Wednesday, November 21, 2018

ከታሪክ ማኅደር ፩

ከታሪክ ማኅደር
ምን ያክል አማርኛ ይችላሉ ? ራስዎን ይፈትሹ !
የዓፄ ምኒልክ ደብዳቤ፦ (ደብዳቤ ቊጥር ፩ ሺ ፯፻፲፭ 1715)
ይድረስ ከራስ ሚካኤል
ይህ ፋሪስ ወልደ ማርያም የሚባለው ቦረና ነገሌ የደጃዝማች ካሣ አሽከር ቤቴ ተቃጥሎ ሌባ ሻይ ቢያመጣ እኔ ቤት ተኛ። እኔም በራስ ሚካኤል ቃል አስደግሜ ተመልሶ እዚያው ተመልሶ ተኛ። ይህንኑ ለአፈ ንጉሥ ነሲቡ ጮኬ ከሰይዱ ጋር አጋጥመውኝ ሌባ ሻዩም ሁለት ግዜ አንተው ቤት ከተኛ ክፈል ብለውኝ ቤቴ ሠላሳ ብር ርስቴ አራት ብር ያወጣል ቢሉኝ እንደገና ጮኬ የአገር ሽማግሌ ጎረቤት በገመተው ክፈል በሚል ለአፈ ንጉሥ ማኀተም ወስጄ ሽማግሌ በገመተው ክፈል በሚል ለአፈ ንጉሥ ማኅተም ወስጄ ሽማግሌ በገመተው ልክፈል ሁለት ዋስ ጨርቼ እንገማመት ሳይለኝ ከርሞ አሁን በዓመቱ ከአፈ ንጉሥ ነሲቡ ማኅተም አላወጣም ብሎ ከሶ ማኅተሙም ራስ ሚካኤል ዘንድ ጠፋ። ከዋሶቹ ሠላሳ አራት ብር ተቀበሏቸው። ይህንኑም እንደገና ጮኼ ማ[ኅ]ተም አምጣ አሉኝ ብሏልና ከዋሶቹ የተበላ ሠላሳ አራት ብር ይመለስና የአገር ሽማግሌ ቤቱን የሚያውቅ ጎረቤት በገመተው ይክፈል።
ሐምሌ ፴ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ።
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ ከጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ከሚል መጽሐፍ ላይ ገልበጠው እንደተየቡት
ኅዳር ሚካኤል፥ 2018 (በራስ አቆጣጠር)

Friday, November 2, 2018

ነገረ ሰብ (ከልጅነት እስከ ሞት)

ነገረ ሰብ (ከልጅነት እስከ ሞት)
 
ከዐራት ተፈጥሮ ምንጮች እንደ መፈጠሩ ባሕሪያቱና ዕድሜውም ዐራት ናቸው፥ በዐራት ይፈረጃሉ፦
 
 
፩ ነፋስ (ልጅነት) ፦ ከፅንስ እስከ ወጣትነት (እስከ ሃያዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን መድረሻው አይታወቅም። ጣፋጭ ነው። ሕይወት ነው። አይጠገብም። ይሮጣል፣ ይቦርቃል፣ ይፈነድቃል፣ በሕልም በምናብ ብዙ ይጓዛል። ድንብር መልክ የለውም። ሁሉም ይቀበለዋል። ሁሉም ይፈልገዋል።
 
 
፪ እሳት (ወጣትነት) ፦ ከወጣትነት እስከ ጉልምስና (እስከ ዐርባዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን ብርሃን ነው። ሙቀት ነው። ኃይል ነው። ያለማ ዘንድ ማጥፋቱ ግድ ነው። ልብ ብለው ካላዩት የማይደክም አጥፊ ነው። በሚገባ ከያዙት የማይለግም አልሚ ነው። ዐለም ሕይወትም ነው። ነፋስ ሲያገኝ እንደ ነፋስ ይሆናል የቅርብ ዘመዱ ነውና።
 
 
፫ ውኃ (ጉልምስና) ፦ ከጉልምስና እስከ ሽምግልና (እስከ ስልሳዎቹ)። ጠባዩ ሲበየን መረጋጋት ነው። ከጥም በኋላ ያለው እርካታ፣ ከእርካታ በኋላ ያለው እፎይታን ይለመዳል። ርጋት፣ ቅዝቃዜ፣ ትዕግሥት መገለጫው ነው። ቀጣይ ሕይወት በእጁ ነው። መሪ ነው። ሠርሥሮ በየጥሻው ይገባል። እሳትን ማጥፋት የሚችል ጉልበት አለው፣ ውኃ የእሳት አለቃ ነው።
 
 
፬ አፈር (እርጅና) ፦ ከሽምግልና እስከ እርጅና (ከስልሳ እስከ ሰማኒዎቹ)። ጠባዩ ሲበይን መቃብር ነው። ይቀዘቅዛል። ፍጹም ርጋት ነው። በሳል ነው። ፍሬው ሁሉ መልካም ነው። ዘመኑም ሁሉ ጣፋጭ እና የማይጠገብ ነው። የሕይወትን ጣዕም ዐውቆ ያሳውቃል። ሕይወት ትቀጥል ዘንድ ይሞግታል። በነፋስ፣ በእሳት፣ በውኃ ዘመኑ የተዘራበትን ያፈራል። ለኅልፈት ይመቻቻል።
 
 
ከሣቴ ብርሃን ቡሩክ በዛሬው ቀን በተክልዬው ጥቅምት፣ (2018 በራስ አቆጣጠር) እንደታያቸው ስለ ነገረ ሰብ ጻፉ።
ሸገር ዐዲስ አበባ