሆንም።
13.    ቃሪያን ሁለት ቦታ ከፍሎ ተካፍሎ መብላት ነውር ነው፤ ያቆራርጣል።

የጥሩ ዕድል ምልክቶች ወይም የመጥፎ ነገር ምልኪዎች
1.      ቤት ውስጥ አይጥ ከገባ ምቀኛ ሰው ቤትህን አይቶታል ማለት ነው።
2.     ውሻ ሌሊት ካላዘነ ሰፈር ውስጥ የሆነ ሰው ይሞታል።
3.     ቡና ሲቀዳ አረፋ ከሠራ የተቀዳለት ሰው ሲሳይ አለው፣ ቀኑ የተቃና ነው፣ ገንዘብ ያገኛል ማለት ነው።
4.     ዓይን ቆብ እርግብግብ ካለ የጠፋ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ወይም ሩቅ አገር ያለን ሰው በቅርቡ ታያለህ።
5.     ቤት ውስጥ የጫማ ሶል ተገልብጦ በሶሉ በኩል መሬት ላይ መጣል የለበትም። መጥፎ ነገር በዚያ ቤት ውስጥ ያጋጥማል።