«ጌ»
እና ትርጉሙ
የ«ጌ»
ትርጉም - እንደ «ጋ» (እዚህጋ፣ እዚያጋ ወዘተ) በቃል መጨረሻ እየገባ ምድር ቦታ ስፍራ ተብሎ ይተረጐማል። (ማስረጃ፦
እጅጌ፣ ባለጌ፣ ገደልጌ፣ ገዳምጌ፣ ጕራጌ፣ ግርጌ፣ ደረስጌ፣ ወገብጌ ዋንዛጌ፣
ሐረርጌ፣ ይተጌ፣ ላምጌ፣ ንብጌ፣ ዐዲስጌ፣ ዕጨጌ (ሐፄጌ)፣ ዐምባላጌ፣ ዐንገትጌ፣ ፍንጥርጌ፣ ቅዱስጌ፣ ራስጌ፣ ሰላምጌ ፤ የኹሉንም ትርጓሜ በየስፍራው ከዚህ በታች ይመለከቷል። ትግሬ ሐባብም አገርን ድጌ ይለዋል።
እጅጌ
= 1. የእጅ፣ ማግቢያ ፤-እጅ። 2. የእጅ ልብስ ወይም እጁን እንዳይበርደው
የእጅ ማጥለቂያ በቀሚስ ላይ የሚሰፋ እጅጌ የእጅ ልብስ።
ባለጌ
= 1. አግድሞ አደግ፣ ስድ፣ መረን፣ ያልተቀጣ፣ ያልተገሠጸ፣ ነውረኛ፣ ነውር ጌጡ ፤ አያት ያሳደገው ልጅ። «ባለጌን ካሳደገው
የገደለው ይጸድቃል።» ወይም «ባለጌ የጠገበ ለት ይርበው አይመስለውም።» እንዲሉ። 2. ባለምድር ፤ -ባለገ 3. ያልተቀጣ ሕገ ወጥ ነውር ነቀፋ
የሚኾን ነገርን የሚሠራ። 2. «ጌ» ቦታን አመልካች ነው ለጊዜው የነቀፋ ስድብ ስም ይመስላል ባላባት ባለርስት ማለት ነው። «ጌ»
ማለት ቤት ማለት ነው። ባላባት ባለርስት ለማለት ባለጌ ይባል ነበር ዱሮ።
ገደልጌ
= በይፋት ያለ ቀበሌ ፤ ገደላም ምድር
ገዳምጌ
= በታች ወግዳ ያለ አገር ፤ የገዳም ምድር ማለት ነው።
ጕራጌ
= 1. ፯ ቱ ክፍል፣ የጕራጌ አገር።
፯ ቤት ጕራጌ እንዲሉ። በዝርዝር ሲቈጥሩት ግን ነገዱና አገሩ እስከ ፳፭ ይደርሳል። 2. የውል ስም የጉራጌ ሕዝብ ወይም
የጉራጌ አገር ከጕርዐ ፈልሰው ወደ ጉራጌ አገር መጥተው ሰባት ቤት ጕራዐጌን ወልደው የሚኖሩ ሕዝብ ናቸው።
ግርጌ
= የእግር፣ ስፍራ ፤-እግር
ደረስጌ
= ደረስጌ ማርያም ደባርቅ፣ ጎንደር ውስጥ ደረስጌ (ደብረ-ስጌ ከሚለው ስም የመጣ)፣ እሚባል ቦታ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው። በዘመነ መሳፍንት ገነው የነበሩት ደጃች ውቤ እራሳቸውን ለማንገሥ ሲሉ የጀርመኑን ሠዓሊ እና ሳይንቲስት ዶክተር ሺምፐር በመቅጠር በ1840ዎቹ መጀመሪያ ያስገነቡት ቤተክርስቲያን ነው። በኋላ ላይ ከወደፊት ዓፄ ቴዎድሮስ ጋር በዚሁ አካባቢ ጦርነት ገጥመው ስለተሸነፉ፣ ራስ ውቤ ለሥርዓተ ንግሣቸው ባሠሩት ቤተ ክርስቲያን ዓፄ ቴዎድሮስ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው ዘውድ ጭነው ነገሡበት። ይሄውም በ1847 መሆኑ ነው። 2. አጼ ቴዎድሮስ ንግሥናቸውን ያወጁበት
ሰገነት፣ ስሜን ጃናሞራ፣ ደረስጌ ማርያም
ወገብጌ
= 1. ጥብጣብ፣ ቀበቶ የሚገባበት፣ በስተላይ ያለ
ውስጠ ክፍት፣ የሱሪ ጫፍ፣
በወገብ ላይ የሚውል ፤ የወገብ ስፍራ።
2. የሱሪ ጥብጣብ ሙያ ስፌት በወገብ
ላይ የሚውል ነገር ኹሉ ወገብጌ ይባላል።
ዋንዛጌ
= የዋንዛጌ ፤ (ጌ ዋንዛ) ትርጉም - ያገር ስም፣ በታችኛው ወግዳ ሰሜን በተጕለት ያለ አገር። ዋንዛ ያለባት ምድር ማለት ነው።
ሐረርጌ
= ሐረር ለዐዲስ አበባ ምሥራቅ የሚኾን ብዙ አውራጆች ያሉት ትልቅ ከተማ። የሐረርጌ ፤ (ሐረር - ጌ) ትርጉም
- ምድረ ቈላ፣ በረሃ፣ ከአዋሽ ማዶ ያለ አገር፣ የዱሮ ዘመን ጠቅላይ ግዛት።
ይተጌ
= የእተጌ ትርጉም -ይተጌ ፤-እት ፤ የምድር እመቤት። የእተጌ (ዎች) ፤ እኀተ
ሐፄጌ) ትርጉም - ይተጌ፣ ንጉሥ፣ እቴ የሚላት፣ የንጉሥ ሚስት፤ ባለኩል፣ ርስቱን፣ ጕልቱን
እንደ እት፣ ተካፍላ የምትገዛ፣ የሴት ንግሥት። (ግጥም) ዐሊ ማን ይላታል ሲጠራ እናቱን ፤ እኛስ እንላለን
እተጌ መነን። እተጌ ሰብለ ወንጌል፣ እተጌ ጣይቱ እንዲሉ። ጌን ተመልከት።
አና፣ የ፣ ተወራራሽ ስለ ኾኑ እተጌ፣ ይተጌ ተብሎ ይነገራል።
ላምጌ
= ፎገራ ውስጥ ከደራ አጠገብ ያለች መንደር።
ንብጌ
= አገር ፤-ናበ። ንብ ያለበት አገር በቡልጋ ውስጥ የሚገኝ።
የግእዝ መጽሐፍ መሐግል ይለዋል ፤ ማሰሪያ ማለት ነው።
ዐዲስጌ
= በተጕለት ወስጥ የሚገኛ አገር ፤ ከዜጋ ወደም በስተግራ ያለ ቀበሌ። (ሐዲስ - ጌ) ፤ ሐዲስ የሚባል ሰው ምድር።
ዕጨጌ
(ሐፄጌ) = አቡን ጳጳስ። (ግጥም) ፤ መኳንንቱ ሠለጠኑ ፤ የጨጌን አገር እመኑ። እኔ የምፈራው ይህነን ፤ ካቡን በላይ መኾን። የምድር ዕጮኛ ፤-ዐጨ ፤ ዕጨጌ።
2. የምድር፣ ዕጮኛ ፤ -ዐጨ። 3. [ነገር ስም] የወላይታ ቋንቋ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በወላይታ አገር ሞተሌሚ የሚባለውን ንጉሥ
አስተምረውት ከዐረመኔነት ወደ ክርስትና ስለ መለሱት የወላይታ ሐዋርያ ለማለት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጨጋ ይሉአቸው ነበርና እጨጌ
ከዚያ ከወላይታ ቋንቋ የተወረሰ ቃል ነው። 4. የደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህር ዕጨጌ ሊቀ ካህናት ከመንግሥት ሲሶ ግብር መቀበል።
ዐምባላጌ
= 1. በትግሬ ግዛት በደቡብ የሚገኝ ትልቅ ጋራ አምባ። 2. የዐምባላ ምድር ፤ አገር። ዐምባ ዐላጊ ቢል ግን ትርጓሜው ሌላ ነው።
3. በትግሬ ግዛት በደቡብ የሚገኝ ትልቅ ጋራ አምባ።
ዐንገትጌ
= 1. ያንገት ስፍራ ፤ ዐንገትን የሚሸፍን የእጀ ጠባብና የቀሚስ የጥብቆ ክሣድ
፤ በስተላይ ያለ ጫፍ (ዘፀ ፳፰፡፴፪)። 2. በአንገት ላይ የሚውል ልብስ የካፖ የኮት የእጀ ጠባብ ቅንፋት (ክሳድ) የሚውልበት
አንገትጌ ይባላል።
ፍንጥርጌ
= በጠራ ውስጥ ያለ ቀበሌ ፤ የፍንጥር ምድር ማለት ነው።
ቅዱስጌ
= በቡልጋ አውራጃ ያለ አገር ፤ የተቀደሰ ምድር ፤ ወይም (ቅዱስ - ጌ) ፤ አንድ ቅዱስ የኖረበት የጸለየበት የሰበከበት የቅዱስ አገር ምድር ማለት ነው። ነገር ግን ምድር የምትነገረው በሴት አንቀጽ መኾኑን አስተውል።
ራስጌ
= 1. በስተራስ በኩል ያለ ስፍራ የግርጌ አንጻር። 2. [ነገር ስም] ከወደላይ የሚኾን ነገር በመኝታ ጊዜ ራሱን የሚያሳርፍበት ወደ ራስ ወገን
ሰላምጌ
= (ሰላምጌ ማሪያም)
የሰላምጌ ማርያም ቤተክርስትያን በሰቆጣ ወረዳ 031 ቀበሌ ሰላምጌ በተባለ ጎጥ የምትገኝ ጥንታዊ ቤተክርስትያን ነች። ሰላምጌ ማርያም
ስያሜዋን ያገኘችው እዚያው ቀበሌ ውስጥ ከሚገኝና ‹‹ የሰላም ዋሻ ›› የሚል ትርጉም ከተሰጠው ዋሻ ነው። ለዐርባ ዓመታት በዋሻው
ውስጥ እንደቆየችና በኋላ ግን ሲራክ የሚባል መነኩሴ ድንኳን በመትከል አስቀመጣት ኋላ፣ ኋላ 12 መነኩሳት ደግሞ የየራሳቸው ባለ
አንድ ክፍል የጸሎት ቤት በመትከል መግቢያም መውጫም ያለው በር በመሥራት የጸሎት ያደርሱ ነበር በዚያን ግዜ እነዚህ 12 ጸሎት
ቤቶች ተገጣጥመውም 12 ክፍሎች ያሉት እቤተ መቅደስ ሆኑ። ይህም ቤተ መቅደስ የተሠራው ከክርስቶስ በፊት እንደሆነ ይነገራል ዐሥራ
ሁለት ክፍሎች ዛሬም ድረስ በቤተክርስትያኑ ህንፃ ውስጥ ይገኛሉ። የጥንት አሠራራቸውም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት አልተቀየረም። የሰላምዕ
ማሪያም ቤተክርስቲያን የዉስጥ ክፍል ለዊያዊን ካህናት ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ኦሪት አምልኮተ እግዚአብሔር
የሚካሄድባቸው ቤተ እምነቶችን እንደሠሩ በታሪክ ይወሳል። ከነዚህም መካከልም ጣና ቂርቆስ፣ መርጡላ ማርያም፣ ደብረዳምና ተድባበ
ማርያም የሚጠቀሱ ናቸው። ሰላምጌ ማርያም ከእነዚህ አቻ እድሜ ያላትና በሕገ ኦሪት አምልኮት እግዚአብሔር ይካሄድባት እንደነበረ
እና ከአክሱም ጽዮን ቀጥላ በዘመነ ኦሪት ከተሠሩ ቤተ እምነቶች አንዷ እንደነበረች በታሪክ ይነገራል። ሰላምጌ ማርያም የበርካታ
ጥንታዊ ቅርሶች ባለቤት ነች። ጥር 21 የንግሥ በዓሏ ነው።
ድጌ
= 1. መቀነት ፤-ደገደገ። 2. [ነገር ስም] ሃያ ዐምስት ወይም ሠላሳ ክንድ
የሚሠራና ወንድ ወደ መንገድ ሲሔድ የሚታጠቀው (አስ) ድጉን ሸብ አደረገ (መቀነት ([ግዕዝ])። (ከግእዝ በቁሙ መቀነት የሆድ
ካሳ የወገብ ምሳ ወገብ የሚያጠና የሚደግፍ። መቀነት)
በከሣቴ ብርሃን ከዚህም ከዚያም የተቀነበበ