Monday, June 12, 2017

ለባለወይራ ቅጠሉ ጥምጣማም

ያኔ በሞኝ ዘመን በየዋሆቹ
እረኛው ሲሞት ለበግ ግልገሎቹ
ሕሊና ካገር ሳትሰደድ እውነትም ሳታብድ
አንድ ለብዙ ብዙ ለአንድ ለመኖር ሲገደድ
ለጋራ ጥቅም ለአንድነት ሀብቱ
ሰው ሲሞት ለማተብ ለእምነቱ
የምንትስዬ ቦታ፣ ሚና ግራ ቢገባህ
ዋሾውን አስመሳይ መቅጣት ቢዳዳህ
ያኔ በዛ ዘመን ቅዱስ፣ በተባረከው
"እውነት ማነው ማንትስ?" ነበር ያልከው
ያኔ በዛ ዘመን ሳይረክስ በፊት ሰው
*****
አሁን ግን በዚህ ቆቅ ዘመን በቁራዎቹ
ቄራ በተስፋፋበት ሲሳይ ለአሞሮቹ
አንዲት ብልት ብቻ ናት በጣም ኢምንት
የማይሸጥ የለም አሁን ጸጉርም ዋጋ አላት
*****
እና ባለወይራው ቅጠል ዘውድ፣ የዋሁ ዳኛ
እንኳንም አላየህ በል በሰላም ባለህበት ተኛ
ብትጠይቅ ባትጠይቅ ላንተ ማን ቦታ ሰጥቶ
ራሱን እየቸበቸበ ነው ሰው በዝቶ አብዝቶ
እና በዚህ ደግ ዘመን ሰው አካሉን የሚሸጥበት በችርቻሮ
ማነው ምንትስ ብትል ማን ሊሰማ ማን ሊሰጥህ ጆሮ
ሁሉም ተነካክቷል ራስን ሸጦ ማደርን ተክኖበታል
ዘመነ ምንትስ መሆኑን ምንትስ ሁሉ ገብቶታል
ራሳችንን አንድ ባንድ ቆጥረን ስናከራይ
በልቶ ለማደር ለአዱኛ ክብር ለሆድ ሲሳይ
ባለወይራው ቅጠል ጥምጣም ምንኛ እግዜሩ ወዶሃል
ይኼን ሁሉ ሸቀጥ ሳታይ በጊዜ ከቤቱ ወስዶሃል
ላንዲት ምንትስ ሲገርምህ አገሩ ሁሉ ምንትስ ሆኖልሃል
ሰኔ 3፣ 2017
ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን
በዓመቱ ላይ የተጨመረው ስምንት ዓመት
ሌላ ምሥጢር የለውም ቀድሞ ነው ለማርጀት
ብ. በየነ

No comments:

Post a Comment