ያገባ ሆነ ያላገባ፣ ሊያነበው
የሚገባ
ብታገባም ባታገባም ይህ ሊያመልጥህ አይገባም…
(ከበይነመረብ፣ ምንጩ ከማይታወቅ የተወሰደ፣ ውርስ ትርጉም፦ በብሩክ በየነ)
ያን ቀን ምሽት ቤቴ ስገባ፣ ባለቤቴ እራት እያቀራረበች ነበር። እጆቿን
ያዝኩ እና “የሆነ ነገር የማናግርሽ ጥብቅ ጉዳይ አለኝ” አልኳት። ምንም ሳትተነፍስ ቁጭ ብላ በዝምታ እራቷን መብላቷን
ቀጠለች። ዓይኖቿ ውስጥ እየተሰማት የነበረውን ጉዳት ማስተዋል አላተሳነኝም።
በሆነ አንዳች ምክንያት ልነግራት ያሰብኩትን ነገር መናገር አልቻልኩም። ወጣም ወረደ ግን ውስጤ ያለውን ጉድ
መንገሩ አማራጭ የሌለው ግዴታዬ ነው። እራሴው ብነግራት ይሻላል። ሌላ ምንም አማራጭ የለኝም። አዎ! ከእሷ ጋር መፋታት እፈልጋለሁ። ጉዳዩን ረጋ ብዬ፣ ቀስ በቀስ
ተነፈስኩላት። ቃላቶቼ ያበሳጩዋት፣ ቁጣን የጫሩባት በጭራሽ አትመስልም። ይልቁንስ፣ ለስለስ ባለ ድምፅ “. . .ግን ለምን?” ስትል
ብቻ ጠየቀችኝ።
ለጥያቄዋ በቀጥታ መልሱን መስጠት አልፈለግኩም ወይም መልስ ልሰጣት ስለማልችል
ዙሪያ ጥምጥም ማውራት ጀመርኩ። ይህን ጊዜ ግን ደሟ ፈላ። ስትበላበት የነበረውን ሳህን አነሳችውና አሽቀንጥራ ወረወራ ከግድግዳው ላይ
ለተመቸው። “ወንድ አይደለህም! ሴታ ሴት!” ስትል አምባረቀች።
የዛች ቀን ሌሊት ሌላ ምንም ነገር አልተነጋገርንም፣ በቃ እንደተዘጋጋን
አደርን። ድምፅ ሳትሰማ ስቅስቅስ ብላ ማልቀሷን ግን አላቋረጠችም። ትዳራችንን ምን ሳንካ እንዳጋጠመው ለማወቅ አጥብቃ
እንደምትፈልግ አሳምሬ ተረድቼዋለሁ። ሆኖም ግን ምንም ዓይነት አጥጋቢ መልስ ልሰጣት እንደማልችል አውቀዋለሁና ባልሞክረው ይሻለኝ
ነበር፤ ከሷ ይልቅ ልቤ በሶስና ፍቅር ተሸንፏል። ሸፍቷል። ለሷ የቀረ ምንም ዓይነት እንጥፍጣፊ ስሜት በውስጤ የለም። አሁን
ግን አዘንኩላት! በጸጸት ስሜት ተሞልቼ ቤታችንን፣
መኪናችንን እንዲሁም ከንግድ ድርጅቴ የሚገኘውን ትርፍ በየወሩ ሲሶውን ያለ ምንም ችግር መውሰድ እንደምትችል የሚያረጋግጥላትን
የፍቺ ስምምነት ውል ረቂቅ አዘጋጀሁ። አዘጋጅቼ ስጨርስና እንድታነበው ስሰጣት ሰነዱን በጨረፍታ ተመለከተችው እና ብጫጭቃ
ጣለችው። ከሕይወት ዘመኗ አሥር ዓመታት ያክል ከእኔ ጋር የኖረችው ሴት ዛሬ ፍጹም ሌላ የማላውቃት እንግዳ ሴት ሆናብኛለች።
ከእኔ ጋር ላጠፋችው ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ሁሉ ከልቤ አዘንኩላት፤ ቢሆንም የሶስና ፍቅር ከቁጥጥሬ ውጪ ሆኖ ሊያሳብደኝ
ደርሶ ስለ ነበር አንዴ ከአፌ የወጣውን ነገር መልሼ ልውጥ የምችልበት ምንም ምክንያት አልነበረኝም። በስተመጨረሻ ያለ ድምፅ
መነፋረቋን አቆመች እና ጭራሽ ፊት ለፊቴ መጥታ በገሃድ እዬዬዋን አቀለጠችው። ይህ እንደሚሆን አስቀድሜ ገምቼው ስለ ነበር
ብዙም አልተደናገጥኩም። እንደ እኔ አረዳድ ውስጧ የታመቀውን ንዴት እና ቁጭት እንዲወጣላት የሚረዳት ብቸኛ አማራጯ ለቅሶዋ ነው። ለሳምንታት ሳወጣና ሳወርድ፣ ውስጥ
ውስጡን ሳብሰለስለው የሰነበትኩት የፍቺ ሐሳቤ አሁን ቁርጥ ሆኗል፣ በተጨባጭ ለይቶለታል።
በማግስቱ፣
የዛን ቀን ምሽት አምሽቼ ወደ ቤት ተመልስኩ። ጠረጴዛው አጠገብ ቁጭ ብላ የሆነ ነገር ስትጽፍ አገኘሁዋት። እራት ባልበላም
በቀጥታ ያመራሁት ወደ መኝታ ቤቴ ነበር። ሙሉ ቀን ከሶስና ጋር ምርጥ ጊዜ አሳልፌ ስለ ነበረ እና በጣም ደክሞኝ ስለ ነበረ
እንቅልፍ እስኪወስደኝ አፍታም አልቆየም። መኻል ላይ ስነቃ፣ አሁንም ጠረጴዛው ላይ አቀርቅራ እየጻፈች እንደነበረ አይቼያለሁ።
የራሷ ጉዳይ ነው። ምንም ደንታ ሳይሰጠኝ ገልበጥ ስል ወዲያውኑ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ መልሶ ወሰደኝ።
ጠዋት ላይ፣
በሰላማዊ መንገድ ልንፋታ እንችላለን ያለቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በወረቀት ከትባ ሰጠችኝ፦ ከእኔ የምትፈልገው ምንም ቤሳ ቤስቲን
ሳንቲም የለም፤ ሆኖም ግን ፍቺው ሙሉ በሙሉ ከመከናወኑ በፊት የአንድ ወር ጊዜ እንድሰጣት ትፈልጋለች። በዚህ በተባለው የአንድ
ወር ጊዜ ውስጥ በተቻለን መጠን በመካከላችን ምንም እንዳልተፈጠረ አስመስለን ለመኖር የሚቻለንን ሁሉ ጥረት ሁለታችንም
እናደርጋለን። ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረበችውን ሰበብ ለመረዳት ብዙም አልተቸገርኩም፤ ልጃችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፈተና
ስለሚፈተን በእኛ የፈረሰ ትዳር ምክንያት ከትምህርቱ ላይ ትኩረቱን አጥቶ ትምህርቱ መስተጓጎል የለበትም፥ ይህ እንዲሆን እሷ በጭራሽ
አትፈልግም። ይኼ ቅድመ ሁኔታ ለእኔ ምንም ችግር አልነበረውም፤ ግጥም አድርጌ ተስማማሁ። ከዚህ በተጨማሪ ግን አንድ ሌላ
የምትጠይቀኝ፣ መፈጸም ያለብኝ ሌላ ግዴታ ደግሞ አለ፤ የሠርጋችን ምሽት እንዴት አድርጌ አንክብክቤ ተሸክሜ ወደ መኝታ ቤታችን
እንዳስገባሁዋት እንዳስታውሰው ጠየቀችኝ። እናም በሚቀጥለው ቀሪ የአንድ ወር የትዳራችን ጊዜ ወደ ሥራዋ ስትሄድ ከመኝታ ቤታችን
እስከ ቤቱ በራፍ ድረስ ልክ እንደዛው አድርጌ እሷን ተሸክሜ እየወሰድኩ እንዳስወጣት ብቻ ከእኔ ትፈልጋለች። ያበደች ነገር ሆኖ
ተሰማኝ። ቢሆንም የቀረንን አብረን የምናሳልፈውን ጥቂት ጊዜ ለሁለታችንም አስቸጋሪ እንዳይሆን፣ እንዲሁም ከመጨቃጨቅ ብዬ ግራ
የሆነ ጥያቄዋን ያለማንገራገር በእሽታ ተቀበልኩት።
ሚስቴ ስለ ፍቺው
ስላቀረበችልኝ ቅድመ ሁኔታ በተመለከተ ለሶስና ነገርኳት። ከት ከት ብላ ከሳቀች በኋላ የሚስቴ ሐሳብ የእብደት ቢጤ መሆኑን
ነገረችኝ። እያላገጠችም “ምንም ዓይነት መላ ታምጣ፣ ታውጣ ታውርድ፣ ወደደችም ጠላችም፣ ፍቺው እንደሆነ አይቀሬ መሆኑ ሊዋጥላት
ይገባል” አለች።
እኔና
ባለቤቴ እንድንፋታ እንደምፈልግ ለእሷ በግልጽ ከተናገርኩባት ቅፅበት ጀምሮ አካል ለአካል፣ ገላ ለገላ በጭራሽ ተነካክተን
አናውቅም። እና በመጀመሪያው ዕለት ተሸክሜ ይዤያት ወደ ውጭ ሳስወጣት፣ ሁለታችንም የአዲሱ ጨዋታ አጨዋወት ዘይቤን
አልቻልንበትም ወይም አልተዋጣልንም። ልጃችን ከኋላችን እያጀበን ትርዒቱን በጭብጨባ አዳመቀው፣
“አባቢ
እማሚን ተሸከማት”
ጮቤ ረገጠ።
የተናገራቸው ቃላት ውስጤን ሰርስረው ገብተው ወዲያው ሰላም ነሱኝ። ከመኝታ ቤቱ እስከ ሳሎን ቤቱ ከዚያም እስከ ቤቱ በራፍ፣ እሷን
በእጄ እንዳንጠለጠልኩ ወይም እንደታቀፍኩ አሥር ሜትር ያክል ተራምጄያለሁ። ዓይኖቿን ጨፈን አድርጋ በሹክሹክታ “ለልጃችን
ስለፍቺው ምንም ነገር እንዳትነገረው” አለች። እየተከናወነ ባለው የማይገባ ጨዋታ ቅር ብሰኝም ለጥያቄዋ መስማማቴን ለማረጋገጥ
ጭንቅላቴን አወዛወዝኩላት። በራፉ ላይ ስንደርስ አወረድኳት። ወደ ሥራ የሚወስዳትን አውቶቡስ ወደ የምትጠብቅበት አቅጣጫ በእግሯ
ሄደች። እኔም ብቻዬን ወደ ቢሮዬ በመኪናዬ አመራሁ።
በሁለተኛው
ቀን፣ ከትላንቱ ይልቅ ሁለታችንም ይበልጥ ዘና ብለን በተሻለ አኳሃን ቲያትሩን ተጫወትነው። ደረቴ ልጥፍ ብላ ተኛች። የሹራቧ ሽቶ
መዓዛው ሲያውደኝ ተሰማኝ። ይህችን ሴት ለረዥም ጊዜ ልብ ብዬ አስተውዬ አይቼያት እንደማላውቅ ተገነዘብኩ። የወጣትነት አፍላ
ዕድሜዋ እንዳለፈ ምልክቶችን ማየት ጀመርኩ። ፊቷ ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሽብሽቦች መቋጠር ጀምረዋል፣ ጸጉሯም እየሸበተ ነው! የትዳራችን
መንኮታኮት እና የማብቃቱ ምልክቶች በእሷ ላይ ቀድመው በግላጭ እየታዩ ነው። ለአንድ አፍታ፣ “ይኼን ያክል ምን መጥፎ በደልኳዋትና
ነው ይኼን ያክል የምታካብደው” ብዬ ራሴን ለመጠየቅ ተገደድኩ።
በአራተኛው ቀን፣ ልሸከማት ሳነሳት፣ በመካከላችን
የሆነ ለየት ያለ የመቀራረብ ዓይነት የመሰለ ስሜት እየተጠነሰሰ እንዳለ ታወቀኝ። ይህች ሴት ከዕድሜዋ አሥር ዓመት ያክሉን ለኔ
የሰጠችኝ ሴት ነበረች። በአምስተኛው ቀን፣ በመኻላችን ያለው ይህ የመቀራረብ ስሜት አሁም ይበልጥ እየጎለበትና እያደገ እየሄደ
እንዳለ እየተረዳሁት መጣሁ። ስለዚህ ነገር፣ ለሶስና ምንም ትንፍሽ ማለት አልፈለግኩም። ወሩ እልም ብሎ በሄደ ቁጥር እሷን
መሸከሙ ግን ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ እየቀለለኝ እየሄደ ነበር። በየቀኑ እንድሸከማት በመገደዴ ምናልባት ከበፊቱ ይልቅ ሰውነቴ
እየጠነከረ ስለሄደ ሊሆን ይችላል።
አንድ ቀን ጠዋት ምን እንደምትለብስ እያማረጠች
አገኘኋት። በርካታ ቀሚሶችን እየለዋወጠች ሞከረቻቸው አንድም ግን የሚጥማትን ማግኘት አልቻለችም። ሽቅብ ተነፈሰችና “ሁሉም
ልብሶቼ ሰፍተውኛል” አለች። ድንገት ያን ጊዜ ገና በእጅጉ መክሳቷን አስተዋልኩት፣ አይ የኔ ነገር! እንዲያ በቀላሉ ስሸከማት የሰነበትኩት፣
ለካ በመክሳቷ ነው።
ይህን ጊዜ
አንዳች ነገር ሰውነቴን ወረረው… በልቧ ውስጥ ይህ ነው የማይባል ከባድ ሕመምና መሪር ስቃይ አምቃ መያዟ በግልጽ ተከሰተልኝ። ሳይታወቀኝም
በደመ ነፍስ ጠጋ አልኩ እና ጠጋ አድርጌ ያዝኩዋት።
ልክ በዚያች ቅፅበት ልጃችን መጣ፥
“አባቢ፣ እማሚን ወደ ውጭ አታወጣትም እንዴ?”
ለእሱ፣ አባቱ እናቱን ተሸክሞ ይዞ ወደ ውጭ የመውጣቱ ነገር፣ ለሕይወቱ አንዳች ፋይዳ ያለው ትልቅ ቁም
ነገር ሆኖለታል። ባለቤቴ ልጃችንን ወደ እኛ ቀረብ እንዲል በእጇ ምልክት ሰጠችውና ጥብቅ አድርጋ አቀፈችው። በዚህች ባለቀች
ሰዓት ሐሳቤን እንድቀይር እንዳልገደድ ስለፈራሁ፣ እየሆነ ያለውን ላለማየት ፊቴን አዞርኩ። ከዚህ በኋላ እጆቿን ያዝኩና፣
ከመኝታ ቤቱ፣ በሳሎን ቤቱ አድርጌ ወደ ኮሪደሩ እንደተለመደው ተሸክሜ ወሰድኳት። እጆቿ በቀስታ አንገቴ ላይ ተጠመጠሙ።
ሰውነቷን እኔም በተራዬ አጥብቄ አቀፍኩት፤ ልክ የጋብቻችን ቀን የነበረው ሁኔታ ይመስል ነበር።
አንድ ነገር ግን ቅር አሰኘኝ፤ የወፍ ያክል የቀለለው ክብደቷ ውስጥ ውስጤን አንጀቴን በላው። በአንድ
ወሩ የመጨረሻው ቀን፣ አቅፌ ከተሸከምኳት በኋላ አንድ እርምጃ እንኳ ወደፊት መራመድ ተሳነኝ። ልጃችን ትምህርት ቤት ቀድሞ ሄዶ
ነበር። እቅፍ አድርጌ ያዝኩዋትና “ትዳራችን የጎደለው ነገር እንዲህ መቀራረብ እንደነበረ እስካሁን አልገባኝም ነበር” አልኳት።
ወደ ቢሮዬ በመኪናዬ ገሰገስኩ…. የበሩን ቁልፍ እንኳ ስላቆልፍ ከመኪናዬ ዘልዬ ወረድኩ። የሆነ ማናቸውም ዓይነት መዘግየት፣ በውስጤ
ያለውን ሐሳብ እንዳያስለውጠኝ በጣም ፈራሁ…ወደ ፎቁ ተንደርድሬ ወጣሁ። ሶስና በሩን ከፈተችልኝ።
“ይቅርታ ሶስና፣ በቃ አልቻልኩም። ሚስቴን ከእንግዲህ ልፈታት አልፈልግም”።
ትኩር ብላ በድንጋጤ አፍጥጣ አየችኝ፣ ቀስ ብላም በጣቷ ግንባሬን ነካችኝ።
“ምን ትኩሳት ነገር አሞሃል እንዴ?”
ከግንባሬ ላይ ጣቷን ዞር አደረግኩት።
“ይቅርታ ሶስና፣ በጭራሽ እሷን መፍታት አልፈልግም። ትዳራችን ጣዕም አጥቶ አሰልቺ የነበረው ምናልባት እሷም
ሆነች እኔ በሕይወታችን ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን ነገሮች ለእያንዳንዳቸው በሚገባ ዋጋ ስላልሰጠናቸው ሊሆን ይችላል። በመኻላችን
ያለው ችግር እንደ ጥንቱ መፋቀር አለመቻላችን አይመስለኝም። በጋብቻችን ቀን ወደ ቤቴ ተሸክሜ እንዳስገባሁዋት ሁሉ ሞት
እስከሚለያየን ድረስ ልክ እንደ ሠርጉ ቀን እስከ መጨረሻው ልሸከማት ይገባኝ እንደነበረ አሁን ተገልጾልኛል።”
ሶስና ልክ ድንገት ከእንቅልፏ የባነነች ያህል የነቃች መሰለች። የመብረቅ ያክል ድምፅ በነበረው ጥፊ አጮለችኝ።
በሩን በላዬ ላይ ጠረቀመችውና እዬዬዋን አስነካችው። ደረጃዎቹን ቁልቁል ወርጄ መኪናዬን አስነስቼ ከአካባቢው ጠፋሁ። በመንገዴ
ላይ ከነበረው የአበቦች መሸጫ መደብር ገባሁና ለባለቤቴ አንድ ቆንጆ እቅፍ አበባ አዘዝኩ። አበባ የምትሸጠው ልጅ እግር ሴት
በካርዱ ላይ ምን ተብሎ እንዲጻፍልኝ እንደምፈልግ ጠየቀችኝ። ፈገግ አልኩ እና ካርዱን ተቀብያት እኔው ራሴ “ሞት ቀኑ ደርሶ እስከሚለያየን
በየቀኑ ጠዋት ጠዋት እየተሸከምኩ ወደ ውጭ አወጣሻለሁ!” ብዬ ጻፍኩ።
ያን ዕለት ምሽት ቤቴ ስደርስ፣ በእጆቼ አበባዎቹን እንደታቀፍኩ፣ ፊቴ በፈገግታ ተሞልቶ፣ ወደ ላይኛው
ፎቅ በሩጫ ተንደርድሬ ወጣሁ፣ ያገኘሁት ግን ባለቤቴን ሳይሆን አስክሬንዋን ነበር። ባለቤቴ ለበርካታ ወራት በካንሰር በሽታ ስትሰቃይ
ነበር፤ እኔ ግን ከሶስና ጋር ስማግጥ ችግሯን የማስተወልበት ጊዜ አልነበረኝም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደምትሞት ጠንቅቃ ታውቀው
ነበር ነገር ግን በፍቺው ጉዳይ ወደፊት ከዘለቅንበት፣ በልጄ ላይ ማናቸውንም ዓይነት አሉታዊ ስሜት እንዳላሳድርበት እኔን
ለማገዝ ስትል ሁሉን በሆዷ ውጣ ያዘችው።— ቢያንስ ቢያንስ እንደ እሷ አስተሳሰብ በልጃችን ዓይን—- እኔ ትዳሩን አክባሪ አባት ሆኜ መታየት
ነበረብኝ…