Thursday, December 29, 2016

ወረፋና ፈረቃ



ወረፋና ፈረቃ

አይወጡም አንድ ላይ፣ ጣይና ጨረቃ
አላቸው ሥርዓት አላቸው ፈረቃ
አይታይም የሰልፉ ደርዝ የሰልፉ መነሻ
የአቡሻኩር ምሥጢር፣ የቀን መዳረሻ

ቀንም ሰልፍ ይዞ ይቆማል ሪጋ፣ ይጠብቃል ወረፋ
ያዘግማል ወደፊት ጠብቆ ተራ፣ ሳያዝን ሳይከፋ
ብርሃንና ጸልማት ሲገቡ ፈረቃ
አንዱ እየተኛ ሌላው እየነቃ
አዎ፣ ቀንም ይጠብቃል ወረፋ
ሳያዝን ሳይከፋ፣ እርስ በርሱ ሳይጋፋ 
እስኪያልፍ ገፊ በተራው እየተገፋ
 

ሁሉንም ባንዴ አልሠራም አንድዬም እራሱ
ፊትና ኋላ አርጎ ነው ሁሉን የከወነው በራሱ
ባንዴም አልተበላም ዕፀ በለሱ
ተራ ጠብቀው ነው የተቃመሱ
በተራ ነው፣ ሥርዓት ያፈረሱ
በተራ ነው፣ ተሲዖል የፈለሱ

ሁሉም ነበረው ተራ፣ ሁሉም ነበረው ወረፋ
ያኔም ቢሆን ዔዶም ከምድር እስትጠፋ

ስንመጣም በወረፋ፣ ስንሄድም በወረፋ
አምላክ አደራህን ወረፋ ይስፋፋ
ጭቁን እስኪጨቁን ጭቆና ይንሰራፋ
ይኼ ነው እና የኛ ንግርት፣ ያ ታላቁ ተስፋ
ቆሞ መጠበቅ ተራ፣ ቆሞ መጠበቅ ወረፋ

ዶን ብሩኖ ወርሃ ታሳስ ዕለተ ረቡዕ በገብሪኤል ባመት በንግሡ፣ 2016

No comments:

Post a Comment