Friday, November 2, 2018

ነገረ ሰብ (ከልጅነት እስከ ሞት)

ነገረ ሰብ (ከልጅነት እስከ ሞት)
 
ከዐራት ተፈጥሮ ምንጮች እንደ መፈጠሩ ባሕሪያቱና ዕድሜውም ዐራት ናቸው፥ በዐራት ይፈረጃሉ፦
 
 
፩ ነፋስ (ልጅነት) ፦ ከፅንስ እስከ ወጣትነት (እስከ ሃያዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን መድረሻው አይታወቅም። ጣፋጭ ነው። ሕይወት ነው። አይጠገብም። ይሮጣል፣ ይቦርቃል፣ ይፈነድቃል፣ በሕልም በምናብ ብዙ ይጓዛል። ድንብር መልክ የለውም። ሁሉም ይቀበለዋል። ሁሉም ይፈልገዋል።
 
 
፪ እሳት (ወጣትነት) ፦ ከወጣትነት እስከ ጉልምስና (እስከ ዐርባዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን ብርሃን ነው። ሙቀት ነው። ኃይል ነው። ያለማ ዘንድ ማጥፋቱ ግድ ነው። ልብ ብለው ካላዩት የማይደክም አጥፊ ነው። በሚገባ ከያዙት የማይለግም አልሚ ነው። ዐለም ሕይወትም ነው። ነፋስ ሲያገኝ እንደ ነፋስ ይሆናል የቅርብ ዘመዱ ነውና።
 
 
፫ ውኃ (ጉልምስና) ፦ ከጉልምስና እስከ ሽምግልና (እስከ ስልሳዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን መረጋጋት ነው። ከጥም በኋላ ያለው እርካታ፣ ከእርካታ በኋላ ያለው እፎይታን ይለመዳል። ርጋት፣ ቅዝቃዜ፣ ትዕግሥት መገለጫው ነው። ቀጣይ ሕይወት በእጁ ነው። መሪ ነው። ሠርሥሮ በየጥሻው ይገባል። እሳትን ማጥፋት የሚችል ጉልበት አለው፣ ውኃ የእሳት አለቃ ነው።
 
 
፬ አፈር (እርጅና) ፦ ከሽምግልና እስከ እርጅና (ከስልሳ እስከ ሰማኒዎቹ)። ጠባዩ ሲበይን መቃብር ነው። ይቀዘቅዛል። ፍጹም ርጋት ነው። በሳል ነው። ፍሬው ሁሉ መልካም ነው። ዘመኑም ሁሉ ጣፋጭ እና የማይጠገብ ነው። የሕይወትን ጣዕም ዐውቆ ያሳውቃል። ሕይወት ትቀጥል ዘንድ ይሞግታል። በነፋስ፣ በእሳት፣ በውኃ ዘመኑ የተዘራበትን ያፈራል። ለኅልፈት ይመቻቻል።
 
 
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ በዛሬው ቀን በተክልዬው ጥቅምት፣ (2018 በራስ አቆጣጠር) እንደታያቸው ስለ ነገረ ሰብ ጻፉ።
ሸገር ዐዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment