ቀስ በቀስ ቻይና በእግሯ ትሄዳለች
የኛና የቻይና የፍቅራችን ጡዘት
የመናበባችን የአንድነታችን ልኬት
ለነሱ ሥራቸው ለኛም ተረት ተረት
ፍሬውን ያፈራል አይቀር እንደ ዘበት
እነ ቹንግ፣ እነ ቹ፣ እነ ፔንግ የዘሩት ፍሬ ሲያፈራ
ቤስት ቢፎር ተብሎ በስቃጥላ ሲታሸግ እንጀራ
ጫት በቡጥሌ ሲሸጥ እንደ ቢራ
የቻይና ሰልዳቶ እድርን ሲመራ
ቹቹ ቹንግ ዕቁብ ሰብሳቢ ዳኛ ሲባል
ገመቹ ቹ ሃን ሲሆን ፓርላማ አባል
ያሳመመን እምዬ ቻይና መልሶ ያከመን ለታ
የቻይና ዲቃላ ክራር እየመታ ሲጫወት ትዝታ
የቻይና ደብተራ ማኅሌት የቆመ ቀን
አበበ ዘይቱንግ ሼኪ ሆኖ ቁርዓን ሲቀራልን
በቻይ-ማርኛ ትምህርት ሲቀዳልን
በቻይ-ግርኛ ሙያ ስንሠለጥን
በቻይ-ሮምኛ የተግባባን ለታ
ቻይንኛ ሲሆን የኛ ፊደል ገበታ
ማዳም ቾንግን ገረንችኤል በሰርግ ሲያገባ
ማዳም ሶንግን ገመቺስ ሊጠብስ ሲያግባባ
ማዳም ፔንግ ጠጅ ጥላ ሊፍታና ሲቆሮ ከጠጡላት
ማዳም ቺንግ አብሲጥ ጥላ እንጀራ ከወጣላት
በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን
የባሕል ልብሱን ለብሶ ሸክፎ ኮተቱን
አደባባይ የወጣ ዕለት ሊያሳይ ትርዒቱን
እነ ቡቺ፣ እነ መቻል ከመንደር ሲጠፉ
እነ ውሮ እንደ ዶሮ በንኩቤተር ሲቀፍቀፉ
ነውርና ኩነኔን ኤክስፖርት አርገናቸው
ይሉኝታና ሼምን ጠብሰን በልተናቸው
እና . . . እና አንቺ አለሚቱ ነሽ ጫልቱ የበረገድሽው ጭን
ፍሬ ባያፈራ ነው አብዝቶ የሚቆጨን
አንተም ተክላይ፣ አንተም ቢራቱ፣ የገለባችሁት ቀሚስ
ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ይወለዳል አንድ ቅዱስ
እና በዚህ መልኩ ዓይናችን ጠቦ. . . ጠቦ. . . ጭራሽ የጠፋ ዕለት
ያ ቅዱስ ቻይና ይመራናል እጃችንን ይዞ አንድ ቀን ወደፊት
ያኔ ከእንቅልፋችን እንነቃ እና እንተርታለን ተረት
ለተረት ማን ብሎን ተክነነዋል ድሮም ከጥንት
«ቀስ በቀስ ቻይና በእግሯ ትሄዳለች
አገር የሚያክል ነገር ክፍለ ሃገሬ ትላለች።»
የካቲት 8፣ 2009 ዓ.ም.
ብሩክ በየነ