Wednesday, July 5, 2017

ላይ ከራስ ዱሜራ. . .




ላይ ከራስ ዱሜራ፣ ራስ ካሳር አቋርጦ ሃገረ ኤርትራ
የኑብያ አሸዋን ጠፍጥፎ በናስር ውሃ ጋዛ ፒራሚድ የሠራ
ካታንጋ ከታላቁ ካሮ ኬፕታውን ኮይኮይና ሳን ስልተ ቀመሩ
ታች ካልሃሪ፣ ሳህራ፣ ቲምቡክቱ ሰንጥቆ ዳካር ጫፍ ድንበሩ
ሰፊው እግሬ አንድ አገር በአንድ ጊዜ ረጋጩ
ጣና፣ ቪክቶሪያ፣ ቮልታ፣ ቻድ ውሃ መጣጩ
ከኪሎማንጃሮም በላይ የሰፋ፣ የረዘመ ደረቴ
ከነዳሽን፣ ከነካሜሩን በላይ የዘለቀ አንገቴ
በቀኝ አንድሮሜዳን ጨብጦ በግራ ስድስቶ
አፍሶ የሚያድር እጄ ከዋክብት አስፈርቶ
ጠቆር ብዬ ቡና፣ እልፍ ምእልፊት ደቂቃኑን የማቃና
ራሴ ላይ የሚታሰረው ምልክት የሰማዩ ቀስተ ደመና
ልቤ ገር ስንት አገር አስልጦ፣ አሳልጦ ሳይገዛ ተገዢ
ደሜ እንዲሁ ደመ መራር ሕዋሱ እንደ ፍል ተባዢ
የጥፍሬ ጥጋጥግ ረዝሞ ጥቁር የቀለመው
ሜዳና ሸንተረር ጋራ ቧጭሮ የሚያፈርሰው
በቶም ቶም ጉባዔ ቃና ባልፉን ካሊምባ መትቼ
በኮራ ገመድ ክራር ማሲንቆ ራሴን አጫውቼ
ድቤ አታሞ ከበሮውን ጀምቤውን ደብድቤ
ስለው ዳንሱን በድንበር በአጥር መች ተገድቤ
ሺ አፍሼ ሺ የምዘራ ዛፎችን በአንድ እፍኝ ቀጣፊ
የእግዜሮች ባርያ ታማኝ ጥቁር አጋፋሪ ጥቁር አሳላፊ
ምሥጢሬን ሳንሶላስል በዜማ በዳንኪራ
የጠራች እውነት በራሴ ኩራዝ ሳበራ
እነማን ቀድመው ሰሙ? እነማን ቀድመው ሰገዱ
ወይስ ስተው፣ ነጭ እንዲቀልም ጥቁር ሰው አረዱ?  

ዕለተ አማኑኤል ሰኔ፣ 2017