Thursday, December 29, 2016

ወረፋና ፈረቃ



ወረፋና ፈረቃ

አይወጡም አንድ ላይ፣ ጣይና ጨረቃ
አላቸው ሥርዓት አላቸው ፈረቃ
አይታይም የሰልፉ ደርዝ የሰልፉ መነሻ
የአቡሻኩር ምሥጢር፣ የቀን መዳረሻ

ቀንም ሰልፍ ይዞ ይቆማል ሪጋ፣ ይጠብቃል ወረፋ
ያዘግማል ወደፊት ጠብቆ ተራ፣ ሳያዝን ሳይከፋ
ብርሃንና ጸልማት ሲገቡ ፈረቃ
አንዱ እየተኛ ሌላው እየነቃ
አዎ፣ ቀንም ይጠብቃል ወረፋ
ሳያዝን ሳይከፋ፣ እርስ በርሱ ሳይጋፋ 
እስኪያልፍ ገፊ በተራው እየተገፋ
 

ሁሉንም ባንዴ አልሠራም አንድዬም እራሱ
ፊትና ኋላ አርጎ ነው ሁሉን የከወነው በራሱ
ባንዴም አልተበላም ዕፀ በለሱ
ተራ ጠብቀው ነው የተቃመሱ
በተራ ነው፣ ሥርዓት ያፈረሱ
በተራ ነው፣ ተሲዖል የፈለሱ

ሁሉም ነበረው ተራ፣ ሁሉም ነበረው ወረፋ
ያኔም ቢሆን ዔዶም ከምድር እስትጠፋ

ስንመጣም በወረፋ፣ ስንሄድም በወረፋ
አምላክ አደራህን ወረፋ ይስፋፋ
ጭቁን እስኪጨቁን ጭቆና ይንሰራፋ
ይኼ ነው እና የኛ ንግርት፣ ያ ታላቁ ተስፋ
ቆሞ መጠበቅ ተራ፣ ቆሞ መጠበቅ ወረፋ

ዶን ብሩኖ ወርሃ ታሳስ ዕለተ ረቡዕ በገብሪኤል ባመት በንግሡ፣ 2016

Thursday, December 22, 2016

ለሔዋን ዘር የገና ስጦታ።




ወይዘሪት እና ወይዘሮ
ያቺ ጉብል ወሲፋ፣ ባይን የምንቀጥባት
ያቺ መለሎዋ ኰረዳ፣ ቀጭኔዋ አንገት
ወይ ብላ ዞራ የምትከት ካዙሪት
ደርባባዋ ቆንጆ፣ የኛዋ ወይዘሪት

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ

ገና ብቅ ስትል ትትያለች ከሩቅ
አላት አንድ ነገር ልብን የሚሰልቅ
አንቺም ወይ ስትዪ እነሱም ወይ ሲሉ
ካንቺ የዋሉ፣ ባንቺ ቀሩ እንደዋለሉ

ማን ዐወቀና እንዳላት አዙሪት
ታምረኛ ዐጥንት፣ የኛዋ ወይዘሪት
ምርጫ ትሆኚ እንዴ? አንድ ወይ ሁለት
ምንድነው ይሄ፣ ዝምብሎ ወይ ማለት
ወደቴ አረግሽን ወደቴ ወይዘሪት!

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ

አንቺን ለማግኘት ስንቱን ወጣን ዳገት
ስንቴ ከፍ ዝቅ አልን፣ ባቀበት ቁልቁለት
በጉብዝናሽ ወራት እኛን አለመስማት
አይዞሽ ቻይበት ውበት ነው ኩራት

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ

ግና ቀንሽ ደርሶ ስትጣይ ግዳይ
እንዴት ይባላል ከቶ፣ አሁንም ወይ?
ምሽቱ ብልን፣ አንቺን ለሱ እኛ የተውንሽ
ነበር ባልሽ ላንቺ፣ ሠርክ በዓል እንዲሆንሽ

እንድትይ ይሆን’ዴ ዞረሽ
ወይ-ዞሮ ብለን የጠራንሽ

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ

ለኑሮሽ ይሁን ለባልሽ ጐብጠሽ፣ አጎንብሰሽ
እንደ ዶሮ ያንንም ይሄንንም ስትቀማምሽ
ቅጥነትሽ የት ሄደ? ደሞ ያ ደም ግባትሽ?
ወለባሽ ይሆን ደርባባነትሽ፣ ወሰራ ዶሮ ያስመሰለሽ?
እና ይጣፍጣል ቢሉ ቢሽኮመኮም ያንቺ ዶሮ
ለግጥ ነው ሽሙጥ፣ አለ አንድ ነገር ዶሮ እና ወይ-ዞሮ
እና ባልተውት ነው ባል-እጦት ወይ ባልቴት ሳትባዪ
ለጠራሽ ሁሉ ዞር በዪ አሁን፣ ወይ በዪ፣ አቤት በዪ
ባልሽ ሲያልፍልሽም፣ አለሽ ብዙ ዓለም ገና
ሰተቶው ሁሉ ማንን ጠባቂ፣ ናፋቂ ሆነና
እንዲህ ነው ወይዘሮ እንዲህ ነው ወይዘሪት
የናንተው ዓለም፣ ለኛ ነው አዙሪት

ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ
ባዜምኩላት ቅኔ ለደረሰው ቀኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ወዮልኝ ለኔ

ወይ ብሎ ወይዘሪት
ወይ ብሎ ወይዘሮ
ያቺም ቄብ፣ እቺም ዶሮ።


ዶን ብሩኖ ወርሃ ታሳስ በዕለተ ረቡዕ በሚካኤል ቀን ተጻፈ። 2016
እንግዲህ ያው ቅዱስ ሚካኤል
ጠብቀኝ እንጂ ሌላ ምን ይባላል
ሰይፉ ከአፎቱ አንድ ጊዜ ተመዟል።



Thursday, December 8, 2016

ቡና እና ቦለቲካ



ቡና እና ቦለቲካ
ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

ከጃቫ ኢንዶኔዥያ እስከ ሱራኔም ደቡብ አሜሪካ
ከጥንት እስተ ዛሬ ሲታይ የዚህች ዓለም ቦለቲካ
ተመስሎ ሲታይ እንደ ቡና ሥርዓት፣
ባለ ጊዜ ነገሥታት የሚያጣጥሙት፣
ሰልቅጠው ወቅጠው አፍልተው የሚጠጡት
ሕዝብ ቡና ነው፣ የቡና ዱቄት።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

አያ ምስኪን ቡና ኅዳር ሆነ ከፋ ተወልዶ
በእረኛው ካልዲ ክፋት ከምድሩ ተሰዶ
በታላቋ ጥንታዊት አክሱም ሆነ በዛሬዋ ኃያል አሜሪካ
ከኦቶማን ቱርክ፣ ከሞሮኮ ደርቡሽ፣ ወይ የኛዋ አፍሪካ
ቡንቹም፣ ኮፊ፣ ካፌ፣ ካፈ ቡና ይባል ቡን
ይወክላል ሕዝብን በእሳት የሚቆላውን
ብረት ምጣድ ላይ ተንጋሎ የሚንጨረጨረውን።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

እንደ ቡና አፊዋ፣ ቡና የምትቆላው፣ አፍላታም የምትጠጣው
ይኼ ሥርዓት የሚሉት የዛር ውላጅ፣ በሷ ያደረው ቃፊር አወሊያው።
ሕዝብ ነው የቡናው ፍሬ፣
ከብረት ምጣዱ የተጣደ
ኋላውን ሳያውቅ ለነፉቅራ፣
ለነዲራ እጅ ነስቶ የሰገደ።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

ይኼ ደሞ ዓማጺ ነኝ ባይ ዘነጐላ፣
የማያረው ጥሬ ቢቆላ፣ ቢቆላ፣
ቢልለት እሱም መልሶ ሕዝቡን የሚቆላ
ከንቱ የሚዳክር ላያመልጥ ከመቁያው ብረት ዘንግ
ከአስከባሪው ባለ ጠብ-መንጃው ርጉም ባለ ቤልጅግ።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

ብረት ምጣዱ ቢለያይ መቆያው በስመ አገር
ከፋርስ እስከ ኩባ፣ ከሃይቲ እስከ ቀጠር
በትምህርት ወግ ሚሉት ዘነዘና ሙቀጫ ተወቅጦ
እስኪልም ተሰልቅጦ
በጀበና በቡሽ የሚሉት ሕግ ታምቆ ተውጦ
ተንተክትኮ፣ ተንተክትኮ ላይቀርለት ህልፈት።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

በረከቦትና ማቶት የባሕልና ሃይማኖት ተቋማት
ወዲህ ደሞ አነስተኛ ሌማት፣ የቡና ገጸ-በረከት
ይኼ ጊርጊራው ዕጣኑ ፕሬስ ባይ ከንቱ ሁከት
ሕዝቡ ሲሆን ዱቄት፣ የነጋሢያኑ ፍጹም ስኬት
አቦል፣ ቶና ወይ ሲና፣ በረካ የሥርዓት ውጤት
ለቡና ፍሬው አንዳች ላይፈይድለት
ላይቀርለት መሆኑ በረከት፣ አጉል ጩኸት።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።

ስኒ በሚሉት አሰላለፍ መደብ፣ ከጀበናው ተቀድቶ
መቅረቡ አይቀርም ቡና ለንጉሡ ተፈልቶ
ቀሪው ትዝታ ነው እንዲያው እንቶ ፈንቶ
ታሪክ ተብሎ የሚነገር እንጉልፋቶ።

ሥርዓቱ ጋዋም ሆነ ቡና፣ ቡናካላ ቁጢም ሆነ አሻራ
ሕዝብ ጥሬ ቡና ነው ለዐሴር ዘር፣ ለንጉሡ የተዘራ።