ወይዘሪት እና ወይዘሮ
ያቺ ጉብል ወሲፋ፣ ባይን የምንቀጥባት
ያቺ መለሎዋ ኰረዳ፣ ቀጭኔዋ አንገት
ወይ ብላ ዞራ የምትከት ካዙሪት
ደርባባዋ ቆንጆ፣ የኛዋ ወይዘሪት
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ገና ብቅ ስትል ትትያለች ከሩቅ
አላት አንድ ነገር ልብን የሚሰልቅ
አንቺም ወይ ስትዪ እነሱም ወይ ሲሉ
ካንቺ የዋሉ፣ ባንቺ ቀሩ እንደዋለሉ
ማን ዐወቀና እንዳላት አዙሪት
ታምረኛ ዐጥንት፣ የኛዋ ወይዘሪት
ምርጫ ትሆኚ እንዴ? አንድ ወይ ሁለት
ምንድነው ይሄ፣ ዝምብሎ ወይ ማለት
ወደቴ አረግሽን ወደቴ ወይዘሪት!
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
አንቺን ለማግኘት ስንቱን ወጣን ዳገት
ስንቴ ከፍ ዝቅ አልን፣ ባቀበት ቁልቁለት
በጉብዝናሽ ወራት እኛን አለመስማት
አይዞሽ ቻይበት ውበት ነው ኩራት
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ግና ቀንሽ ደርሶ ስትጣይ ግዳይ
እንዴት ይባላል ከቶ፣ አሁንም ወይ?
ምሽቱ ብልን፣ አንቺን ለሱ እኛ የተውንሽ
ነበር ባልሽ ላንቺ፣ ሠርክ በዓል እንዲሆንሽ
እንድትይ ይሆን’ዴ ዞረሽ
ወይ-ዞሮ ብለን የጠራንሽ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ለኑሮሽ ይሁን ለባልሽ ጐብጠሽ፣ አጎንብሰሽ
እንደ ዶሮ ያንንም ይሄንንም ስትቀማምሽ
ቅጥነትሽ የት ሄደ? ደሞ ያ ደም ግባትሽ?
ወለባሽ ይሆን ደርባባነትሽ፣ ወሰራ ዶሮ ያስመሰለሽ?
እና ይጣፍጣል ቢሉ ቢሽኮመኮም ያንቺ ዶሮ
ለግጥ ነው ሽሙጥ፣ አለ አንድ ነገር ዶሮ እና ወይ-ዞሮ
እና ባልተውት ነው ባል-እጦት ወይ ባልቴት ሳትባዪ
ለጠራሽ ሁሉ ዞር በዪ አሁን፣ ወይ በዪ፣ አቤት በዪ
ባልሽ ሲያልፍልሽም፣ አለሽ ብዙ ዓለም ገና
ሰተቶው ሁሉ ማንን ጠባቂ፣ ናፋቂ ሆነና
እንዲህ ነው ወይዘሮ እንዲህ ነው ወይዘሪት
የናንተው ዓለም፣ ለኛ ነው አዙሪት
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ወይ ብሎ ወይዘሪት
ወይ ብሎ ወይዘሮ
ያቺም ቄብ፣ እቺም ዶሮ።
ዶን ብሩኖ ወርሃ ታሳስ በዕለተ ረቡዕ በሚካኤል ቀን ተጻፈ። 2016
እንግዲህ ያው ቅዱስ ሚካኤል
ጠብቀኝ እንጂ ሌላ ምን ይባላል
ሰይፉ ከአፎቱ አንድ ጊዜ ተመዟል።
።
No comments:
Post a Comment