Wednesday, December 25, 2019

ሄርሜቴክ ፍልስፍና ዳግም ውልደት፦ ፯ቱ ጥንታዊያን መርሆዎች

ሄርሜቴክ ፍልስፍና ዳግም ውልደት፦ ፯ቱ ጥንታዊያን መርሆዎች

ሄርሜቴክ ፍልስፍና ዳግም ውልደት፦ ፯ቱ ጥንታዊያን መርሆዎች
1. የሥነ አእምሮ (ሜንታሊዝም) መርሆ፦
ሁሉም ነገር አእምሮ ነው፤ ሕዋም አእምሮ ነች።
2. የተዛምዶ መርሆ፦
ልክ ከላይ እንዳለው፣ ልክ ከታች እንዳለው ተመሳሳይ ይሆናል። ልክ ከታች እንዳለው ከላይ ያለው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። በመሃል ያለው ከመሃል ይወጣል፤ ከመሃል የወጣው ከመሃል ይሆናል።
3. የንዝረት መርሆ፦
ምንም ባለበት የሚጸና የለም። ሁሉም ነገር ይንቀሳቀሳል፤ ሁሉም ነገር ይነዝራል።
4. የተቃርኖ መርሆ፦
ሁሉም ነገር በሁለታዊነት የተዋቀረ ነው፤ ሁሉም ነገር ተቃራኒ አለው፤ ሁሉም ነገር ተቃራኒ ተጣማጅ አለው፤ የሚመሳሰል እና የማይመሳሰል አንድ ናቸው፤ ተቃራኒዎች በተፈጥሮ ዐይን አንድ ናቸው፤ ሆኖም ግን በመጠን ደረጃ ይለያያሉ፤ ጽንፎች መጨረሻ ላይ ይገናኝሉ፤ ሁሉም እውነት ነው ግን ግማሽ እውነት ብቻ፤ ሁሉም ተቃርኖዎች ሊታረቁ ይችሉ ይሆን ይሆናል።
5. የሥልተ ምት መርሆ፦
ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ ይፈሳል፤ ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ። ሁሉም ነገር የራሱ ሞገድ አለው፤ ሁሉም ነገሮች ይነሣሉ ደግሞ መልሰው ይወድቃሉ፤ የፔንዱለም ውዝዋዜ በሁሉም ነገር ውስጥ ይንጸባረቃል፤ በግራ በኩል ያለው የፔንዱለም ጉዞ ወደ ቀኝ ካለው የፔንዱለሙ ጉዞ ጋር እኩል ርቀት ነው፤ ሥልተ ምት ተቻችሎ ይቀጥላል።
6. የምክንያት እና ውጤት መርሆ፦
እያንዳንዱ ምክንያት የራሱ ውጤት አለው፤ እያንዳንዱ ውጤት የራሱ ምክንያት አለው፤ ሁሉም ነገር የሚሆነው “ዕድል ያልታወቀ ሕግ ስያሜ” ነው የሚለው ሕግ መሠረት ነው። በርካታ የተለዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ ሆኖም ምንም ከዚህ ሕግ የሚወጣ ነገር የለም።
7. የሥነ ጾታ መርሆ፦
ጾታ በሁሉም ነገር ውስጥ አለ፤ ሁሉም ነገር የየራሱ ተባዕታይ እና አንስታይ መርሆዎች አሉት፤ ጾታ በሁሉም ነገር ላይ ይንጸባረቃል።
The Hermetic Revival: 7 Ancient Principles
1. The Principle of Mentalism:
The All is mind; The Universe is Mental.
2. The Principle of Correspondence:
As above, so below; as below, so above. As within, so without; as without, so within.
3. The Principle of Vibration:
Nothing rests; Everything moves; Everything vibrates.
4. The Principle of Polarity:
Everything is dual; Everything has poles; Everything has its pair of opposites; Like and unlike are the same; Opposites are identical in nature, but different in degree; Extremes meet; All truths, are but half-truths; All paradoxes may be reconciled.
5. The Principle of Rhythm:
Everything flows, out and in; Everything has its tides; All things rise and fall; The pendulum swing manifests in everything; The measure of the swing to the right is the measure of the swing to the left; Rhythm compensates.
6. The Principle of Cause & Effect:
Every cause has its effect; Every effect has its cause; Everything happens according to law’ Chance is but a name for law not recognized’ There are many planes of causation, but nothing escapes the law.
7. The Principle of Gender:
Gender is in everything; Everything has its masculine and feminine principles; Gender manifests on all planes.
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ በፍጥነት እንዳዘገጁት የዕለተ ፲፬ ጥር 2019 እሳቤ

Friday, October 25, 2019

እንትን እና እንትና

እንደምን አለህ ጋሽ እንትን
እንደምን አለሽ እትዬ እንትን
አንተስ አቶ እንትና እንደምን ከርመሃል
አንቺስ ወይዘሮ እንትና እንደምን ይዞሻል
"ድሮስ እንትን" ብለህ ሰው የፈረጅከው
"ድሮም እንትን" ብለሽ ሰው የፈረድሽው
"እውነትም እንትን" ብለህ ነገር ያሳረግከው
"እውነትም እንትን" ብለሽ የደመደምሽው
እንትናን በእንትንነቱ አንተ እንትን ስትለው
እንትናን በእንትንነቱ አንቺ እንትን ስትይው
እንትናም ይህን ሰምቶ ለእንትንነትህ አንተን "እንትን" ካለህ
ያው እንትን ለእንትን ጥርስ ላይሳበር አንተስ ምኑ ነው የከፋህ?
እንትናም ያንን ሰምታ ለእንትንነትሽ አንቺን እንትን ካለችሽ
እንትን ለእንትን አብረህ አዝግም ነውና ምኑ ነው የከፋሽ?
እንትን ወቃሽ አያርገኝ እንዳላሉ በሥራ ሕያዋን ቀደምት አበው
እነ እንትናም እንትናን ሰርክ ካነሱ በቁም ሙታን እነማን ናቸው?
እና ይኼ ሁሉ እንትን ገብቶህ ከተረዳኸው
እና ይኼን ሁሉ እንትን ገብቶሽ ከፈታሽው
ወንድሜ ሙት ተመርመር ችግሩ ካንተ ነው
እህቴ ሙች ተመርመሪ ችግሩ ካንቺ ነው
አሊያም ከሌላ ፕላኔት ነው የመጣኸው
ከሌላ ዓለም ነው እዚህ የተገኘሽው
እንትንም እንትናም እንደ እንትን ሁሉ ነውና እንደ ፈቺው
አንተ እንትናን እንትን ብትለው እዛ ቤት ሌላ እንትን ነው
የሰው መጨረሻ፣ የነገር ጥማት አራራው ጥግ ሲደርስ
እንትን ማለት እንትን ብሎ ሞልቷል ታምሶ የሚታመስ
ሳይጠሩት አቤት ባይ ሳይልኩት ወዴት የሚል አብዝቶ
የእንትን ጎረቤት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ነው ከቶ




በጥቅምት ሚካኤል ማግስት 2019
ከሰላሙ እምዬ እንትና ሰፈር።

Thursday, July 4, 2019

ለፈገግታችሁ፣


ለፈገግታችሁ፣
በጌታቸው ታረቀኝ ከተጻፈው አቤቶ ልጅ እያሱ ከሚለው ታሪካዊ ድራማ መግቢያ ላይ የተወሰደ
ገቢር 1
ትዕይንት 1
መብራት ሲጠፋ መጋረጃው ከመከፈቱ በፊት ለተመልካች የሚነበብ
«የተከበራችሁ ተመልካቾቻችን ዛሬ የምትመለከቱት . . . »
መጋረጃ ይነሳል። . . . በጨለማው ነጋሪት ይሰማል። ጥሩምባ ይሰማል . . . (ጣሴ በባህላዊ የቤተመንግስት ስርአት ለብሶ ይገባል።)
ጣሴ (በአዋጅ ነጋሪ ስልት) . . . ስማ ስማ . . . ጆሮ ያለህ ስማ . . . የሰማህ ላልሰማው አሰማ . . . ስሚ ስሚ ጆሮ ያለሽ ስሚ . . . የሰማሽ ላልሰማችው አሰሚ . . . አፈሩ በጎርፍ ተሸርሽሮ እንዳያልቅ አቧራው እየተነሳ በንፋስ እንዳይቦን ከፈረንጅ አገር አስመጥቼ የተከልኩትን የባህር ዛፍ እየዘነጠፍክ ጥርስህን የምትፍቅ የምትፍቂ . . . ጥርስ አባታችሁ ይርገፍና በድዳችሁ ነው የማስቀራችሁ። ቢሻው ጥርሳችሁ በስብሶ ይርገፍ እንጂ የባህር ማዶ ዛፌን እንዳትነኩ ብያለሁ!!! የኮረንቲ መብራት ተከተማው አልፎ በየባላገሩ እንዲደርስ የዘረጋሁትን የመዳብ ሽቦ እየበጠሳችሁ የእጅ አምባርና የጆሮ ጉትቻ የምትሰሩና የምታጌጡ . . . እጅ እና እግራችሁን እያስቆረጥኩ መቀጣጫ ነው የማደርጋችሁ . . . በነገይቱ ተሲአት ደግሞ የንጉሠ ነገሥት እያሱ አምስተኛ . . . የንግስ በዓል በታላቁ ቤተ መንግስት ስለሚከበር ሙላሽ ሁላ መጥተሽ ምሳ እንድተበይ ተጠርተሻል!! በማትመጡት ላይ ግን . . .

Tuesday, June 4, 2019

በሕይወትህ በጥብቅ ልታከብራቸው የሚገቡ ስድስት ግላዊ መመሪያዎች፦


1. ብቻህን ስትሆን ፥ ሐሳብህን ተቆጣጠረው።
2. ከጓደኞችህ ጋር ስትሆን ፥ ምላስህን ተቆጣጠረው።
3. ንዴት ላይ ስትሆን ፥ ቁጣህን ተቆጣጠረው።
4. ከሌሎች ጋር ስትሆን ፥ ዓመልህን ተቆጣጠረው።
5. ችግር ላይ ስትሆን ፥ ስሜትህን ተቆጣጠረው።
6. ፈጣሪ በረከቱን ሲሰጥህ ፥ ራስ ወዳድነትህን ተቆጣጠረው።
ትርጉም ከከሣቴ ብርሃን ቡሩክ
ምንጭ፦ #Daily Prayers
Image may contain: text

Thursday, April 18, 2019

«ጌ» ፊደል እና ትርጉሙ


«ጌ» እና ትርጉሙ
የ«ጌ» ትርጉም - እንደ «ጋ» (እዚህጋ፣ እዚያጋ ወዘተ) በቃል መጨረሻ እየገባ ምድር ቦታ ስፍራ ተብሎ ይተረጐማል። (ማስረጃ እጅጌ፣  ባለጌ፣  ገደልጌ፣  ገዳምጌ፣  ጕራጌ፣  ግርጌ፣  ደረስጌ፣  ወገብጌ ዋንዛጌ፣  ሐረርጌ፣  ይተጌ፣  ላምጌ፣  ንብጌ፣  ዐዲስጌ፣  ዕጨጌ (ሐፄጌ)  ዐምባላጌ፣  ዐንገትጌ፣  ፍንጥርጌ፣  ቅዱስጌ፣  ራስጌ፣  ሰላምጌ የኹሉንም ትርጓሜ በየስፍራው ከዚህ በታች ይመለከቷል። ትግሬ ሐባብም አገርን ድጌ ይለዋል።
እጅጌ = 1. የእጅ፣  ማግቢያ ፤-እጅ። 2. የእጅ ልብስ ወይም እጁን እንዳይበርደው የእጅ ማጥለቂያ በቀሚስ ላይ የሚሰፋ እጅጌ የእጅ ልብስ።
ባለጌ = 1. አግድሞ አደግ፣  ስድ፣  መረን፣  ያልተቀጣ፣  ያልተገሠጸ፣  ነውረኛ፣  ነውር ጌጡ አያት ያሳደገው ልጅ። «ባለጌን ካሳደገው የገደለው ይጸድቃል።» ወይም «ባለጌ የጠገበ ለት ይርበው አይመስለውም።» እንዲሉ። 2. ባለምድር ፤ -ባለገ 3. ያልተቀጣ ሕገ ወጥ ነውር ነቀፋ የሚኾን ነገርን የሚሠራ። 2. «ጌ» ቦታን አመልካች ነው ለጊዜው የነቀፋ ስድብ ስም ይመስላል ባላባት ባለርስት ማለት ነው። «ጌ» ማለት ቤት ማለት ነው። ባላባት ባለርስት ለማለት ባለጌ ይባል ነበር ዱሮ።
ገደልጌ = በይፋት ያለ ቀበሌ ገደላም ምድር
ገዳምጌ = በታች ወግዳ ያለ አገር የገዳም ምድር ማለት ነው።
ጕራጌ = 1. ክፍል፣  የጕራጌ አገር። ቤት ጕራጌ እንዲሉ። በዝርዝር ሲቈጥሩት ግን ነገዱና አገሩ እስከ ፳፭ ይደርሳል። 2. የውል ስም የጉራጌ ሕዝብ ወይም የጉራጌ አገር ከጕርዐ ፈልሰው ወደ ጉራጌ አገር መጥተው ሰባት ቤት ጕራዐጌን ወልደው የሚኖሩ ሕዝብ ናቸው።
ግርጌ = የእግር፣  ስፍራ -እግር
ደረስጌ = ደረስጌ ማርያም ደባርቅ፣ ጎንደር ውስጥ ደረስጌ (ደብረ-ስጌ ከሚለው ስም የመጣ)፣ እሚባል ቦታ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው። በዘመነ መሳፍንት ገነው የነበሩት ደጃች ውቤ እራሳቸውን ለማንገሥ ሲሉ የጀርመኑን ሠዓሊ እና ሳይንቲስት ዶክተር ሺምፐር በመቅጠር 1840ዎቹ መጀመሪያ ያስገነቡት ቤተክርስቲያን ነው። በኋላ ላይ ከወደፊት ዓፄ ቴዎድሮስ ጋር በዚሁ አካባቢ ጦርነት ገጥመው ስለተሸነፉ፣ ራስ ውቤ ለሥርዓተ ንግሣቸው ባሠሩት ቤተ ክርስቲያን ዓፄ ቴዎድሮስ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው ዘውድ ጭነው ነገሡበት። ይሄውም 1847 መሆኑ ነው። 2. አጼ ቴዎድሮስ ንግሥናቸውን ያወጁበት ሰገነት፣ ስሜን ጃናሞራ፣ ደረስጌ ማርያም
ወገብጌ = 1. ጥብጣብ፣ ቀበቶ የሚገባበት፣  በስተላይ ያለ ውስጠ ክፍት፣  የሱሪ ጫፍ፣  በወገብ ላይ የሚውል የወገብ ስፍራ። 2. የሱሪ ጥብጣብ ሙያ ስፌት በወገብ ላይ የሚውል ነገር ኹሉ ወገብጌ ይባላል።
ዋንዛጌ = የዋንዛጌ ( ዋንዛ) ትርጉም - ያገር ስም፣ በታችኛው ወግዳ ሰሜን በተጕለት ያለ አገር። ዋንዛ ያለባት ምድር ማለት ነው።
ሐረርጌ = ሐረር ለዐዲስ አበባ ምሥራቅ የሚኾን ብዙ አውራጆች ያሉት ትልቅ ከተማ። የሐረርጌ ፤ (ሐረር - ጌ) ትርጉም - ምድረ ቈላ፣  በረሃ፣  ከአዋሽ ማዶ ያለ አገር፣ የዱሮ ዘመን ጠቅላይ ግዛት።
ይተጌ = የእተጌ ትርጉም  -ይተጌ -እት ፤ የምድር እመቤት። የእተጌ (ዎች) ፤ እኀተ ሐፄጌ) ትርጉም - ይተጌ፣  ንጉሥ፣  እቴ የሚላት፣  የንጉሥ ሚስት፤ ባለኩል፣  ርስቱን፣  ጕልቱን እንደ እት፣  ተካፍላ የምትገዛ፣  የሴት ንግሥት። (ግጥም) ዐሊ ማን ይላታል ሲጠራ እናቱን ፤ እኛስ እንላለን እተጌ መነን። እተጌ ሰብለ ወንጌል፣  እተጌ ጣይቱ እንዲሉ። ጌን ተመልከት። አና፣  የ፣  ተወራራሽ ስለ ኾኑ እተጌ፣  ይተጌ ተብሎ ይነገራል።
ላምጌ = ፎገራ ውስጥ ከደራ አጠገብ ያለች መንደር።
ንብጌ = አገር -ናበ። ንብ ያለበት አገር በቡልጋ ውስጥ የሚገኝ። የግእዝ መጽሐፍ መሐግል ይለዋል ፤ ማሰሪያ ማለት ነው።
ዐዲስጌ = በተጕለት ወስጥ የሚገኛ አገር ከዜጋ ወደም በስተግራ ያለ ቀበሌ። (ሐዲስ - ጌ) ሐዲስ የሚባል ሰው ምድር።
ዕጨጌ (ሐፄጌ) = አቡን ጳጳስ። (ግጥም) መኳንንቱ ሠለጠኑ የጨጌን አገር እመኑ። እኔ የምፈራው ይህነን ካቡን በላይ መኾን። የምድር ዕጮኛ ፤-ዐጨ ፤ ዕጨጌ። 2. የምድር፣ ዕጮኛ ፤ -ዐጨ። 3. [ነገር ስም] የወላይታ ቋንቋ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በወላይታ አገር ሞተሌሚ የሚባለውን ንጉሥ አስተምረውት ከዐረመኔነት ወደ ክርስትና ስለ መለሱት የወላይታ ሐዋርያ ለማለት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጨጋ ይሉአቸው ነበርና እጨጌ ከዚያ ከወላይታ ቋንቋ የተወረሰ ቃል ነው። 4. የደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህር ዕጨጌ ሊቀ ካህናት ከመንግሥት ሲሶ ግብር መቀበል።
ዐምባላጌ =  1. በትግሬ ግዛት በደቡብ የሚገኝ ትልቅ ጋራ አምባ። 2. የዐምባላ ምድር ፤ አገር። ዐምባ ዐላጊ ቢል ግን ትርጓሜው ሌላ ነው። 3. በትግሬ ግዛት በደቡብ የሚገኝ ትልቅ ጋራ አምባ።
ዐንገትጌ = 1. ያንገት ስፍራ ፤ ዐንገትን የሚሸፍን የእጀ ጠባብና የቀሚስ የጥብቆ ክሣድ ፤ በስተላይ ያለ ጫፍ (ዘፀ ፳፰፡፴፪)። 2. በአንገት ላይ የሚውል ልብስ የካፖ የኮት የእጀ ጠባብ ቅንፋት (ክሳድ) የሚውልበት አንገትጌ ይባላል።
ፍንጥርጌ = በጠራ ውስጥ ያለ ቀበሌ የፍንጥር ምድር ማለት ነው።
ቅዱስጌ = በቡልጋ አውራጃ ያለ አገር የተቀደሰ ምድር ወይም (ቅዱስ - ጌ) አንድ ቅዱስ የኖረበት የጸለየበት የሰበከበት የቅዱስ አገር ምድር ማለት ነው። ነገር ግን ምድር የምትነገረው በሴት አንቀጽ መኾኑን አስተውል።
ራስጌ = 1. በስተራስ በኩል ያለ ስፍራ የግርጌ አንጻር። 2. [ነገር ስም] ከወደላይ የሚኾን ነገር በመኝታ ጊዜ ራሱን የሚያሳርፍበት ወደ ራስ ወገን
ሰላምጌ = (ሰላምጌ ማሪያም) የሰላምጌ ማርያም ቤተክርስትያን በሰቆጣ ወረዳ 031 ቀበሌ ሰላምጌ በተባለ ጎጥ የምትገኝ ጥንታዊ ቤተክርስትያን ነች። ሰላምጌ ማርያም ስያሜዋን ያገኘችው እዚያው ቀበሌ ውስጥ ከሚገኝና ‹‹ የሰላም ዋሻ ›› የሚል ትርጉም ከተሰጠው ዋሻ ነው። ለዐርባ ዓመታት በዋሻው ውስጥ እንደቆየችና በኋላ ግን ሲራክ የሚባል መነኩሴ ድንኳን በመትከል አስቀመጣት ኋላ፣ ኋላ 12 መነኩሳት ደግሞ የየራሳቸው ባለ አንድ ክፍል የጸሎት ቤት በመትከል መግቢያም መውጫም ያለው በር በመሥራት የጸሎት ያደርሱ ነበር በዚያን ግዜ እነዚህ 12 ጸሎት ቤቶች ተገጣጥመውም 12 ክፍሎች ያሉት እቤተ መቅደስ ሆኑ። ይህም ቤተ መቅደስ የተሠራው ከክርስቶስ በፊት እንደሆነ ይነገራል ዐሥራ ሁለት ክፍሎች ዛሬም ድረስ በቤተክርስትያኑ ህንፃ ውስጥ ይገኛሉ። የጥንት አሠራራቸውም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት አልተቀየረም። የሰላምዕ ማሪያም ቤተክርስቲያን የዉስጥ ክፍል ለዊያዊን ካህናት ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ኦሪት አምልኮተ እግዚአብሔር የሚካሄድባቸው ቤተ እምነቶችን እንደሠሩ በታሪክ ይወሳል። ከነዚህም መካከልም ጣና ቂርቆስ፣ መርጡላ ማርያም፣ ደብረዳምና ተድባበ ማርያም የሚጠቀሱ ናቸው። ሰላምጌ ማርያም ከእነዚህ አቻ እድሜ ያላትና በሕገ ኦሪት አምልኮት እግዚአብሔር ይካሄድባት እንደነበረ እና ከአክሱም ጽዮን ቀጥላ በዘመነ ኦሪት ከተሠሩ ቤተ እምነቶች አንዷ እንደነበረች በታሪክ ይነገራል። ሰላምጌ ማርያም የበርካታ ጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት ነች። ጥር 21 የንግሥ በዓሏ ነው።
ድጌ =  1. መቀነት ፤-ደገደገ። 2. [ነገር ስም] ሃያ ዐምስት ወይም ሠላሳ ክንድ የሚሠራና ወንድ ወደ መንገድ ሲሔድ የሚታጠቀው (አስ) ድጉን ሸብ አደረገ (መቀነት ([ግዕዝ])። (ከግእዝ በቁሙ መቀነት የሆድ ካሳ የወገብ ምሳ ወገብ የሚያጠና የሚደግፍ። መቀነት)

በከሣቴ ብርሃን ከዚህም ከዚያም የተቀነበበ