አዛምድ አሉ "ቲቸር" ፈረንጁ መምሬ
አዛመድኩላቸው እኔም ጨማምሬ
ሰኔን ከሰኞ፣ ግንቦትን ከየካቲት
ወንፊት ከውኃ፣ ቤንዚንን ከእሳት
ጋንጩር ከደብተራ፣ እንጀራ ከወጥ
እጅ መንሻ ለባሻ፣ አስክሬንና ምስጥ
ሌባ ላመሉ ላይቀር መላሱ
ዓይንም ላፍንጫ ማልቀሱ
ያው አይቻል ነገር
አዲስ ማቀናበር
ከእባብ እንቁላል እርግብ ማስፈልፈል
ዝንጀሮን እርሻ ትቶ በሬን ለቆ በገደል
ዱባና ቅል ያለ ጠባዩ አይበቅል
የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ
ፈረስና ግልቢያ አህያና ልፊያ
ዶሮና ጥሬ እጅና አፍ ላይተላለፍ
አይጥና ድመት እርም ላይደጋገፍ
ሰኔ ብሎ ሰኞ የካቲት ብሎ ግንቦት
"ቲቸር" ቢፈልጉ ኤክስ ነው ይበሉት
እርስዎ በገዛ ራስዎ ያው በሚያውቁት
ሳቢና ተሳቢን አዛምድ ነው ያሉት
የካቲት 22፥ 2019 ዐርብ ማለዳ
ብሩክ በ.
No comments:
Post a Comment